Saturday, 13 January 2018 15:43

ፍቅር ለዘላለም ይኑር

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(3 votes)

   ጥበብ ያለ ቲያትር ኦና ናት፡፡ ጥበብን ከእነ አጎጥጓጢዎቿ ለመቃረም ካሻህ ከቲያትር እልፍኝ ተዶል፤ ያለው ጥበበኛ በእዝነ ህሊናዬ እያቃጨለ ቢፈታተነኝ፣ እንደ ምንም ትንፋሽ ሰብስቤ፣ በዕለተ ሰንበት  እግሬን አነሳሁ፡፡ የሀሩሩ በትር የዋዛ አልነበረም፡፡ በንዳዱ በትር ግን ወደ ኋላ አላፈገፈግሁም፡፡ ቆምጨጭ ብዬ መወዝወዜን ተያያዝኩት፡፡ እንደ ቀትር እባብ እየተንቀለቀልኩ ከቲያትሩ እልፍኝ ተቃረብኩ፡፡ ሰፊው እልፍኝ በሰው ጫካ ተወሯል፡፡ የቀረ የአዳም ዘር የለም፡፡ ገና ከአርበ ሰፊው አዳራሽ እንደተከተትኩ፣ የሆነ ደስ የሚል ድባብ መላ አካላቴን ሲደባብስኝ ተሰማኝ። የጥበብ ካራማ እላዬ ላይ እየተሳፈረብኝ እንደሆነ ገባኝ፡፡ ዙሪያ ገባውን በጥሞና ሰለልኩት፡፡ ወዲያ፣ ጥግ ላይ አፍላ ጥንዶች እርስ በእርስ መንቁራቸውን ሰክተው ነገር አለማቸውን ረስተዋል፡፡
 “ወትሮም ለፍቅር ባዳ የሆነ ገላ ለሩካቤ ሥጋ ይካለባል፤ ፍቅር ለዘላለም ይኑር፤“ በውስጤ መፈክር ቢጤ አነበነብኩ፡፡ አፍታም ሳይቆይ ጆሮ የሚሰረስር የቲያትር ማስጀመሪያ ደውል ተንጫረረ። የቤቱ ድባብን ተዋርሶት የነበረው ጫጫታ ወዲያው በጥሞና ተተካ፡፡
የመድረኩ መጋረጃ እንደተተረተረ፣ የውበቷ ፀዳል ከሩቅ የሚጣራ ጠይም ጣኦት መድረኩ ላይ ነገሰችበት፡፡ ያፍዝ ያደንግዝ ውበቷ እጅ ወደ ላይ ያለኝ ስለመሰለኝ፣ እጄን እንደ ምርኮኛ ወደ ላይ አንጨፈረርኩ፡፡  ከመጤፍ የቆጠረኝ ታዳሚ የለም፡፡
“እረ ጎበዝ! ምን አይነት ማሕጸን ነው ያፈራት!?”  በጺም ቁጥቋጦ የተወረረውን ፊቴን እንደ ካራ በሚበልተው መዳፌ እየቆፈርኩ ለራሴ አጉተመተምኩ፡፡
የመድረኳን ንግሥት እድምተኛው ሊውጣት ያሰፈሰፈ ይመስላል፡፡ እርሷም አተዋወኑን በእጅጉ ተክናበታለች፡፡ ተውረግርጋ፣ ተውረግርጋ አትጠግብም፡፡ እውነትም የመድረክ ንግሥት! አመልማሎ ከናፍሮቿን ክፍት ክድን እያደረገች፣ ትከሸዋ ላይ እንደ ሀር ነዶ የተበተነውን ፀጉሯን በአለንጋ ጣቶቿ ትሰቀሰቀዋለች፡፡ ውብ ገጽታዋ በነገር እየተብሰከሰች ስለመሆኗ  አፍ አውጥቶ ይናጋራል፤
“ይህ ሴት አውል፣ እግሩ እስኪቀጥን እንዲያ ተመላልሶ እጁ እንዳልስገባኝ፣ እንዲህ ለዓይኑ ይጠየፈኝ?” አለች፤ ሲቃ በተጫነው ድምጸት፡፡
 እንባዎቿ መንታ፣ መንታ እየሆኑ ተንጀረጀሩ። በምናብ እቅፌ ውስጥ ከትቼ ላጽናናት ሞከርኩ፡፡ ግና ብዙ አንገራገረችብኝ፡፡ ወዲያው እየተመናቀረች መድረኩን ጥላ እብስ አለች፡፡ መድረኩን መልሶ ጨለማ ዋጠው፡፡ አንጀት የሚበላ ለስላሳ ዜማ በአዳራሹ አራት መዓዘን መንቆርቆር ጀመረ፡፡
እረ እንደምንአለህ፣ እኔስ እንደምንም
እቱ እንደምናለህ፣ እኔስ እንደምንም
አምላክ የሰጠውን፣ ሰው አልችል አይልም
እንጉርጉሮው በስሜት ናጠኝ፡፡ በዜማው ላይ የተሰለፉት ስንኞች ሽንቆጣን ለመቋቋም ሀሞት ይጠይቃል፡፡ በዛ ላይ የድምጽዋ መረዋ፣ ውብ ዜማ ሲታከልበት  ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል፡፡
ትያትሩ ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡
አንድ ጥበበኛ የሀገር ሽማግሌ ፀጉሩን ካንጨፋረረ፣ ኮበሌ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠዋል፡፡ ኮበሌው፣ ጠይሟን ንግሥት ፊት የነሳው አባወራ መሆኑ ነው፡፡
 “ሚስቴ ዱላ የሚማዘዙባት ደመ ግቡ ሴት ናት፤ግን ምን ያደርጋል?” አለ፤ ራሱን እያሸሸ፡፡
“ወዲህ በል ጉዳይህን”  ጥበበኛው አዛውንት ለፍሬ ነገሩ ተቻኮሉ፡፡
”ለዓይኔ ጠላኋት፣ ሌላው ይቅርና አልጋ እንኳን ቀይረናል” አለ፤ ሀፍረት ባሸማቀቀው ስሜት፡፡
ጥበበኛው አዛውንት፣ በመቋሚያቸው ወለሉን እየቆረቆሩ፣ ጥቂት ደቂቃዎችን ጥሞና ውስጥ ገቡና፤  
“ልጄ፤ የፍቅር ጠኔ አጠናግሮኋል” አሉ፤ ገጽታውን እየሰለሉ፡፡
“አልገባኝም አባት”
“እንዲገባህ ከፈለክ የፍቅር ሰው ሁን!”
“በፍቅር ክንፍ ካደረገችኝ ጉብል ጋር እኮ ነው ሶስት ጉልቻ የመሰረትኩት”
“ነገር አለሙ ተሳክሮብሀል ጃል፣ ባልተቤትህ አእምሮህ ላይ እንጂ ልብህ ላይ የለችም፤ስለዚህ አእምሮህ ጠባይ ማረሚያ መግባት  አለበት”
“ምን  ማለት ይሆን አባት?”
“ሚስትህ በአእምሮህ ዓለም አርጅታለች፤ ዳግመኛ በፍቅር ክንፍ እንዳታደርግህ ከፈለክ አንድ መላ ላቀብልህ”
“ይፍጠኑ አባት”
“አእምሮህን አቂለው፤ጠዋትና ማታ ራስህን በመሰታየት እየተመለከትክ “ሚስቴ አይደለችም“፣ “ሚስቴ አይደለችም” እያልክ ለአእምሮህ ንገረው፡፡ አእምሮ እንደ ህጻን ልጅ የሰጡት ነው የሚቀበለው፤ ያን ጊዜ በራስህ ላይ የሚገርም ለውጥ ታስተውላለህ፡፡ ሚስትህን እንደ ትኩስ ፍቅረኛ መሻት ትጀምራለህ፡፡”
“አእምሮን የማቄል ስልት ነው ያሉት አባት? መቸም መላ ከእርስዎ አይጠፋም፤እስቲ ይሁና፣ በሰጡኝ ምክር ትንሽ አዝግሜ መለስ እላለሁ” አለ እና ጎፈሬውን ክምብል ቀና እያደረገ፣ ከመድረኩ ተሰወረ፡፡
የኮበሌው ለፍቅር መቃተት፣ የሀውልት ቀራጩን ታሪክ አስታወሰኝ፡፡
*   *   *
አንድ ሀውልት ቀራጭ ቁጭ ብሎ ለሀውልቱ የሚያስፈልጉትን ድንጋዮች በመሮና በመዶሻ እየቆራረጠ ሲያስቀምጥ የተመለከተ ሰው፣ ጠጋ ብሎ ቀራጩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡-
“ምን እየሰራህ ነው? ሀውልት አትሰራም እንዴ? እኔ ለመመልከት የመጣሁት እኮ ሀውልት ትቀርጻለህ ብዬ ነው፡፡ አንተ ግን ድንጋዮቹን  ብቻ ነው የምትቆራርጠው “አለው፡፡
“ሀውልቱ በድንጋዮች ውስጥ ተደብቋል፡፡ ከእኔ የሚጠበቀው ሀውልቱን የሸፈኑትን አላስፈላጊ ድንጋዮች ከላዩ ላይ መግፈፍ ብቻ ነው፡፡ ከእዚያ በኋላ ሀውልቱ እራሱን ይገልጣል፡፡ ሀውልት አይሰራም፣ ሀውልት ለመሥራት የሚያስፈልገው ከድንጋዩ ውስጥ የት እንደሚገኝ ለይቶ ማወቅ ብቻ ነው፡፡ የሀውልት ተፈጥሮ ልክ እንደ ፍቅር ተፈጥሮ ነው፡፡” አለ ቀራጩ፡፡
“ምኑን ከምኑ ጋር ነው የምታገናኘው ጎበዝ?!”  
“አየህ! ፍቅር በሰው ልጅ ልቦና ላይ (ልክ እንደ ሀውልቱ) ተዳፍኖ ተቀምጧል፡፡ ለእርሱ የሚያስፈልገው የሚገለጥበትን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው፡፡ ጥያቄው ፍቅር ከየት ይመጣል ወይም እንዴት ይፈጠራል ሳይሆን እንዴት በላዩ ላይ ተደራርተው የሸፈኑትን ድሪቶዎች ማስወገድ ይቻላል የሚለው ኹነኛ ጥያቄ ነው በቅድሚያ መመለስ ያለበት፡፡”  ቀራጩ የሰውዬውን ማሰብ የሚፈታትን የጠቢብ መልስ ሰጠ፡፡
*   *   *
ቲያትሩ ለሀውልት ቀራጩ ቢያንስ ኩርማን ድርሻ ሊሰጠው በተገባ ነበር፡፡ ታሪኩ ጥልቀት የጎደለው ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጡዘቱም ቢሆን በጣም የሳሳ ነው፡፡ ገጸባህሪ አሳሳል ላይ ብዙ የሚያሳማ ድክመት አለው፡፡ ትያትሩን በሂስ ካራዬ ያለ ርህራሄ እየበለትኩ ባለሁት ቅጽበት ፋታ የሌለው የእጅ ስልኬ፣ በጥሪው አስበርግጎ ወደ ገሀዱ ዓለም መለሰኝ፡፡
የፍቅረኛዬ የሥልክ ጥሪ ነው፡፡ ትውውቃችን ገና ወራትን አልተሻገረም፡፡ ይኸው በፍቅር መሀላ ከተሳሰርንበት ዕለት አንስቶ እንዳሻት ታከንፈኛለች። እኔም ሰርክ ዓይኗን ካላየሁ ደርሶ ሲያቅበዘብዘኝ ነው የሚውለው፡፡ በሱሷ ተለክፌያለሁ፡፡ አይቼ አልጠግባትም፡፡ እንዳትሟሟብኝ በሙሉ ዓይኔ አላያትም፡፡
ሥልኩ ለሁለተኛ ዙር መጥራት ጀመረ፡፡ እልኋ እንደ ውበቷ ነው፡፡ በዋዛ እንደማትለቀኝ ቢገባኝም በራሴ የሐሳብ ታንኳ መቅዘፉን ምርጫዬ አደረግሁ። በርግጥ ይህቺ ነፍስ እና ሥጋዬ የሚለይላት ውዷ ፍቅረኛዬ፣ የበኽር ልጅነቷ ለማን ይሆን? ለቅብዝብዙ አእምሮዬ ወይስ ለጭምቱ ልቦናዬ?
ውቧን ፍቅረኛዬን ከልቤ መንደር ላይ ላስሳት ተንደረደርኩ፡፡ ክልፍልፉን አእምሮዬን ጠርቅሜ፣ የሰከነውን ልቦናዬን ወለል አድርጌ ከፈትኩት። አሰሳው ግን ያለ ስኬት ተገባደደ፡፡ ኦና እጄን ተመለስኩ፡፡ ፍቅረኛዬ በልቤ አምባ ላይ የውሃ ሽታ ሆነች፡፡የቀረኝ አንድ እድል ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ወደ ተቅበዝባዡ አእምሮዬ ማማተር።  የምናቤን መስኮት ስከፍት፣ እርሷ እንደ እምቦሳ ስትቦርቅ አንድ ሆነ፡፡ ደመ-ነፍሴ በአሸናፊነት ስሜት ሲሰለጥንብኝ ይሰማኛል፡፡ ፊት ልሰጠው አልፈለግሁም፡፡በጥሞና አጤንኩት፡፡ ይህ ቡረቃ ውሎ አድሮ ለማዝገምም አይዶል፡፡ የኮበሌው ዕጣ ታወሰኝ፡፡ ጊዜ ለሚያቃናው፣ጊዜ ለሚያጎብጠው ፍቅር እጅ አልሰጥም ብዬ ለራሴ መሃላ  ገባሁ፡፡ ፍቅር ለዘላለም ይኑር!!

Read 1799 times