Saturday, 20 January 2018 11:53

በየዓመቱ 500 ሚ. ብር የሚያወጣ መድሃኒት ይቃጠላል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

 በ11 ሚ. ዶላር ወጪ ስምንት ዘመናዊ የመድሃኒት ማቃጠያ ሥፍራ ሊገነባ ነው
               
   ከተለያዩ የዓለም አገራት በግዥና በእርዳታ ከሚገኙት መድሃኒቶች መካከል 500 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መድሃኒት በየዓመቱ  እንደሚቃጠል ተገለፀ፡፡
የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ የኤጀንሲው የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ ዕቃዎች የጨረታ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ ኢሳ እንደተናገሩት፤ በየቅርንጫፍ መ/ቤቶቹ ያሉት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ከጥቅም ውጪ የሆኑ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶች በየዓመቱ እንዲቃጠሉ ይደረጋል፡፡
መድሃኒቶቹ ከዚህ ቀደም ተለምዶአዊ በሆነ መንገድ ይወገዱ እንደነበር የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ይህ አሠራር የአካባቢ ብክለት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ በመሆኑ ተለምዶአዊውን አሰራር በማስቀረት ዘመናዊ የማቃጠያ ሥፍራዎችን ለመገንባት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በ11 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይገነባሉ የተባሉት የስምንቱ ዘመናዊ የመድሃኒት ማቃጠያ ቦታዎች የቦታ መረጣና የአካባቢ ጥናት ሥራ ተጠናቅቆ ውል መፈረሙን የገለፁት አቶ ሰይፉ፤ እስከ ፊታችን ሰኔ ግንባታው  ተጠናቆ፣ አዲሶቹ ዘመናዊ የማቃጠያ ቦታዎች ሥራ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
መድሃኒቶቹ እንዲቃጠሉና እንዲወገዱ ከሚደረጉባቸው ምክንያቶች መካከል የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ማለፍ፣ ከአንዳንድ የመድሃኒት አቅራቢዎች የሚመጡ መድሃኒቶች የጥራት ችግር መኖርና አዳዲስ ግኝቶች መምጣት (በተለይም ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር የተያያዙ) እንደሆኑ  ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ የጥራት ችግር ያለባቸውን መድሃኒቶች የሚልኩ አቅራቢዎች ምትክ መድሃኒቶችን እንዲተኩ ይደረግና ቀደም ሲል የገባው መድሃኒት ይወገዳል ብለዋል - ዳይሬክተሩ፡፡
 የጤና ተቋማትም በየጊዜው የሚፈልጉትን መድሃኒት መጠን በትክክል ትንበያ የማያቀርቡ በመሆናቸው አንዳንድ ጊዜ መድሃኒቶች ከሚፈለገው መጠን በላይ በመምጣታቸው ሣቢያ ክምችት እንደሚፈጠርና መድሃኒቶቹ ለብልሽት እንደሚዳረጉም አቶ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡
ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የመድሃኒት ፍጆታዎች ከውጪ አገር በሚመጡ መድሃኒቶች የሚሸፈን መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰይፉ፤ እነዚህ መድሃኒቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሚደረገው ሂደት መድሃኒቶቹ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚደርሰውን የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን ያጣሉ፤ ይህም መድሃኒቶቹ ረዘም ያለ የመጠቀሚያ ጊዜ እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መድሀኒቶች የማስወገዱና የማቃጠሉ ሥራ መከናወኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ በጀት ዓመት ይኸው ሥራ በአዲስ የማስወገጃና የማቃጠያ ሥፍራ እንደሚከናወንም ገልፀዋል፡፡ በአገር ውስጥ ለመወገድ የማይችሉ አንዳንድ መድሃኒቶችና ኬሚካሎች እዛው አቅራቢ ድርጅቱ ዘንድ ተመልሰው ሄደው እንደሚወገዱና ብዙውን ጊዜ ግን እነዚህ መድሃኒቶችና ኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሣያልፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በመሆኑ ችግሩ በብዛት እንደማያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡
በታህሳስ ወር 2000 ዓ.ም ሥራውን የጀመረው ኤጀንሲው፤ በወቅቱ 640 ሚሊዮን ብር በጀት የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ15 ቢሊዮን ብር የጤና ግብአት ለማሰራጨት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኤጀንሲው በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች 19 ቅርንጫፎችን ከፍቶ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ኤጀንሲው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ግብአቶች፣ ኤም አርአይ፣ ኤክስሬይ፣ ሲቲ ስካን፣ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ልየታና ህክምና የሚውሉ ማሽኖች፣ የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች፣ ለጨቅላ ህፃናት ህክምና የሚያገለግሉ መሳሪያዎችና የራዲዮግራፊ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ያስገባል፡፡ በቅርቡም በስድስት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ጨረር ህክምና መስጫ ማሽኖችን ገዝቶ፣ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Read 3927 times