Saturday, 13 January 2018 15:48

መንታ እውነት

Written by  መሐመድ ነስሩ (ሶፎኒያስ አቢስ)
Rate this item
(8 votes)

   ‹‹እዬብ!››
‹‹አቤት››
‹‹ት-ወ-ደ-ኛ-ለ-ህ?››
‹‹በጣም!››
ተጠመጠመችበት፤ እጆቿ አንገቱ ላይ ‹የአንገት ሹራብ› ሰሩ፤ … ተጠጋችው… በጣም ተጠጋችው፡፡
‹‹በደምብ እቀፈኝ! የኔ እንደሆንክ እንዳምን አድርገህ እቀፈኝ!››
አቀፋት፡፡ በደንብ አቀፋት! የእሱ እንደሆነች እንድታምን አድርጎ አቀፋት! አጥብቆ!!
‹‹ሳመኝ!!››
ሳማት፡፡
‹‹እንዲህ ነው የሚሳመው?››
‹‹ታዲያ እንዴት ነው?››
‹‹በደንብ አስጨንቀህ!››
አስጨንቆ ሳማት … ‹የአየር ያለህ!› እስክትል፤ ትንፋሽ እስኪያጥራት!
… ትወደዋለች፤ እንደሚወዳት ግን ማመን ቸግሯታል፡፡ የምትጠላው የዝምታ መጋረጃ በመሀላቸው መዘርጋት ጀመረ፡፡ አንድ የፍቅር ምዕራፍ በዝምታ ባከነ፡፡ በሚሰስቱ ዐይኖችዋ አየችው፡፡ ጠይም ነው፤ ቴምር የመሰለ! የተቀነደቡ የሚመስሉ ቅንድቦች አሉት፡፡ ክንዱ ላይ እንዳንተራሳት፣ ዐይኑን ጣሪያ ላይ ሰክቷል፡፡
‹‹ምን ሆነሃል?››
‹‹ምንም››
‹‹ምን እያሰብክ ነው?››
‹‹ምንም!››
‹‹ሶፋኒትን እያሰብክ ነው አይደል?››
ዝም አለ፡፡
‹‹ነው አይደል?!››
‹‹አይደለም፡፡›› ዋሻት
‹‹አትዋሸኝ››
‹‹አልዋሸሁሽም›› ሌላ ውሸት …
ስለ እራሱ ስሜት እርግጠኛ አይደለም። እርግጠኛ ነኝ ያለባቸውን የሀቆቹን ዘንጎች ሰዎች ነቅንቀውበታል፡፡ ራሱን እያወለቀ እንደሆነ ይሰማዋል - አንዳንዴ፡፡ ከእራሱ ርቆ የሚኖር ይመስለዋል፡፡ በሰዎች የሚዘወር ድኩም! ሰዎች እንደፈለጉ የሚያሾሩት፣ የሚቀባበሉት ኳስ!
‹‹ታፈቅራታለህ … ኢዮብ!››
‹‹ስንቴ ነው የምነግርሽ? በፍቅር ስሜት አስቤያት አላውቅም፡፡››
‹‹እውነቱን ልንገርህ?... ማፍቀርህን ማመን ስላልፈለግክ ነው እንጂ እንደምታፈቅራትማ ታውቃለህ?!
ሶፋኒት ከአፉ ወርዳ አታውቅም፡፡ ከጥርሶቹ ትቀርባለች ለምላሱ፤ ከደም ትዘወተራለች፣ ትዘልማለች በልቡ፡፡ ሰርክ ስለ እሷ ታላቅነት ያወራል፡፡ እሱን የሚያውቅ ሁሉ እሷን ያውቃታል። በቃላት ብሩሽ ምስሏን ስሎ ያሳያል፡፡ የሰብዕናዋን ግርማ ያነበንባል፡፡ በተለይ ለቀረበው ስለ እሷ ማውራት ከጀመረ የአዲስ አበባ ወረሀ-ሐምሌ ዝናብ ነው፡፡ ማባሪያ የለውም!፡፡ብስለቷ የሚደንቅ መሆኑን ይተርካል፡፡ ‹ሰማይ› ነው የሚላት፤ የማይደረስባት ሩቅ መሆኗን ለማፅናት …ሰማይ!
ከገነት ጋር በፍቅር መንፈስ የተዋወቁት በቅርብ ነው፡፡ ለዐይን እውቂያው ግን ሳይሰነብቱ አልቀሩም። ግቢው የግድ ያተያያል፤ ያገናኛል … ኮሜርስ! (ንግድ ስራ ኮሌጅ)…
‹‹ጥሩ ልጅ ነች›› ይላል ስለ ገነት ለጠየቀው ሁሉ፤ ‹‹የምትወደድ ልጅ ነች፤ ፍቅር አውቃ!›› ይህን ይመሰክራል፤ ለእሷም አይደብቃትም፡፡
ይወዳታል፤ ግና ሰዎች (ገነት ራሷን ጨምሮ) ስሜቱ ላይ ወጀብ ያበዙበታል፤ ማዕበል ይሞሉበታል፡፡
‹‹አንተ ልጅ በሶፋኒት ፍቅር ወድቀሃል›› ይሉታል፡፡ ያምታቱበታል፡፡
‹‹ፍቅርና መውደድን የሚነጥል አጥር ምንድነው? እውነት አፍቅሬያት ይሆን?››
‹‹ገኒ?!››
‹‹አቤት››
‹‹ከኔ በላይ እኔን የሚያውቅ ሰው አለ?..  እኔ’ኮ የማውቀው ሶፋኒት የማከብራት ጓደኛዬ፣ የምወዳት እህቴ፤ ገነት የማፈቅራት ፍቅረኛዬ መሆናቸውን ነው፡፡››
ከንፈሩን ሳመችው፡፡ እጆቿን ገላው ላይ ሸርተቴ አጫወተቻቸው፡፡
‹‹ይቅርታ የኔ ጌታ! … ስለማፈቅርህ’ኮ ነው! በጣም ስለማፈቅርህ!››
ፍፁም ተጠጋችው፡፡
*   *   *
ቤቱ ጠባብ ትመስላለች፡፡ ከበሩ በስተግራ አንድ አልጋ፣ በስተቀኝ አንድ መጽሐፍ መደርደሪያ፣ መሀል ላይ አንድ ወንበርና አንድ ጠረጴዛ ይታያሉ። መደርደሪያው አናት ላይ አንድ ፎቶ አለ - በውብ ፍሬም ውስጥ! የሶፋኒት ፎቶ! በወጣ በገባ ቁጥር ዐይኑን ጣል ሳያደርግባት አያልፍም፡፡ ብቻውን ከሆነ በድኑን ፎቶ እንደ ህያው ሰው አገላብጦ ይስመዋል፡፡
ሶፋኒት ኑሮዋ ወሊሶ ነው፡፡ በመምህርነት ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ከእዮብ ጋር የተዋወቁት እዛው ነው፡፡ ቤታቸውን ነው ተከራይታ የምትኖረው፡፡
‹‹እዮብዬ?!››
‹‹ወይዬ!››
‹‹እንጋባለን አይደል?!››
መልስ አልሰጣትም፡፡
‹‹አንተ እዬ …››
‹‹አቤት››
‹‹አንጋባም?››
‹‹እኔ እንጃ!›› ቅጭም ብሎ፡፡
ከእቅፉ ውስጥ ወጣች፤ ዐይኗ የዝንጀሮ እንትን መሰለ…
የዘወትሩን መልስ ሰጣት፡፡
‹‹ስለ ነገ ማንም እርግጠኛ አይደለም ገኒ!›› ጀርባዋን ሰጠችው፡፡ ፀጉሯን በተነችው፡፡ማባባል ለምዷል፤ ተለማምጦ ማሳመን! ተመልሳ እንድታቅፈው ለማድረግ በጣም ረጅም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡
‹‹እዮብ››
‹‹አቤት››
‹‹ሶፋኒትን’ኮ  ታፈቅራታለህ!››
ጭንቅላቱ መጦዝ ጀመረ፡፡
ፍቅር ከመጀመራቸው በፊት ስለ ሶፋኒት አውርቷታል፡፡ እጅግ በጣም ብ…ዙ! ያኔም ቢሆን  ታዲያ ‹‹የህይወቴን ጎዳና የለወጠች፤ ሰው ለሚባለው ፍጡር ክብር እንዲኖረኝ ያደረገች፤ የምወዳት፤ የምትናፍቀኝ፤ ጓደኛዬ!›› ከማለት የዘለለ አውርቷት አያውቅም፡፡
‹‹ከምትነግረኝ አንጻር እሷም የምትወድህ ይመስለኛል፤ እምቢ አትልህም፤ ለምን አትጠይቃትም?››
‹‹ገነት እባክሽ ተይኝ … እባክሽ!››
ቱግ ብሏል፡፡ በርከት ላሉ ጊዜያት ተወያይተው ዳግም ላያነሱት የተስማሙበት ርዕስ! ግን አንድም ቀን ሳይነሳ ሊታለፍ ያልተቻለ ርዕስ! ‹‹ገነት ምን እያደረገች ነው?›› ይጠይቃል ራሱን፤ በዚህ በኩል አፈቅርሃለሁ እያለች፤ በዛ በኩል የሶፋኒት እንድሆን መገፋፋት ምን ማለት ነው?
*   *   *
ማልዶ ነው የነቃው፡፡ እንዳይቀሰቅሳት ተጠንቅቆ ወረደ-ከአልጋው! የጉዞ ቦርሳውን በመሸካከፍ ላይ ነበር፡፡
‹‹ወ-ዴ-ት ነው?!›› ግራ እየገባት ጠየቀችው፡፡
‹‹ወሊሶ››
‹‹እ-ን-ዴ?!›› በድንጋጤ፡፡
‹‹ለምን?›› አላለችውም፡፡ ለምን እንደሚሄድ አልጠፋትም፡፡ ናፋቂ ነው፡፡ ናፋቂነቱን ጠንቅቃ ነው የምታውቅ፡፡ ሶፋኒት በጣም እንደምትናፍቀው፤ እሷን ብቻ ለማግኘት እንደሚመላለስም ታውቃለች። ፍቅረኛው ከመሆኗ በፊት አውርቶላታል፡፡ አሁንም የሚክዳት አይመስልም፡፡
‹‹ኤግዛም ሳምንት’ኮ ነው የቀረው!›› አለችው ከብርድ ልብስ ውስጥ ቀጭን ሰውነቷን እየመዘዘች፡፡
‹‹መሄድ አለብኝ››
ነገሩ ሁሉ ድንገት ነው፡፡ ‹‹ስሜቴን ማክበር እፈልጋለሁ፡፡›› ይላል ዘወትር! እና ውሳኔዎቹ ቅፅበታዊ ናቸው፡፡
ሊሰናበታት ሲጠጋ በሁለት ዓለም መካከል ሮጠ፡፡ ‹‹… እወዳታለሁ’ኮ! አዎ፤ እወዳታለሁ! ታዲያ ለምን ግራ ታጋባኛለች? በእርግጥ ለሶፊ ያለኝ ስሜት ጥልቅ ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ፍቅር ነው ማለት ነው? … መውደድ ብቻ የማይሆነው ለምንድን ነው? ለነገሩ ሰዎች የፈለጉትን ስም ቢያወጡ ምን አገባኝ! ስሜቴን ማመኔ ይበቃል! … ግን … አፈቅራት ይሆን? … ‹ብዙሀን ይመውኡ› ነው አይደል መጽሐፉ የሚለው? … አፈቅራታለሁ እንዴ ሶፊን?!››
ለመሄድ ቸኩሏል፡፡ ወሊሶ ደርሶ …
ጉንጯን ሳማትና ወጣ፡፡
‹‹ቤቱን ቆልፈሽ … ቁልፉን ጎረቤት አስቀምጪ እሺ?!››
የሰማችው አትመስልም፡፡ እሱም በእምባ የረጠቡ ዐይኖቿን ማየቱን ለራሱ መንገር አልፈለገም፡፡ እርምጃውን አፈጠነ…

Read 3296 times