Saturday, 20 January 2018 11:42

አዋሽ ወይን ኩባንያ ለተፈናቃዮች እርዳታ ለገሰ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ከተመሰረተ 81 ዓመታት ያስቆጠረው አዋሽ ወይን አክሲዮን ማህበር፣ በቅርቡ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የ40 ቶን (400 ኩንታል) በቆሎና የ100 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል።
ኩባንያው ጥር 6 ቀን 2010 ዓ.ም 400 ኩንታል በቆሎና የ100 ሺህ ብር ድጋፍ በአርሲ ሮቤ ለሚገኙ ከ450 በላይ ተፈናቃዮች አስረክቧል፡፡
የድጋፍ ርክክቡ በተከናወነበት ወቅትም የአዋሽ አክሲዮን ማህበር የስራ አመራሮች ለህብረተሰቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያስታወቁ ሲሆን ሌሎች ኩባንያዎችም ይህን ልምድ በመቅሰም ለተፈናቃዮች በየፊናቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሚላ፣ ጉደር፣ ገበታ፣ አዋሽ በተሰኙ የወይን ጠጅ ምርቶቹ የሚታወቀው አዋሽ ወይን አክሲዮን ማህበር፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በግል ባለሀብቶች ይዞታ ስር የሚገኝ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ላይ 517 ሄክታር መሬት ላይ ሰፊ የወይን እርሻ ባለቤትም ነው፡፡
በወይን እርሻው አካባቢ ለሚገኙ ከ200 በላይ አባወራዎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቅርቡ በዶሌ፣ ዶኬቻና መልኩ ቀበሌዎችን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል፡፡ ቀደም ሲል ማህበረሰቡ የመጠጥ ውሃ ያገኝ የነበረው በቀጥታ ከአዋሽ ወንዝ ሲሆን ይህም ለውሃ ወለድ በሽታዎች ያጋልጥ እንደነበር ታውቋል። ድርጅቱ በ1.2 ሚሊዮን ብር የጋራ የንፁህ መጠጥ ውሃ መጠቀሚያ ቦኖ ለማህበረሰቡ ከማሰራቱም በተጨማሪ ለከብቶች የሚሆን የሰው ሰራሽ የኩሬ ውሃም አስቆፍሯል፡፡ በተጨማሪም የህፃናት ማቆያ ማዕከል መገንባቱንና የህክምና ክሊኒክ ግንባታዎችን  እያከናወነ መሆኑን ኩባንያው  አስታውቋል፡፡
በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ማህበረሰቡ እንዲያገኝና የአካባቢውን ወጣቶችም በተለያዩ የስራ መስኮች በድርጅቱ ውስጥ ቀጥሮ የስራ እድል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ኩባንያው ጨምሮ ገልጧል፡፡  
አዋሽ ወይን አክሲዮን ማህበር በአሁኑ ወቅት በልደታና በመካኒሳ በሚገኙ ፋብሪካዎቹ በዓመት 10 ሚሊዮን ሊትር የተለያዩ የወይን ጠጅ መጠጦችን እያመረተ መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 2810 times