Saturday, 20 January 2018 12:09

የተፈናቃዮቹ አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ - በራሳቸው አንደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

• ከምንረዳ ይልቅ ሰርተን መኖር የምንችልበትን ሁኔታ ይመቻችልን
         • ከ20 ዓመት በላይ ለፍቼ ያፈራሁት ሀብት ከእጄ ወጥቷል
         • እህል የጫነ መኪና ነው በናፍቆት እየተጠባበቅን ያለነው
         • በአንድ ጀምበር ወደ ራሽን ጠባቂነት ተለውጫለሁ

    በኦሮሚያና በሶማሌ ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ደም አፋሳሽ ግጭት ተከትሎ፣ ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ዜጎች መፈናቀላቸው አይዘነጋም፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከጅግጅጋና አካባቢው ከ7 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉ ያስታወቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ለእነዚህ ተፈናቃዮች በተለያዩ መርሃ ግብሮች እርዳታ እያሰባሰበ ይገኛል፡፡ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ከሰሞኑም አዋሽ ወይን አክሲዮን ማህበር በግጭቱ ተፈናቅለው፣ በአርሲ ሮቤ ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ከ450 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ያዘጋጀውን 4መቶ ኩንታል በቆሎ በእርዳታ የለገሰ ሲሆን በዚህ የእርዳታ አሰጣጥ ስነ ስርአት ላይ የተገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ተፈናቃዮችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ ውድ አንባቢያን፡- በዚህ ዘገባ ማካተት የቻልነው ከጅግጅጋ ተፈናቅለው፣ በአርሲ ሮቤ ከተጠለሉት ዜጎች ጥቂቶቹን ብቻ ሲሆን ወደፊት በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡

   
          “እኔም ቤተሰቤም ባዶአችንን ቀርተን የሰው እጅ ጠባቂ ሆነናል”
              አብዱልሃኪም መሃመድ፤ ዕድሜ 38

   ወደ ሶማሌ ክልል የሄድኩት በ1998 ዓ.ም ነው። 10ኛ ክፍልን እንደጨረስኩ ነው የተሻለ ስራ ፍለጋ ወደ ጅግጅጋ የሄድኩት፡፡ እዚያ እንደሄድኩ ኮሌጅ ገብቼ እየሰራሁ፣ በምህንድስና ዘርፍ ተማርኩኝ። ትምህርቴን እንደጨረስኩ በኮንስትራክሽን መያ ተሰማርቼ፣ ከጉልበት ስራ ጀምሮ በመስራት፣ የራሴን የኮንስትራክሽን ድርጅት አቋቁሜ፣ ህንፃዎችን ኮንትራት እየወሰድኩ እሰራ ነበር፡፡ በአብዛኛው የግለሰብ መኖሪያ ቤት ነበር የምሰራው፡፡ በስሬ ከ20 የማያንሱ ጊዜያዊና ቋሚ ሰራተኞች ነበሩ፡፡ ወደ እዚህ ካምፕ  አብረውኝ የመጡ ሰራተኞችም አሉ፡፡
ምን ያህል ካፒታል ነበረህ?
አንድ ቪላ ቤት ስንሰራ በትንሹ 1.5 ሚሊዮን ብር ነበር ኮንትራት የምንይዘው፡፡ በአብዛኛው ገንዘቡን ቶሎ ቶሎ ስለምንጠቀምበት፣ ባንክ ቤት የማስቀመጥ እድሉ እምብዛም ነበር፡፡ ያም ሆኖ በሚገባ ሁለት ልጆቼንና ቤተሰቤን ማስተዳደር የሚችል ሀብት ነበረኝ፡፡ የራሴ ቦታና መኖሪያ ቤትም ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ አለኝ፡፡ በታጠቁ ሰዎች መንገድ ላይ ተይዤ፣ከከተማዋ እስከተባረርኩ ጊዜ ድረስ 4 ሳይቶች ላይ የኮንስትራክሽን ስራዎችን እያከናወንኩ ነበር፡፡
እንዴት ባለ ሁኔታ ነው የተፈናቀልከው?


                  “ከ40 ዓመት በላይ ጅግጅጋ ኖሬያለሁ”
                     አቶ ዲታ ከድር፤ ዕድሜ 66


     ጅግጅጋ ከ40 ዓመት በላይ ኖሬያለሁ። ከወጣትነቴ ጀምሮ በግንበኛነትና በአናጢነት እየሰራሁ፣ መሬትም ቤትም ገዝቼያለሁ፡፡ የራሴ መኖሪያ ቤት አለኝ፡፡ እዚያው አግብቼ 11 ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ 5ቱ ሞተውብኛል፤ 6ቱ በህይወት አሉ። ይኸው ከኔው ጋር ተፈናቅለው፣ እዚህ ሮቤ ከተማ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ አሁን አንዷ ልጄ ከከተማዋ በተባረርንበት ወቅት ሌሊት በመኪና ስንጓዝ፣ አደጋ ደርሶብን፣ እግሯ ተሰብሯል (ከእንባቸው ጋር እየታገሉ)፡፡ ይኸው ከችግር ጋር እሷን በመንከባከብ ላይ ነው ያለነው፡፡ አሁን ድረስ በአንድ ጎኗ  እንደተኛች ነው ያለችው፡፡ በቂ ምግብ የለንም፡፡ ስለዚህ ማገገም አልቻለችም፡፡ የሚመጣልን ምግብ አንዳንዴ ይዘገያል፡፡ ያለ ምግብ የምንውልበት ቀን አለ፡፡ በዚያ ላይ ለአንድ ቤተሰብ ለወር ተብሎ የሚመጣው ከ15 ኪሎ አይበልጥም፡፡
ልጆቼ አትክልት፣ ወተት፣ ሩዝ እየበሉ ነው ያደጉት፡፡ ዛሬ ይሄ ሁሉ የለም፡፡ ት/ቤት እንኳ ግቡ ብላቸው ደስተኛ አልሆኑም፡፡ እኔም ሆነ ልጆቼ ከዕለት ገበታችን ስጋ አይጠፋም ነበር፤ ዛሬ ስጋ ናፍቆናል፡፡ እንዲሁ ከተማ ውስጥ በአይናችን እናየዋለን እንጂ ገንዘብ ኖሮን ገዝተን መመገብ አልቻልንም፡፡
እርስዎ እዚህ  ዘመድ የለዎትም?
የትውልድ ቦታዬ እዚህ (አርሲ ሮቤ) ቢሆንም ሙሉ ቤተሰቤ እኔን ተከትሎ ሶማሌ ክልል ነበር የሚኖረው፡፡ ሌሎቹም በየቦታው ተበትነዋል፡፡ አሁን ምን ላይ እንዳለሁ እንኳን አያውቁም፡፡ እኔ ጅግጅጋ የሄድኩበት አጋጣሚ ብሄራዊ ውትድርና ነው፡፡ ሃገሬን በውትድርና አገልግዬ ጦሩ ሲበተን፣ እኔም ወደ መደበኛ ኑሮዬ ተመለስኩ፡፡ እዚያው አግብቼ ነው ኑሮዬን የመሰረትኩት፡፡
ለወደፊት ምን ያስባሉ?
እኔ እድሜዬ ቢገፋም ዛሬም በሙያዬ ሰርቼ ማደር እችላለሁ፡፡ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ እርዳታ እየተበጣጠሰ ከሚሰጠን ኑሮአችንን የምናቋቁምበት መንገድ እንዲመቻችልን ነው የምንፈልገው፡፡ እኔ ጅግጅጋ ንብረት ቢኖረኝም ብዙ የመመለስ ፍላጎት የለኝም፡፡ ሞራሌ ተነክቷል፡፡ ትናንት ከአካባቢው ስንፈናቀል ያጋጠመኝ ነገር ከአይምሮዬ አይወጣም።


--------------------


              “2 ሚ. ብር የነበረኝ ሰው፣ ዛሬ እርዳታ ጠባቂ ሆኛለሁ”
                  አቶ ታደሰ ጌታቸው፤ዕድሜ 34

    ከጅጅጋ ከተማ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም ነው የተፈናቀልኩት፡፡ በመጀመሪያ ሃረር ቆይተን፣ ከሃረር ወደ አዳማ መጥተን፣ ከአዳማ ወደ አሰላ፣ ከዚያም ወደ ትውልድ ቦታችን አርሲ ሮቤ ልንመጣ ችለናል፡፡
እንዴት ባለ ሁኔታ ነው ከጅጅጋ የተፈናቀላችሁት?
በመጀመሪያ የድንበር ግጭት አለ የሚባል ነገር እሰማ ነበር፡፡ እኔ ብዙም ሚዲያ አልከታተለም፡፡ ስራ ይበዛብኛል፡፡ እንዲሁ በወሬ ነው ግጭት እንዳለ ራሱ የሰማሁት፡፡ መስከረም 3 ቀን ከስራ ቦታ ወደ መኖሪያ ቤቴ ምሳ ለመብላት ስሄድ፣ መንገድ ላይ አስቁመውኝ፣ ብሄሬን ጠየቁኝ፡- ኦሮሞ መሆኔን ስነግራቸው፣ ና ብለው ይዘውኝ፣ ተሳቢ መኪና ላይ ጫኑኝ፡፡ ከዚያ ወደ ካምፕ ነው የወሰዱን፡፡ በወቅቱ ቤተሰቦቼን አላገኘኋቸውም ነበር፡፡ ሁለት ህፃናት ልጆች አሉኝ፡፡ በኋላ ነው እነሱም በሌላ አቅጣጫ መጥተው ሃረር ላይ የተገናኘነው፡፡ አሁን ሳስበው ነገሩ ሁሉ ይዘገንነኛል፡፡ በመሃል ቤተሰቦቼን ባጣስ ኖሮ፣ ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ እስካሁንም ከቅዥቱ አልወጣሁም፡፡
ጅጅጋ  እያለህ በምን ነበር የምትተዳደረው?
በሙያዬ መሃንዲስ ነኝ፡፡ የተለያዩ ህንፃዎችን መኖርያ ቤቶችን እየተኮናተርኩ እገነባለሁ። ወደ 40 ገደማ ሠራተኞች ከስሬ አስተዳድር ነበር። አሁን ያ ሁሉ ቀርቶ ባዶ እጄን ቀርቻለሁ፡፡ ልጆቼ በቅንጦት ያደጉ ነበሩ፡፡ ዛሬ ይኸው እንደምታያቸው አመድ በላያቸው ላይ የተነሰነሰ መስለው ጠውልገዋል፡፡ ሃብት የነበረኝ ሰው ነበርኩ፡፡ 2 ሚሊዮን ብር ገደማ ነበር የማንቀሳቅሰው፡፡ ዛሬ ግን የብር መልኩም ጠፍቶብኛል፡፡ ከተፈናቀልኩ ጀምሮ ብር የሚባል ነበር በእጅ ነክቼ አላውቅም፡፡ በመንግስትና በህብረተሰቡ እርዳታ ነው ያለነው፡፡ እሱም ቢሆን በአግባቡ አይደርሰንም፡፡ አሁን እንኳ አንተን ሳናግርህ እኔም ቤተሰቤም ቁርስ አልበላንም። ገና ከመኪና ተራግፎ የሚመጣንን በቆሎ ነው እየተጠባበቅን ያለነው፡፡ ይሄን ማሰብ አንዳንዴ እንደ እብድ ያደርገኛል፡፡ ልጆቼ በቆሎ በልተው  አያውቁም፡፡ ያደጉት አማርጠው በልተው፣ ተቀማጥለው ነው፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤት ነው ሲማሩ የነበረው፡፡ እዚህ የመንግስት ት/ቤት በመንግስት እርዳታ ባስገባቸውም፣ በአማርኛ ቋንቋ ስለነበር የሚማሩት፣ እዚህ ያለውን መልመድ አልቻሉም፡፡
በጅጅጋ ምን ያህል ጊዜ ኖረሃል?
አባቴ እዚያ ይኖር ነበር፡፡ እኔ እዚህ አርሲ ሮቤ ብወለድም፣ በልጅነቴ ሄጄ፣ እዚያ ነው አባቴ ጋር ያደግሁትና የተማርኩት፡፡ እዚያው ነው አግብቼ ልጆች የወለድኩትም፡፡
አሁን የሚደረግላችሁ ድጋፍ ምን ይመስላል?
ስንመጣ ህብረተሰቡ በሰፊው እጁን ዘርግቶ ነው የተቀበለን፡፡ ብዙ እንክብካቤም አድርጎልናል። ግን እየቆየ ሲሄድ ድጋፉ እየተቀዛቀዘ፣ ዛሬ ህይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ እህል የጫነ መኪና ነው በናፍቆት እየተጠባበቅን ያለነው፡፡ እኛ ሰርተን መኖር የምናውቅ ሰዎች ነን፤ እባካችሁ ስንዴ ከምታመጡልን ስራ ስጡን፣ የምንሰራበትን ሁኔታ አመቻቹልን ብለን እየጠየቅን ነው፡፡ ተደራጅተንም ቢሆን እንስራ ብለን ጠይቀናል፡፡
ወደ ጅጅጋ ለመመለስ አላሰብክም?
አገር ሰላም ከሆነ እንመለሳለን ብለን ነበር፤ ግን ዛሬም ሁኔታው አስፈሪ ነው፡፡   

------------------


                 “ሰርቶ ከመብላት ወደ ራሽን ጠባቂነት ተለውጫለሁ”
                     ሙክታር ኢማን፤ዕድሜ 33


      ወደ ጅግጅጋ የሄድኩት ስራ ፍለጋ ነበር፡፡ ገና በ17 ዓመቴ ነበር ወደዚያ የሄድኩት፡፡ ከቀን ስራ ጀምሮ የተለያዩ ሙያዎችን እየሰራሁ፣ አሁን ግምበኛ ሆኛለሁ፡፡ በቀን 300 ብር ይከፈለኛል፡፡ ትዳር መስርቼም  የ3 አመት ልጅ አለችኝ፡፡
የተፈናቀልከው እንዴት ነበር?
እኔ ከቤቴ ለስራ ነበር የወጣሁት፡፡ መንገድ ላይ ሰዎች እርስ በእርስ ይባረራሉ፡፡ ወደ እኔም የተወሰኑ ወጣቶች እየሮጡ መጡ፡፡ ከዚያ ሊደበድቡኝ እንደሆነ አውቄ፣ በሩጫ አምልጬ፣ ወደ ተሰባሰቡ ሰዎች መሃል ገባሁ፡፡ እነዚያ ሰዎች ግማሾቹ ተደብድበው እንዲሰበሰቡ የተደረገ ነበሩ፡፡ በኋላ በመኪና ተጭነን፣ ሁላችንም ወደ ሃረር መጣን። ባለቤቴና ልጄም እንዳጋጣሚ እኔ የተጫንኩበት መኪና ውስጥ ነበሩ፡፡
አሁን ያለህበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
ያው ሰርቶ ከመብላት ወደ ራሽን ጠባቂነት ተለውጬ፣ የሰው እጅ ተጠባባቂ ሆኜ እየኖርኩ ነው። እኔ በጉልበቴ የፈለግሁትን እየሰራሁ፣ በላቤ የምኖር ዜጋ ነበርኩ፡፡ የሰው እጅ ጠባቂነትን የምፀየፍ ሰው ነበርኩ፡፡ ግን አጋጣሚውን ምን ላደርግ እችላለሁ? በቃ የእኔና የቤተሰቤ ህይወት ወደ ማልፈልገው ነገር ነው ያመራው፡፡ የሚያሳዝነው ይሄ ሁኔታ ሲፈጠር፣ እኔ ግጭት እንኳ መኖሩን አላውቅም ነበር፡፡ ስራ ስራዬን ብቻ የምል ሰው ነኝ፡፡ ከአካባቢዬ ሰዎች ጋርም ጥሩ ቀረቤታ ነበረኝ፡፡ እርግጠኛ ነኝ እኔ ላይ በደረሰው ነገር እነሱም ያዝናሉ፡፡
አሁን የሚመጣልንን ስንዴም፣ ዘይትም፣ በቆሎም እየተቀበልን መብላት ብቻ ነው ያለን እድል፤ መምረጥ አንችልም፡፡ ብር በእጃችን ላይ የለም፡፡ እኔ የብር መልኩም ጠፍቶብኛል፡፡ በአንድ ጀምበር ነው ወደ ተረጅነት የተቀየርኩት፤ ያውም በማላውቀው ምክንያት፡፡
ለወደፊት ምን ታስባለህ?
እኔ ወደ ጅግጅጋ የመመለስ ፍላጎት የለኝም። መንግስት ሁኔታውን ካመቻቸልን እዚሁ (አርሲ ሮቤ) መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ተደራጅተንም ቢሆን ለመስራት መንግስትን እየወተወትን ነው፡፡ እነሱም “ጉዳዩን እየተመለከትን ነው፤ ጥቂት ታገሱ” ብለውናል፡፡   


--------------------


               “የ1 ወር ከ15 ቀን አራስ ሆኜ ነው የተፈናቀልኩት”
                  መገርቱ ዩሱፍ፤ ዕድሜ 23


     ጅግጅጋ የሄድኩት በጋብቻ ነው፡፡ ባለቤቴ ጅግጅጋ ይኖር ነበር፡፡ ቤተሰቦቼን ለጋብቻ ለምኖ ተፈቅዶለት ነው አግብቼው ወደ ጅግጅጋ የሄድኩት። ባለቤቴ ነጋዴ ነው፡፡ እኔ አልሰራም፣ ልጄን ነበር የማሳድገው፡፡ ኑሮአችንም ቆንጆ ነበር፡፡
ከጅግጅጋ እንዴት ነው የወጣችሁት?
እኔ በህይወቴ አይቼ የማላውቃቸውን ዘግናኝ ነገሮች ነው ያየሁት፡፡ ብዙ የተደበደቡና የተጎዱ ሰዎችን አይቻለሁ፡፡ ወደኛ የመጡት ድንገት ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን ነው፡፡ ከቤት አስወጡን፤ ከዚያም መኪና ላይ ጫኑንና ወደ ካምፕ ወሰዱን። ካምፕ ውስጥ 3 ቀን ከቆየን በኋላ ወደ ሃረር ተጭነን መጣን። ሃረር ላይ ነው የምንተዋወቅ ሰዎች የተገናኘነው፡፡ እኔ በተፈናቀልኩበት ወቅት ወልጄ፣ ገና የአንድ ወር ከ15 ቀን አራስ ነበርኩ፡፡
አሁን ምን አይነት ድጋፍ እየተደረገላችሁ ነው?
ህብረተሰቡ የአቅሙን እየደገፈን ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ (አርሲ ሮቤ) ብቻ ያለነው ከ4 መቶ በላይ ነን፡፡ የከተማዋ ህዝብ ሁሉንም የመደገፍ አቅም የለውም። የመንግስት እርዳታም እየቆየ ነው የሚመጣው፡፡ ያው በሰው እጅ ነው ያለነው፡፡ ባለቤቴም እኔም ቤት ውስጥ ቁጭ ብለን እርዳታ ነው የምንጠብቀው። ቤቱን መንግስት በነፃ ነው የሰጠን፡፡ ግን ምግቡ ያንሰናል፤ ልጄን ለማጥባት የተለያየ ምግብ መመገብ ቢኖርብኝም በቆሎ ብቻ ነው የምመገበው፡፡ እኔ በፊት የበቆሎ ዱቄትን ለምግብነት አልጠቀምም ነበር፡፡
ዛሬ ግን ችግር የማላውቀውን አስለምዶኛል። ባለቤቴም ተስፋ ቆርጦ የሚያደርገው ጠፍቶት፣ ግራ እንደተጋባ ነው ያለው፡፡ እኔ መንግስት ዝም ብሎ ከሚረዳን ራሳችን ሰርተን መኖር የምንችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን ነው የምፈልገው፡፡ መረዳት አልፈልግም፡፡ መስራት እንችላለን፤ ስራውንም እናውቅበታለን፡፡

Read 1637 times