Saturday, 20 January 2018 12:34

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

    “ማዕከላዊ ተዘጋ” … አሉ? … እሰይ!!
             
    …እስር ቤትማ ማለት
የሰው የራሱ ሃሳብ ነው፣
ከዐዋቂዎች መልስ ገልብጦ
‹ፈተና ማለፍ› የቻለው፡፡
እስር ቤትማ ማለት
አዙሮ ማየት እያቃተው፣
በራሱ እስካልደረሰ - የሌሎች ህመም ‘ማይገባው፣
የሚኖር እየመሰለ
በየቀኑ የሚሞት ነው፡፡
እስር ቤትማ ማለት
የህሊናው መብራት ጠፍቶ፣
ውድቅት መንፈሱ ውስጥ ደርቶ፣
በጠራራ፣ በብራ
በቀን ብርሃን ‘ሚደናቀፍ፣
ራሱ ከራሱ ሸሽቶ፣
ራሱን ከራሱ አውጥቶ፣
ከጨቋኝ ጉያ ‘ሚወትፍ!!
ወዳጄ፤ እስር ቤት … ግንብና ብረት፣ ካቴናና ሰንሰለት ብቻ አይደለም፡፡ ጨቋኝ መንግስታት ባሉበት ቦታ … አገር፣ ከተማና መንደር እስር ቤት ይሆናሉ፡፡ ከቤትህ ወጥተህ፣ እስክትመጣ ተመልሰህ ጥላና ጭራ (tail and shadow) ይበጅልሃል፡፡ … ያውም በቴክስትና በምልክት ታጅበህ!!
 ግድግዳና ጣሪያ፣ የብረት በርና መስኮት የሌለው፣ ዘበኛና ቆጥ ሰፋሪ እማይጠብቀው፣ ሽንት ለመሽናት ፍቃድ የማያስፈልገው ትበልቅና ዋና እስር ቤት ደግሞ አለ - ‹አለማሰብ› የሚባል!!
ወዳጄ፤ መስኮቶቹን ሁሉ ከፍተህ ዓለምን በተለያየ አቅጣጫ ማየት ካልቻልክ በገዛ ሃሳብህ ታስረሃል!! … ነፃነትህ በውስጥህ ታቃስታለች!! … ታጣጥራለች!! … ተጠያቂው አንተና ሃሳብህ ናችሁ። የታሰርክባቸውን ሃሳቦች በጥሰህ ካልጣልካቸው ለነፍስህ እዳ እያቆየህላት ነው፡፡ አሽቀንጥረህ ከጣልካቸው ግን ራስህን በራስህ ካሰርክበት ጉዳይ ትፈታለህ፡፡
“ሰዎች ነፃ ነን ብለው ያስባሉ፡፡ ምክኒያቱም በመኖር ጉጉት፣ ፍላጎትና ምኞት ስለተጠመዱ ወደ ውስጣቸው አይመለከቱም፡፡ ያልገባቸውና ያጡት ነገር … ፍላጎታቸውና ምኞታቸው ሊያናውዛቸው የቻለበትን ምክንያት ነው፡፡ “Men think themselves free because they are conscious of their valiations and desires, but are ignorant of the causes by which they are led to wish and desire.” የሚለን ባራክ ስፒኖዛ ነው፡፡
ወዳጄ፤ ጨምድደው ከያዙንና ከተጣድንባቸው አጓጉል ሃሳቦች ስንላቀቅ እፎይታና እረፍት ይኖረናል። በምትካቸውም “ዕውነት” ብለን ለምንቀበላቸው ሁሉን አቀፋዊ፣ ውብ፣ ሰዋዊና ዘመናዊ ሃሳቦች ቦታ (room) እናመቻችላቸዋለን። በነዚህ ሃሳቦች በኩልም የሌሎች ሰዎች የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማረቅ የምንችል ይመስለኛል፡፡
“ሃሳብን የምታሸንፈው በተሻለ ሀሳብ እንጂ በጉልበት አይደለም” (Minds are conquered not by arms but by the greatness of the soul” … በማለት የፃፈልንም እሱ ራሱ ነው - ስፒኖዛ!
ጥላቻ የፍራሃትና የበታችነት ስሜት ውጤት ነው ይባላል፡፡ ጥቃትን በጥቃት መመለስ አድሮ ውሎ ይፀፅታል፡፡ አፀፋውን ፍቅር በመስጠት ማሸነፍ ግን ትልቅነት ነው፡፡ ደስታና በራስ የመተማመን ፀጋንም ያጎናጽፋል፡፡
ወዳጄ፤ ነፃነት ማለት ዕውቀት፣ ዕውቀት ደግሞ ራስን መሆን፣ ራስን መሆን ደግሞ መንቃት፣ መንቃት ደግሞ የሌሎችን መብት ሳይነኩ የራስን አለማስደፈር፣ ለጨቋኝ ስርዓትና ኢ-ፍትሃዊነት አለመንበርከክ ይመስለኛል፡፡ ጤነኛ ሰው በስሜት ህዋሳቶቹ በኩል ወደ አእምሮው የሚደርሰውን መልዕክት አላውቅም ካለ፣ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ነገርን ላለማየት ፊቱን ካዞረ …ሊያብል የተኛ እንደሚባለው ዳተኛ ሆኗል ማለት ነው፡፡
ልጆች ሆነን ስናጠፋ “ጥሩ አይደለም እንዳይደገም ተብለን” እንገሰፃለን፡፡ ጥፋት መሆኑን እያወቅን ስንደጋግመውና እኛኑ መልሶ ሲጎዳን የተመለከቱ ዘመዶቻችን “አንጎለ ቢስ” ይሉን ነበር። ወዳጄ፡- “አንጎለ ቢስ” ሆኖ መኖር ይቻላል ማለት ነው?
ቁም ነገሩን እናቆየውና … ሰውየው ቅዠት ቢያስቸግረው ጭንቅላቱን ለመታከም ሃኪም ጋ ሄደ አሉ፡፡ ሃኪሙም መረመረውና፤ “ቀዶ ጥገና ያስፈልግሃል፣ ጭንቅላትህ ተፈቶ ቆሻሻው መጠረግ አለበት” አለው፡፡ ሰውየው ተስማማና ጭንቅላቱ ተፈትቶ ተጠረገለት፡፡ ሐኪሙን አመስግኖ ወጣ። ሐኪሙ መሳሪያዎቹን ሲሰበስብ ከመሃል የሰውየውን አንጎል አገኘ፡፡ ይደነግጥና ሰውየው በሄደበት እየሮጠ፤
“ና! ና! ተመለስ! ተመለስ!” እያለ ሲጣራ … ሰውየው ዞር ብሎ፡-
“ምነው? ለምን?” በማለት ይጠይቀዋል፡፡
ሐኪሙም “ይቅርታ! አንጎልህን ረስቼ አላስገባሁትም” አለው፡፡
“ተወው አልፈልገውም! ወታደርነት ልቀጠር ነው የምሄደው” አለ አሉ አጅሬው፡፡ ይቺ የድሮ ቀልድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹ወታደር› በሚለው ፋንታ ‹ፌደራል ፖሊስ› በሚለው ተተክታለች። ይቺ ቀልድ ከላይ ለተነሳው ጥያቄ “አዎ … ‹ኑሮ› ከተባለ አንጎለ ቢስ ሆኖ መኖር ይቻላል” የሚል መልስ ትመስላለች፡፡ ትስማማለህ ወዳጄ?
በጃኩሊን ትሪሜር በተፃፈው “አፍሪካዊ ፍልስፍና” መጽሃፍ ውስጥ ስለ አፈጣጠር (creation myth) የተጠቀሰው እንዲህ ይላል፡-
ናይጄሪያና አካባኒው በሚኖሩ የዩሩባ ጎሳዎች እምነትና ፍልስፍና አንድን ሰው ‹ሰው› የሚያሰኘው ኦሪ (Ori) ወይም አንጎል (Inner head) ነው፡፡ ዕጣ ፈንታችንም በሱ ይወሰናል ብለው ያምናሉ፡፡ ዩሩባዎች ሰው ሆነው ወደ ምድር ከመውረዳቸው በፊት ካንገት በላይ ያለውን አካላቸውን ጭንቅላት ሰሪው (potter of heads) ኦጃላ ጋ በመሄድ ያሰራሉ፡፡
ኦጃላ ግድ የለሽና ባካና ነው፡፡ ለስራው የሚከፈለውንና ቀብድ የሚቀበለውን ገንዘብ እየረጨ ብድር ተቆልሎበታል፡፡ በዚህ የተነሳ አበዳሪዎቹን ለመደበቅ ሲሸሽ የሚጠፈጥፈው ጭንቅላት በአብዛኛው እርጥብ፣ ሞላላ ወይ እሳት በዝቶበት ያረረ ስለሚሆን ደንበኞቹ ይማረሩበት ነበር፡፡ ለኦጃላ ብዙ ገንዘብ የሚሰጡ ብቻ ምድር ላይ የተመቸ ኑሮ የሚያኖር አናት ይዘው ይመጣሉ ይባላል፡፡
ወዳጄ፤ በነዚህ መስመሮች መሃል ምድር ላይ ብዙዎቹ ጥቂቶች ሰርተው በሚጭኑባቸው ሃሳብ፣ ህግና ስርዓት ይተዳደራሉ፡፡ ብዙሃኑ በሚከፍሉት ግብር ጥቂቶቹ ይወስናሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሚጭሩት ጦርነት ብዙኃኑ ይማገዳሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሚፈጥሩት የስራ ዕድል ብዙኃኑ ለዳቦ ይናከሳሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሚያወሩላቸው ተረት፣ በሚከውኑላቸው ድራማ፣ በሚያዜሙላቸው ዘፈንና ቀረርቶዎች ብዙኃኑ ይታደማሉ፣ ይጨፍራሉ … የሚል ይነበባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጥቂት ባለ ገንዘቦች ብዘኃኑን አስረው ጠፍረው እያረሱበት ነው ለማለት ይመስላል፡፡
“ሰው ነፃ ሆኖ ቢወለድም ባለበት ቦታ ሁሉ እንደታሰረ ነው፡፡ (Man is born free but every where he is in chain) የሚለን ጂን ጃኩዊስ ሩሶ ነው፡፡
“ማዕከላዊ ተዘጋ” አሉ? …
እሰይ!!
ሠላም!!  

Read 3444 times