Saturday, 20 January 2018 11:58

ሊቀ ጳጳሱ እና ከንቲባዋ እርቅ ፈፀሙ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  ለፈረሰው የለገጣፎ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ-ክርስቲያን 3ሺ ካ.ሜ ቦታ ተፈቀደ

      ከ8 ወራት በፊት ህገ ወጥ ግንባታ ነው፣ በሚል በመንግስት ግብረ ኃይል እንዲፈርስ ለተደረገው የለገጣፎ ለገዳዲ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መስሪያ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የተሰጠ ሲሆን፤ በዚሁ ሳቢያ አለመግባባት ውስጥ የቆዩት ሊቀጳጳሱና ከንቲባዋ እርቅ ፈፀሙ፤ ታቦቱም ከነበረበት ፖሊስ ጣቢያ በምዕመናን ታጅቦ ወጥቷል፤ የጥምቀት በዓልም በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል፡፡  
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ስለ ጉዳዩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ ላለፉት 8 ወራት የቤተ ክርስቲያኒቱ መፍረስ ተገቢ አለመሆኑን ለተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ሲያሳስቡ መቆየታቸውንና በመጨረሻም የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በራሳቸው ውሳኔ፣ ከካቢኔ አባሎቻቸው ጋር መክረው፣ በምትኩ 3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
“ከከንቲባዋ ጋር ተነጋግረን እርቅ ፈፅመናል፤” ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ “የተሰጠን ቦታም ለአቅመ ደካሞች የተመቸና ከበፊቱ የተሻለ ነው፤” ብለዋል፡፡ የቀድሞ የቤተክርስቲያኑ ይዞታ 1 ሺህ ካሬ ሜትር ብቻ እንደነበር የጠቆሙት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ “አሁን 3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶናል፣ ከከንቲባዋ ጋር ተነጋግረንም ፍፁም እርቅ አውርደናል፤” ብለዋል፡፡
ረቡዕ ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም፣ ታቦቱ ላለፉት 8 ወራት ከተቀመጠበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኝ ኮንቴነር በማውጣት በምዕመናን ታጅቦ በተፈቀደው ቦታ ላይ ለጊዜው በተሰራው ድንኳን ውስጥ መቀመጡን የጠቆሙት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤በጥምቀት በዓል ላይ የቤተ ክርስቲያኑ ህንፃ የመሠረት ድንጋይ ይጣላል፤ ብለዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያንን አፍርሶ ህዝብን እመራለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው፤” ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የከተማው አስተዳደርና ከንቲባዋ ይሄን ከግምት በማስገባት የተሻለ ቦታ ሰጥተው፣ ችግሩን መፍታታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፤ ብለዋል፡፡ የጥምቀት በዓል በልዩ ሁኔታ በቦታው ላይ እንደሚከበርና ሥነ ሥርዐቱም እስከ እሁድ ድረስ እንደሚዘልቅ የሃገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አስታውቀዋል፡፡  በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለው ለመጡና በለገጣፎ ለሚገኙ 4 አባወራዎች መኖሪያ ቤት ሠርታ ለማቋቋም ቃል መግባቷን ብፁዕነታቸው ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።

Read 6366 times