Saturday, 20 January 2018 12:36

የቅፅበት ስካር

Written by  መሐመድ ነስሩ (ሶፎኒያስ አቢስ)
Rate this item
(8 votes)

     እህል በረንዳ…የጭነት መኪና ላይ ዕቃ በመጫንና በማውረድ ሞያ የሚተዳደረው ወንድወሰን ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖታል፡፡ በደስታ ለስላሳ መዳፎች እየተዳበሰ ግሏል፡፡ በዕድለኝነቱ ድማሜ ሰክሯል፡፡ ለዓመታት እንደ ቀንድ ተሸክሞት የኖረውን ድህነትን የሚከላበትን ስል ሰይፍ በላከለት ፈጣሪ ጠቢብነት ተደንቋል፡፡
‹‹‹እውነትም ሳይደግስ አይጣላም፡፡› ይህን ሁሉ ዘመን በመከራ ስቀፈደድ፤ በረሀብ ብዛት አፌ ተዘግቶ ሆዴ አፍ ሲያወጣ እያሳየ አልነበረምና! አይ እግዚአብሔር! እነዛን ሁሉ ዓመታት ፀጥ ያለኝ ቸል ብሎኝ አልነበረም ለካ! ለዛሬዋ ቀን ድግስ ድምቀት ጎንበስ ቀና ሲል ኖሯል ለካ! ተመስገን … ተመስገን!››
……ከኮሾሮ ካርቶን እምብዛም ከማትሰፋው ቤቱ ውስጥ የሳር ፍራሹ ላይ ጋደም ብሏል፡፡ ይህን የመከራ አመት እንዴት እንደሚሻገረው፣ በየትኛው አቋራጭ መጓዝ እንዳለበት ንድፍ ያወጣል፡፡ የድልድዩን ምንነት በተመስጦ ያስባል፡፡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየተወለጋገደ በየትኛው ጉልበት ተጉዞ እንደሚጨርሰው ያጤናል፤ ይህንን እንደ ጎለጎታ ተራራ ቆሞ የሚታየውን አመት!
…ይሄኔ ነበር የከረከሰችው ራዲዮው ‹የሎተሪ ዕጣ…› የሚል ድምፅ ያሰማችው፡፡ በቸልተኝነት ነው የሚጠራውን ቁጥር ከኪሱ ካወጣው ሎተሪ ትኬት ጋር ሊያመሳስል የሞከረው፡፡
 ፌሽታ!
መቶ ሺህ ብር፤ አንድ መቶ ሺህ ብር…! ፈፅሞ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም፤ ፈፅሞ!
‹‹አምላኬ … አምላኬ … አምላኬ!››
መሬቱን ሳመ፡፡ ተነሳ፡፡ ዘለለ፡፡ እጆቹን አወናጨፈ። እግሮቹን አወራጨ፡፡
‹‹ቡትቶ መልበስ ቀረ!
መራብ ቀረ!
ከኩንታል ጋር መታገል ቀረ!
ድህነት ደህና ሰንብት!!!››
…የለበሰውን ልብስ ተመለከተው፤ መቀደድ የጀመረ ሻማ ጃኬት፣ ከስሩ ምንም አልለበሰም፤ የለውማ! ከወገቡ ግድም ጀምሮ ያለውን የሰውነቱን ክፍል ተመለከተ፤ ተጨረማምቶ የዘጠና አመት አሮጊት ፊት የመሰለ ካኪ ሱሪ! ቀፈፈው! ጃኬቱን አውልቆ ጣለ! ሱሪውን አውልቆ ጣለ!
‹‹ቡትቶ መልበስ ቀረ…! አምላኬ - አምላኬ!! ምን ይሳንሃል አንተ? … ምን ይሳንሃል?!!››
አዕምሮውን እንደገዛ ፍራሹ ላይ ቁጭ ብሎ ለማሰብ ሞከረ፡፡ በግርግዳው ቀዳዳዎች የሚገባው ንፋስ ‹ጠቅ› ሲያደርገው አለመልበሱን አስተዋለ፤ እየሳቀ ሱሪና ጃኬቱን መልሶ ለበሰ፡፡
‹‹ለዛሬ ምሽት ብቻ ነው የጥንት ወዳጆቼ!›› አላቸው፤ መልስ አልሰጡትም - ልብሶቹ፡፡
‹‹እሺ - ምንድነው የማደርግበት?›› እቅድ ለማውጣት ሞከረ፡፡ ሥራ እጅግ የሚበዛ ሰሞን ጥቂት አስሮችን ቆጥሮ ይሆናል፡፡ ከዛ ባለፈ ይህን የሚያህል ገንዘብ እጁ ገብቶ አያውቅም፡፡ ግር ብሎታል፡፡
‹‹…መኪና እገዛለሁ›› አለ፡፡
‹‹አዎ አሰሪያችን መስፍን በመኪና ነውኮ ሀብት በሀብት የሆነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ መኪና እገዛለሁ። ከዛ በሚገኝ ገቢ ሌሎች መኪኖችን እጨምራለሁ፡፡ከዛ ትልቅ ሆቴል እከፍታለሁ፡፡ በጣም ታዋቂ ሆቴል! እነሸራተንን እንደነ ከድር ሻይ ቤት የሚያስቆጥር ሆቴል!›› በሳቅ ደመቀ…
‹‹…መኪና ላይ የሚሰራ ታማኝ ሰው ያስፈልገኛል፤ … ማነው መስራት ያለበት? ማን?! … ማን?! አዎ.. . ባልደረባዬ ተሾመ፤ እሱ ታዛዥ ነገር ነው፤ እንደፈለግኩ ላዘው እችላለሁ፡፡››
አንድ ነገር ትዝ አለው፡፡
‹‹አይ … አይ… ተሾመ መሆን የለበትም። ‹ፈርቅ› በመያዝ ይታማል፤ ከአንድም ሁለቴ፤ ከሁለትም ሶስቴ … ኩንታል ወግቶ በቆሎ ሸጧል ብሎ ሲቆጣ ነበር መስፍን፡፡ እሱማ ያራቁተኛል … በበቆሎ ያልታመነ … እንዴት በመኪና ይታመናል? አይሆንም! … ታዲያ ማን?!››
በሻከሩ እጆቹ ረጅም ፊቱን ሞዠቀ፤
‹‹ማን?! … ኦ! … ሱልጣን … እሱ ታማኝ ነው፡፡ አንድም ቀን በማጭበርበር ታምቶ አያውቅም፡፡ ብቻ አሰሪያችን ሲፈልገው ስለማያገኘው ይበሳጭበት ነበር። ሰላት እያለ መስጊድ ስለሚመላለስ፡፡ ይሄ ታዲያ እኔን ያሰጋኛል እንዴ? ተሳፋሪዎችንና እህል የሚጭኑልኝ ነጋዴዎችን ያጉላላብኛል … ቢሆንም ይሁን!››
ጥቂት አሰበ፡፡
‹‹የለም! መሆን የለበትም፡፡ ‹ደንበኛ ንጉስ ነው› አይደለ የሚባል፡፡ እነሱን ካስከፋብኝ ምን ሊቀረኝ። በመኪናዬ የሚጭን ሰው ላይገኝኮ ነው፡፡ ያ ደግሞ ኪሳራ ነው፤ አይ ሱልጣንም አይሆንም! … ታዲያ ማን? …›› ኮስተር፤ ከባድ ሂሳብ በማስላት ላይ እንዳለ ተማሪ! … ፊቱን ኮምጨጭ፤ በቀዶ ጥገና ላይ እንዳለ ዶክተር!
‹‹…በቀለስ ቢሆን?! … ይሆናል … ይሆናል… ሲሰራ ደከመኝ አያውቅም፡፡ ብረት ነው፡፡ ‹ባሌስትራ› ነው ቅፅል ስሙ፤ በጣም ጥሩ ነው፡፡ መኪናዬ ድንገት ብትበላሽ እንኳን ጎትቶ ሊያመጣት ይችላል፡፡›› ፈገገ፡፡
‹‹በቀለ ግድንግድ ነው፡፡ ኮስታራ ግንብ!፡፡ … ሳስበው ግን ኮስታራነቱ ጥሩ አይመስለኝም፡፡ ‹‹ፈገግታ የሌለው ሱቅ አይክፈት›› ብሏል ሼክስፒር፤ የሚል ነገር በቀደም የገዛሁት ዳቦ የተጠቀለለበት ጋዜጣ ላይ አንብቤያለሁ፡፡ የታላቅ ሰዎችን ነገር መስማት ጥሩ ነው … ደሞም መኪናን ከሱቅ ምን ለየው … ያው አይደል? ደንበኞቼን ያስፈራራብኛል ይሄ ሰው … አይ በቀለም አይሆንም፡፡››
….በሚገዛው መኪና ላይ በታማኝነት ሊሰራለት የሚችል ሰው በመፈለግ ላይ ነው፡፡ ሁነኛ ሰው ማግኘት ቸግሮት ይማስናል፡፡
‹‹ወይ ጉድ! ከዛ ሁሉ ሰው አንድ የረባ ሰው ይጥፋ…!›› ተከዘ
‹‹ማንን ልቅጠር?››
‹‹አገኘሁት … አገኘሁት!›› ማፏጨት ያዘ
‹‹ታዲዮስ አዎ… እሱ ጥሩ ልጅ ነው፡፡ ከኔ ጋርም ቅርርብ አለው፡፡ ታታሪነቱ የተመሰከረለት ነው፡፡ ታማኝነቱም ቢሆን አያጠራጥርም፡፡ ታታሪና ታማኝ ሰራተኛ ያዋጣል!›› ፈገግታ ፊቱን ሞላው፡፡ ፊቱ ላይ ያልቆየ ፈገግታ!
‹‹….ታታሪነቱና ታማኝነቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ፤ ታዲዮስም ችግር አለበት፡፡ ማዳበሪያዎችን በአግባቡ ባለማስቀመጡ ተሰርቀዋል፡፡
‹ከየት አባቴ አምጥቼ ነው ሀምሳ ማዳበሪያ የምገዛው?› ብሎ ሲጨናነቅ ነበር፤ ትላንት፡፡ ይሄ የሚያሳየው እንዝህላልነቱን ነው፡፡ እንዝህላል ሰው ደግሞ ለእንደኔ አይነቱ ባለሀብት አዋጭ አይደለም።…
‹‹ታዲያ ማን - ?! … ትክክለኛ ሰው በሀገሩም የለም እንዴ እባካችሁ?!››
ተበሳጨ፡፡ ገንዘብ ተገኝቶ ሰራተኛ ሊሆን የሚችል፤ ያ ብር እንዲራባ ትክክለኛ አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል ሰው መጥፋቱ አናዶታል፡፡
‹‹ከገጠር ላስመጣ ይሆን? ከዘመድ ውስጥ ለአባቴ ደህና ሰው ላኩልኝ ብዬ ልላክባቸው?! ደግሞ እነሱን ሲያሰለጥን ማን ጊዜውን ያባክናል? … ኤጭ!›› እጁን አወራጨ…
ሆዱ ምልክት ሰጠው፤ የተፈጥሮ ጥሪ! ጉዞ ወደ መፀዳጃ ቤት! …
በሩ ጋ እንደደረሰ ቤቱን አስተዋለ፤ ይቺ የኪራይ ቤት፤ ቤት ሳይሆን መቃብር መስላ ታየችው። ከጥበቷ መፈራረስ የጀመረው ጭቃ ግድግዳዋ ‹መቃብር ሳይሻል አይቀርም› አስባለው፡፡
‹‹እንደውም ቤት ልግዛ መሰል…›› ሲልም አሰበ፡፡ ‹‹ሰው እንዴት እዚህ ውስጥ ይኖራል?››
‹‹ትልቅ ቤት ከመሃል ከተማ ብገዛ ‹ሰርቪሶቹን› እያከራየሁ መኖር እችላለሁ፡፡›› አሰላ፡፡
‹‹ው … ው … ከኪራይ የምትገኝ ብር ምኗ በቅቶ ያኖረኛል?! … ባይሆን ለጊዜው ምርጥ ግቢ እከራይና እኖራለሁ፡፡ ቤቱን መኪናው በሚሰራው ብር መግዛት ነው፤ ትንሽ ታግሶ!››
… ወጣ፡፡
ቁጢጥ ብሎ የተፈጥሮ ግዴታውን እየተወጣ ጸጉሩን እያፍተለተለ በሀሳብ ጭልጥ ብሎ ጠፋ፡፡
‹‹ታዲያ ማንን ነው ማሰራት ያለብኝ … ማንን?! በቀደም ከዛ ጋዜጣ ላይ ዲዮጋን ስለተባለ ፈላስፋ አንብቤ ነበር፡፡ ፈላስፋው ሰው የለም ብሎ በቀትር ሰው ፍለጋ ፋኖስ ይዞ ወጥቷል፡፡ ሰው የለም ለካ! ይሄ ፈላስፋ እውነት ብሏል  ልበል?!››
በሰው ተስፋ የቆረጠ መሰለ፤ በዚህ መሀል ግን አንድ አስደንጋጭ ሀሳብ ብልጭ አለበት፡፡
‹‹እንዴ መኪናዬ ቢገለበጥስ?››
ደነገጠ፤ ፊቱ ጠለሸ፡፡
‹‹መኪና መግዛት የለብኝም፡፡ ሌላ ነገር … ሌላ የተሻለ! እንዴ ቢገለበጥ - ጭራሽ ባዶዬን ልቀርኮ ነው፡፡ ማን ተመልሶ የድህነት ጭቶ ያካል! … ላክ የምችልበት ጥፍር አይኖረኝም!››
ሌሎች የሥራ አማራጮችን ለማሰብ ሞከረ፡፡
‹‹…መርካቶ ዱባይ ተራ አንድ ሱቅ ብገዛስ? … አዎ ታማኝ ሰው ገለመሌ እያልኩም አልቸገርም፡፡ ራሴ እሰራለሁ፡፡››
ሁነኛ ሰው የማጣቱን ችግር እንደቀረፈው በማሰብ እፎይታ ተሰማው፡፡
‹‹ደሞ መኪናው በሰላም ይገባ ይሆን? ይገለበጥ ይሆን? እያልኩ ምን አስጨነቀኝ? … ሀብት ላይ ተኝቼ ሳለ ለምን ልሰቃይ? … ስቃይ፣ ጭንቀት ምናምን ባንድ ሀብታም ህይወት ውስጥ ሊከሰቱ የማይገቡ ነገሮች ናቸው፡፡›› ኩራት ልቡን ሞልቶት ከት ብሎ ሳቀ፡፡
ከሰከንድ በኋላ፤
‹‹…ማንስ ደግሞ ከሰው ጋር ሲጨቃጨቅ ይውላል፡፡ የአዲስ አበባ ሰው እንደሆነ ምላሱ ብዙ ካልተንጣጣች ያወራ አይመስለውም፡፡ በዛ ላይ ክርክር መውደዱ! ኤ-ጭ … ከስንት መቶው ጋር ‹ቀንስ አልቀንስም፤ የመጨረሻው ነው፤ የመጀመሪያው ነው።› እያልኩ አልዳረቅም … ኧረ ወደዛ!››
ሰዎቹ ከፊቱ ቆመው የሚገፈትራቸው ይመስል የእጁን መዳፍ ወደፊት እያሽቀነጠረ፡፡
‹‹አዎ መኪና ነው የምገዛው … በማያውቁት ነገር ውስጥም መግባት ጥሩ አይደለም፡፡ በጭነት መኪና ስራ የከበሩ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ አለቃዬ የነበረው መስፍንን ማሰብ ይበቃኛል፡፡ በብር ላይ እየተራመዱ ከሀብት ወደ ሀብት ለመጓዝ ከመኪና የተሻለ ነገር አይኖርም፡፡››
‹‹ድንቅ ሀሳብ!› ሲል ጮኸ፡፡ ‹‹ድንቅ ሀሳብ!››
‹‹ምን ሆኜ ነው እስካሁን?!›› በራሱ ተገረመ፡፡
‹‹ለአደጋው ችግር አይኖርም ኢንሹራንስ አለ፡፡››
‹‹አዎ! ኢንሹራንስ እገባለሁ፡፡ ምርጥ አሳቢ ነኝ አይደል?!›› የመኪና ስራ የተሻለ እንደሆነ በልበ ሙሉነት አመነ፡፡ ተፈጥሯዊ ውሉን ፈፅሞ ሲያበቃ፤ ከቁጢጡ ብድግ እያለ ሳለ፤ … ጧ!! አለ፡፡ የወደቀ ነገር ድምፅ ሰማ፡፡ ሱሪውን ወደ ላይ ሊስብ እየጀመረ… ጧ!
ጎንበስ አለ … ሎተሪው፤ ሎተሪው! 100ሺ ብር! … መቶ ሺ ብር! … በጉድጓዱ ወለል ላይ እየተንሸራተተ ነበር፤ ሸርተተተተተተተተተተተተተ ት…..
‹‹ወይኔ!›› ባረቀ ‹‹ወ-ይ-ኔ!›› ቀኝ እጁን ላከው። አመለጠው፡፡ ወለሉን ለቆ ወረደ - ሎተሪው! ጉድጓዱ አፍ ላይ ደረሰ፡፡ እጁን ወረወረ ወንድወሰን፤ አልደረሰበትም፡፡ መቶ ሺ ብሩ ቁልቁል ተወረወረ! … መቶ ሺ ብር! ቁልቁል የሽንት ቤት ገደል ውስጥ! …

Read 2781 times