Saturday, 20 January 2018 12:11

በኦነግ ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ወጣቶችም ይፈቱ!

Written by  ቡልቻ ደመቅሳ
Rate this item
(1 Vote)

   ኦነግ “ኦሮሞ ነፃ መውጣት አለበት” ብሎ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ሲታገል፣ የረገፉና የታሰሩ ወጣቶች ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም እስከ አሁን በእስር ቤት የሚማቅቁ ቁጥራቸው አያሌ ነው፡፡ ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች፣ የኦሮሞ ነፃ መውጣት ትክክለኛ ጥያቄ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ ኦነግና ህውሓት በአንድ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ይመሩ ስለነበር፣ ካርቱም ላይ አብረው ቡና ይጠጡ ነበር፡፡ የደርግን ሀሳብና እቅድ በቅርብ ያውቁ ስለነበርም፣ ትግሉ ቶሎ አይጠናቀቅም በማለት አሜሪካኖች እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ከእነሱ ጋር መፃፃፍ ጀመሩ፡፡ አሜሪካኖቹ ድሮውንም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መቆራረጥን ስለማይሹ ሳይወዱ በግድ አዎንታዊ ምላሽ ለህወሓት ሰጡ፡፡ ከዚያም ታዋቂ ሰዎችና የራሳቸውን ደጋፊዎች በመጋበዝ  ኢህአዴግን በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡
አሜሪካኖቹ የኢትዮጵያን ጉዳይ በጥልቀት ይከታተሉ ስለነበር፣ የኦሮሞ ብዛትና የታገለበትን እድሜ ዘመን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኦነግ በስብሰባው ላይ እንዲጋበዝ አደረጉ፡፡ ኦነጎችም መገንጠል የሚባለውን ሃሳብ ለጊዜው በጉያቸው ሸጉጠው ወደ ስብሰባው መጡ፡፡ ሆኖም ነገሩ ሁሉ በደንብ ስላልታሰበበት ኢህአዴግና ኦነግ ሳይስማሙ ቀርተው ኦነግ ከሃገር ተባረረ፡፡ ኢህአዴግም አምባገነንነቱን አፋፋመ፡፡ ኦነግም የጦርነቱን ጉዳይ ለመቀጠል ወደ ኤርትራ ተጠጋ፡፡ ኢህአዴግ በሃይል ህዝቡን ለመጫን ቢሞክርም ህዝቡ ግን አልገዛም አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ደርግን ማሸነፍ የቻለው የተባበረ የጦር ኃይሎች ድጋፍ ታክሎበት ነው፡፡)
እንግዲህ አሁን የፖለቲካ ጫና በመብዛቱ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስት፣ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን እፈታለሁ ብሎ ቃል ገብቷል፡፡ የተወሰኑትንም ከሰሞኑ መፍታት ጀምሯል፡፡ ድሮውንስ ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችንና ፖለቲከኞችን “ለምን ከእኔ የተለየ የፖለቲካ ሃሳብ አራመድክ” ብሎ ማሰር ተገቢ ነበርን? ለማንኛውም ከእስር የመፍታት እርምጃው  መልካም ነው፡፡ የቀሩትም ፖለቲከኞች መፈታት አለባቸው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ ህሊና ይቀበለዋል ብዬ የማምነው አንድ ነገር አለ፡፡ አያሌ የኦሮሞ ወጣቶች በኦነግ ምክንያት ታስረዋል፡፡ ቁጥራቸውም በጣም ብዙ ነው፡፡ የታሰሩት በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ነው፡፡  ምርጫ ማለት የህዝቡን ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ስለዚህ በኦነግ ምክንያት የታሰሩ ወጣቶችም  እንደ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ይገባል፡፡ መንግስት ይህንን ጉዳይ በጥልቀት ያስብበት ዘንድም እንደ አንድ አገሩን የሚወድ ዜጋ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡  

Read 2584 times