Saturday, 21 April 2012 16:53

በውበት የደመቁት የበድሉ ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

ግጥሞች በውበት ፏፏቴ ዜማ … በቃላት ጡንቻ … በሀሣብ ነበልባል … የተነከሩ ቀለማማ ናቸው፡፡ ታዲያ ሰው ሲገጥማቸው፣ ቀን ሲቀናቸው ነው፡፡ አለበለዚያ ድንኳናቸው በጭጋግ ጓዳቸው በፍዘት ይዳምናል፡፡ የነፍስ በር የማያንኳኩ የስሜት መሸንቆሪያ የሌላቸው ዱልዱም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ገጣሚዎችም አንዱ ላይ ብርቱ፣ አንዱ ላይ ቀሽም ሆነው ይገኛሉ፡፡ ካርሊሌ በሀሣብ ልዕቀት፣ አላንፖ በውበት፣ ማቲው አርኖልድ በትርጓሜ ዕጣ እንደወደቀላቸው ማለቴ ነው፡፡ እኛ ሀገርም በሀሣብ ልቀው፣ በቋንቋ የሳሉ፤ በውበት ደምቀው፣ ድድርነት የሸሻቸው አሉ፡፡ ቀንቶአቸው ሁለቱንና ሦስቱን ባንድ የጨበጡ፣ ባለ ተቀብዖዎችም አይታጡም!

የዛሬ ዳሰሳዬ መነሻ በድሉ ዋቅጅራም ግሩም የሚያሠኝ የቃላት አጠቃቀምና መሳጭ የሀሣብ ከፍታ ያለው ገጣሚ ነው፡፡ በ”ፍካት ናፋቂዎች” ነፍሳችንን አማሥሎ፣ ልባችንን አስደንሶ፣ አሥቆ አሥለቅሶ፣ ትዝታውን በድንኳናችን አስቀምጧል፤ በማይረሣ ዜማ!

የአሁኑ የበድሉ መጽሐፍ “እውነት ማለት የኔ ልጅ” 56 ግጥሞችን የያዘ ሲሆን፣ 31 ያህል ግጥሞቹ በእንስት ፆታ ወይም ለእንስት የተፃፈ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን ፍቅር ብቻ አይደለም፡፡ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ ማህበራዊ ጥበባዊና ሌላም ሌላም፡፡ በሴት ፆታ መፃፉ ግን ሁላችንም ለሴት ቅርብ ስለሆንን ይሆን ወይስ ወደ ግሪኩ ዘመን ሄዶ? አላውቅም!

የአሁኑ የበድሉ ግጥሞች ሲኒክስ የሚባለውንና በግሪክ ፈላስፎች የተወለደው፣ ኋላም በሥነ ጽሑፉ አለም ያደገውን አመለካከት የሚያንፀባርቁ ይመሥላል፡፡ አእምሮ ፈቃድና አመክንዮ፣ መንጋው እጅ ከሰጠለት አስተሳሰብና ስግደት ከፍ ብሎ እንዲገዛ የሚፈቅድ የመሮጫ መም ነው፡፡ ለምሳሌ የሳሙኤል በልተር “Way of All flesh” እና የሶመርሴት “Of human bondage” በዚህ ይታቀፋሉ፡፡

የበድሉ ግጥሞችም እንዲህ ነው ሣቃቸው፡፡ እንጉርጉሮዋቸውም!

የመድበሉ ርዕስ ከሆነው “እውነት ማለት የእኔ ልጅ” ጥቂት ስንኞች ልምዘዝ፡-

የኔ ልጅ!

እውነትሽ ብርሃን ሲከላው፣ ጊዜና ትውልድ ሲከዱት፣

ለዘመኑ ኩነኔ ይሆናል፣ በንስሀ አያጸዱት፡፡

በላይ ዘለቀ ሀቅ አንቆት ነው፤ እንቢ ለእውነቴ እንዳለ፣

ቀንዲሉን በልቡ ይዞ፣ ውስጡ እንደተቃጠለ፣

ጀግናው ሽፍታ ተብሎ፣ አደባባይ የተሰቀለ፣

አሁንም በአንድ የግጥም ተመራማሪ አጠራር፣ ከዚሁ ግጥም ሁለት “አረፍተ ስንኞች” ልዝገን፡-

የኔ ልጅ!

በጊዜ ስግደት እንዳይመስልሽ፣ ባደባባይ ጭበጨባ፣

በሚቆምልሽ ህይወት፣ በሚነፋልሽ ጥሩንባ፤

መኖርሽ ትርጉም የሚያገኝ፣ እውነትሽ የሚለካ፡፡

በህዝብ ልብ ያልሠረፀ ገድል፣ ሀገር ያልበቀለበት እውነት፤

ሸራ ወጥረው ቢነድፉት

በድንጋይ በወርቅ ቢቀርፁት፤

ጊዜ ጠብቆ ይነሳል፤

ቀኑ ሲነጋ ይፈርሳል፡፡

ገፀ ባህሪው እውነትን አይደለም የሚነግራት፡፡ የእውነትን መንገዶችን ለማግኘት ከሕይወት ፍተሻ ያገኘውን ሀቅ፣ ከአሳሳች እውነቶች ነጥላ እንድታይ አይኖችዋን ሊያበራ ይታገላል፡፡ እውነት ያምታታል፣ በድምፅ ብልጫ ያሣሥታል ይላታል፡፡ አንዳንዴ እውነት እነደ አትናቴዎስ ብቻውን ሊቆም እንደሚችል ያወጋታል፡፡ የጥሩንባ ጩኸት፤ የቡድን ጋጋታ ያለመሆኑን! የእውነት ነገር ያ ነው!

በድሉ በእንስት ፆታ የፃፋቸው ግጥሞች ብዙ ናቸው ብለናል፡፡ የፍቅር ጉዳይም እንደዚሁም ፍም ነው! የላቀ ጣዕመ ዜማ የሚረግጥ ፏፏቴ፣ የማይዘንብ ደመና ነው፡፡ ወርቅ ይፈለቀቃል፣ ሣቅ ይፈነከታል፣ እምባ ይፈተላል፡፡ ዝምታ ይዳወራል! ፍቅር ውስጥ መሆን ሁሉን ነገር ውብ ያደርገዋል! … የወደዱዋትም የምድር ሁሉ ድንቅ  ናት! እንዳሉት ነው ሰውየው!

በአንዱ ግጥሙ የሕሊና ጅራፍ ጩኸት ይሰማናል - “ባክሽ ሴጣን ሁኚ!” ይሰኛል፡፡

ባክሽ ሴጣን ሁኚ፣

ደስታ የተለየው፣

ጨቅጫቃ ነዝናዛ፤

ለአያያዝ አይመች፣ ወልጋዳ ጠምዛዛ፣

አይመች ለፍቅር፣ እሾህ ቀናተኛ፣

ትህትና ያልተጠጋው፣ ለካፊ መገኛ፡፡

ባክሽ ሴጣን ሁኚ፣

ባክሽ ሲዖል ሁኚ፣

ነፍሴን አንገብግቢያት፣

አቃጥያት፣  ጥበሻት፡፡

መልአክ ከሆንሽማ፣

ችሮታሽ - ንፍገቴን፣

ሳቅሽ - ጭቅጭቄን፣

ፍቅርሽ - ጥላቻዬን፣

እምነትሽ - ዝሙቴን፣

ያሳብቅብኛል፤

ባክሽ ሴጣን ሁኚ፣ ለኔ እሱ ይሻለኛል፡፡

በራሱ ላይ ፍም መከመር የሚባለው፣ በጐነት የቀጣው ሰው ስቃይና ኑዛዜ ነው፡፡ ንቁ ሕሊና፣ ተፀፃች ልብ ያለው ሰው ነው በግጥሙ ውስጥ የሚታየው! በእርግብነትዋ ቀጥታዋለች፡፡ እባብ ሆና ራስ ራሷን ቢላት ኩነኔውን ትጋራው ነበር፡፡ ግና እርሷ ፀድቃ እርሱን ኮነነችው! ዋ!

“በይ ተረት ንገሪኝ” የሚለው ግጥም ሀሣቡ ብቻ አይደለም - ቋንቋው ድንቅ ነው፡፡ ግጥም ደግሞ ያለ ጥሩ ቋንቋ ሙት ነው፡፡ ምናልባትም የሮማንቲስቲዝም ሰዎች እነ ወርድስዎርዝ መጥተው፣ ግጥም ሌላው የሥነ ጽሑፍ ዘውግ የሚጠቀምበትንም ቋንቋ መጠቀም ይችላል ብለው ፉርሽ ባያደርጉት፣ ግጥም የተለየና የተመረጠ ቋንቋ ያስፈልገዋል የሚለው መርህ እስከኛ ዘመን በዘለቀ ነበር፡፡ ያም ቢሆን በድሉ አምልጧል፡፡

ደመና ሆድ ብሶት በምሬት ሲያካፋ፣

ጉም ካመሻሽ ጀምበር፣ በፍቅር ሲላፋ፣

እንዲህ አመሻሽ ላይ፤

ይከፋዋል ነፍሴ፤ ሀዘን ያነጉታል፤

ይሸፍታል ልቤ፣ ሁዋሊት ይጐተታል … ይላል!

ከልብ ላይ መብረቅ ብልጭ ይላል፡፡ ብርርር በል፣ በል ያሠኛል፡፡ ግጥም እንዲህ በቃላት አብዶ ጨርቅ ሲያስጥል ደስ ይላል፡፡

ይሸፍታል ልቤ፣

ከከተማ ግዞት፣ ትርምስ አምልጦ፣

ጉም ከዋጣት ጐጆ፣ ደጃፍ ተቀምጦ፣

ተረት ያዳምጣል፡፡

ገፀ ባህሪው ራሱም ተረት ነው፡፡ የቃላቱ ውበት ግን አሪፍ ነው፡፡ በጣም! “አንተንስ እኔን አያርግህ” የሚለው ግጥም አሁንም ብዙሀኑን የሚቃወም ነው፡፡ እዚህ አገር ከብዙሃኑ ጋር ከመሆን እዚያ ዛፍ ላይ መሆን ይሻላል ብሎ ያምናል፡፡ ገፀ ባህሪው ደግሞ “አትሳሳት ምቾቱ ሙሉ አይደለም!” የሚል ሙግት አለው፡፡ ግጥሙ ፀፀት ቁዘማ፣ እህህህ - ነው!  እንዲህ ይላል፡-

አመትባል እየቆጠርኩ፣ ምልክልህ ገንዘብ፤

ችግር የታከተው ልብህ፣ ጐራውን ጥሎ ቢሰለብ፣

እሱን ባረገኝ አልክ አሉኝ፣

እኔን፣

በተስፋው ቀብር ቤት ነዋሪ፣ የምኞቱን እረኛ

ተቀባይ የሌለው ዘፋኝ፣ የሰው መሀሉን ብቸኛ፤

እኔን፡፡

ባይተዋርነትን እንዴት አድርጐ እንደገለጠው አያችሁ? … የገጣሚ ተዓምር ይሄ ነው -ተቀባይ የሌለው ዘፋኝ! እንደምድረበዳው ድምፅ! … ውስጡ ሲፈተሽ ብዙ ሕመም፣ ብዙ ሥቃይ፣ ብዙ ትርጉም! … የሀሣብ ክብደትም አለው፡፡ በተስፋው ቀብር ቤት የሚኖርስ? ምኞቱ እረኛ …ምኞቱን የሚበላው ተኩላስ ብዛት? … በተስፋ ቀብር ቤት መኖር?? … ይገርማል! … በድሉ ቋንቋም ሀሣብም ታድሏል!

የበድሉ “እውነት ማለት የኔ ልጅ!” አንዳንድ እንደርሱ ግጥም “እኔን!” የሚያሠኙ ጥቂት ስብራቶች አሉበት፡፡ አንዳንድ ቦታ ዜማ ያለአግባብ ሲሠበር እየታየ አልተቃናም፡፡

አንድ ሁለት ግጥሞች ምነው ባልገቡ ብዬ ከንፈሬን ነክሻለሁ፡፡ ገዛኸኝ ይህንን ማየት ነበረበት! ዜማዎቹ አንከስ የሚሉበት ቦታ አለ፡፡ ግን ሞራ እንደዋጠው ኩላሊት ብዙ ውበቶች ሸፍነውታል፡፡ ይሁን እንጂ በድሉን የመሰለ ሁለንተናዊ ምልዐት ያለው ገጣሚ ትንኝም እንዳያርፍበት ልንጠነቀቅ ይገባል! ሀውልት ሆኖ ትውልዳችንን በሙሉ ብቃት ሊወከል የሚችል ትልቅ ገጣሚ ነውና! የደበበ ሰይፉንና የዮሐንስ አድማሱን ነፍስና ግጥም የያዘው “ይድረስ ለባለቅኔው ደበበ” የሚለው ብቻውን በጥሞና ሲመረመር ብዙ የሚያስብል ነው፡፡ እኔ ግን አሁን ስሜቴን እንጂ ውስጡን የማየት ጊዜው የለኝምና አልፌዋለሁ፡፡

አቦ ሀበሻ ያውቅበታል፣ ጨዋታው ፈረስ፣ … ይበልጥ ሲኒክሳዊ ነው፡፡ የተሸነፈ እውነት! … ግን ሲኒክሳዊያን የማይቀበሉት፡፡ ሎጂክ የሚያሸንፈው ሕሊና የሚቃወመው! የመንገድ ላይ ቀላህ! … የታሪክን መፋለስ አንዳንዴም ጀግና ሆኖ ያለ ሀውልት መቅረት፣ ያለመዘከርን ያሣያልና ጀግንነትንም መንጋ አይበይነውም! መታሰቢያ አያፀናውም፤ ቀን ሲዞር ይዞራልና! የሚል ቀጭን ድምፅ ውስጡ አለ፡፡ ሁሉም በእሣት ይቃጠላል፤ ግን ጀግናን የሚገድል፣ አድርባይንም የሚያስወግድ፣ ምናምንቴውንም የሚነቅለው ያው አንዱ ጥይት ነው! ቀላህ ደግሞ መርዝ አቀባይ … የሞት ድግስ ከረጢት ነው፡፡

የበድሉን ግጥሞች ለመተንተን ሠፊ ናቸው፡፡ ድድር! ክምር! አንዱ ብዙ ነው! ግጥም ማለት ይኸው ነው፤ ባንድ ኖት ብዙ ምንዛሪ! ቦታ አይበቃም፡፡

ቢሆንም አንድ ግጥም እንዲሁ ልዘርጋና ሥዕሉን እንየው! ለኔ ግን የገደል ማሚቱ ለቅቆብኛል! … የሚደጋገም ድምፅ፣ ያለፈ ምኞት ግን ከልብ አልወጣ ያለ! … የሚጮህ ምኞት! … ግን የማይገኝ! “ለዛች ለተሰዋች ቀን” ይላል፡-

በወጣትነት ገሞራ፣ አንቺን በማግኘት ሰቀቀን፣

እንደ አንድ አመት ረዝማ፣ ለተሰዋች ለዛች ቀን፣

ይኸው እስከ ዛሬ፤ ቀናት እሰዋለሁ፤

ብትመጣ ኖሮ፤

ብትመጣ ኖሮ፤

ብትመጣ ኖሮ - እያልኩ አስባለሁ!

የዚህ ገጣሚ ግጥሞች ቁርጥ፤ ክትፎ፤ ቀይ ወጥ፣ አልጫ፣ ቅቅል፣ በያይነቱ ናቸው፡፡ ከፍታቸው የላቀ ነው! የተሣለ ቢላዋ፣ የሚያስተውል ልቦና፣ የሚያጣጥም ነፍስ ግን ይፈልጋሉ! አንድ መጽሐፍ ውስጥ ሊኖሩ ከሚገባቸው የላቁ ግጥሞች የላቀ ይዘዋል!

ብትመጣ ኖሮን እንቀጥል፡-

ብትመጣ ኖሮ፣

እራት ሳንበላ፣ ወይን ሳንጐነጭ፣

ተቃቅፈን ሳንደንስ፣ ብርጭቆ ሳይጋጭ፣

ሳይጠፋ ሙዚቃው የደነስንበቱ፤

ሳይጨልም ፋኖሱ የደመቅንበቱ፤

ባልነጋ ሌሊቱ

እያልኩ እያሰብኩኝ፣ በሁዋሊት ምናኔ

የዛሬ ሃያ ዓመት ለተሰዋች ቀኔ፣

ሁሌ ይቆጨኛል፣ ዛሬም ያለኝን ቀን እሰዋልሻለሁ፣

ብትመጣ ኖሮ፤

ብትመጣ ኖሮ፤

ብትመጣ ኖሮ፤ … እያልኩ እመኛለሁ፡፡

አ-ቤ-ት! … እውነትም ብትመጣ ኖሮ! እንኳን አልመጣች፤ ብትመጣ ኖሮ የዚህ አይነት መሳሳብ … የዚህ አይነት ምጥ … ከየት ይመጣል! እንኳን ቀረች!

 

 

 

Read 7490 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:56