Saturday, 13 January 2018 15:42

‹‹…በልጅነት…. ልጅ መውለድ…ይብቃ …››

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 እናትነት …ሁሉም ነገር፡፡
እናት ካለች ቤተሰብ አለ፡፡ ቤተሰብ ሲኖር አካበቢ ወይንም መንደር ከዚያም አገር ይኖራል፡፡ አገር ካለ አለም እውን ይሆናል፡፡ እናት ደህና ካልሆነች ግን ሁሉም ነገር ይበላሻል፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው
በውጭው አቆጣጠር ከጃኑዋሪ 9/ እስከ ፌብረዋሪ 7/ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ድረስ ለአንድ ወር የሚቆይ የእናቶችን ደህንነት የሚመለከት Campaign ወይንም የተለያዩ ስራዎች የሚሰሩበት እቅድ ተነድፎአል፡፡
በርእስነት የተቀመጠው አባባል በእንግሊዝኛው <<…NO MOTHERHOOD…DURING CHILD HOOD…>> የሚለውን የዘንድሮው አገር አቀፍ የእናቶች ደህንነት የአንድ ወር ዘመቻ ካተኮ ረባቸው ነጥቦች አንዱ ነው፡፡ በዚህ አመት ሌላው በአጠቃላይ የእናቶች ደህንነትን በሚመለከት ለጉዳት ከሚዳርጉዋቸው ውስጥ የፊስቱላ ሕመም እንዲሁም የደም መፍሰስ እና በልጅነት በእርግዝና ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶች ምን እንደሆኑ ጎልተው እንዲወጡ እና የሚመለከተው ሁሉ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከላከላቸው የሚል እሳቤ የያዘ ነው። ይህንኑ መሰረት በማድረግም መልእክቶቹን ከተለያዩ ባለሙያዎችና የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከሆኑት በማሰባሰብ ለአንባቢ እነሆ ብለናል፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስትና በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት በእርግጥ በአገር ውስጥ ያሉ የፌስቱላ ታካሚዎች ምን ያህል ናቸው የሚለውን ለመለየት ወደሁዋላ በመመለስ የተደረጉ ጥናቶችን ማየት አስፈላጊ ቢሆንም የፌስቱላ ሕመም አሁንም ድረስ መኖሩን ግን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት ቁጥር ከፍ ዝቅ ቢልም ባሁኑ ወቅት ግን ከ5-7/ሺህ/ድረስ የሚሆኑ ኢትዮያውያን ሴቶች በዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው የሚል ግምት አለ፡፡ ስለዚህም ፊስቱላ ሙሉ በሙሉ ጠፍቶአል የማይባል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት መስራት የሚያስችል አደረጃጀት ስላለ የተሸለ ነገር ይታያል፡፡ መንግስትም ፊስቱላን ለማጥፋት የሚል ፕሮግራም ነድፎ ሐም ሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያም በግብረኃይሉ የሚሳተፍ ሲሆን የዚህ እቅድም በ5/አመት ጊዜ ውስጥ ፊስቱላ እንደዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር የማይሆንበት ደረጃ እንዲፈጠርና ለአዳዲስ ተጎጂ ዎችም አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ በተገቢው መንገድ ማዳረስ ይገባል የሚል ነው፡፡
ዶ/ር ዋሲሁን አለማየሁ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት እና በአሰላ Referral & teaching ሆስፒታል የፊስቱላ ሕክምና ክፍል አስተባባሪና ኃላፊ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ፊስቱላ የሚከሰተው በዋናነት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሲሆን በተለይም በተራዘመ ምጥ ምክንያት ነው፡፡ አንዲት ሴት በምጥ ከ24/ሰአት በላይ ከቆየች በእራስዋም እንዲሁም በልጅዋ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡  ከዚህም በተጨማሪ በቤታቸው በተራዘመ ምጥ ቆይተው ለእርዳታ ወደሆስፒታሉ የመጡ እናቶችን የማዋለድ ስራ በሚሰራበት ወቅት በተለያዩ መሳሪያዎች መጠቀምና ኦፕራሲዮን ማድረግ ስለሚኖር በዚያ ምክንያትም ለፊስቱላ የሚጋለጡ እናቶች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሌሎች ምክንያቶች ማለትም ለምሳሌ ለካንሰር ሕክምና በሚደረጉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሳቢያ ፊስቱላ ሊከሰት ይችላል፡፡
በዚህ በእናቶች ደህንነት ምክንያት የሚነሳው ፊስቱላ ከማህጸንና ዙሪያውን ካሉ አካላት ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ቀዳዳ ሲፈጠር የሚታየውን ሲሆን ቃሉ ግን በማንኛውም የሰውነት ክፍል አላስፈላጊ ቀዳዳ ተፈጥሮ ሲታይ የምንጠቀምበት ነው፡፡ በእናቶች ላይ ስንመለከተው በማህጸንና በሽንት መሽኛ አካባቢ ወይንም በማህጸንና በሰገራ መውጫ አካባቢ የሚፈጠር ቀዳዳ ፊስቱላ ይባላል። ይህም በኢትዮጵያ ፊስቱላ የሚባለውን የጤና ችግር ከ90/በመቶ በላይ ድርሻ ይይዛል፡፡ በወሊድ ሰአት ልጁ በሚያልፍበት መንገድ ላይ እና በሽንት ፊኛው መሐል ላይ ለረጅም ሰአት ሲቆይ የደም ዝውውር ይዛባል፡፡ የደም ዝውውር ሲዛባ የሽንት ፊኛውና የወሊድ አካል ለረጅም ጊዜ ደም ስለሚያጣ ይጎዳል፡፡ ያ ክፍል ደም በማጣቱ ምክንያትም ስለሚሞት ይረግፋል፡፡ በሚረግፍበት ጊዜ በፊት ያልነበረ ክፍተት በሁለቱ መካከል ይፈጠራል። ያ ክፍተት ደግሞ ሽንት በማንኛውም ጊዜ ሴትየዋ ልትቆጣጠር በማትችልበት መንገድ ይፈሳል፡፡
ፊስቱላ መከላከል የምንችለው ነገር ነው፡፡ መከላል የሚቻል ነገር በመሆኑም ሁሉም ባለሙያውም ሆነ ህብረተሰቡ በቀበሌ ደረጃ ካሉት ጀምሮ የሚችለውን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሐኪሞቹ ችግሩ የገጠማቸው ሴቶች ሲመጡ ሕክምናውን ከመስጠት ባሻገር ያቺ የታከመች ሴት ከእራስዋ አልፋ ሌላዋን እናት ማስተማር እንድትችል አቅም ፈጥሮ ወደቤተሰብዋ መቀላቀል ተገቢ ነው፡፡ እየሰራን ያለነውም በዚህ መንገድ ነው፡፡
ጤና መኮንን ብርቄ ግርማ
ጤና መኮንን ብርቄ ግርማ እንደገለጹት በአሰላ ሆስፒታል የፌስቱላ ታካሚዎች የሚረዱት በአንድ ክፍል ውስጥ የነበረ ሲሆን ከማህጸንና ጽንስ ሕክምና ክፍል ጋር በተያያዘ ሕክምናው ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ክፍል እራሱን ችሎ ባለሙያዎችም ለብቻ ተቀጥረው በማገልገል ላይ እንገኛለን፡፡ የፌስቱላ ሕክምና ክፍሉ የራሱ የሆነ 15/አስራ አምስት አልጋ ያለው ሲሆን በወር ውስጥ በአማካይ ከ6-10/ታካሚዎችን ያስተናግዳል፡፡ የታካሚዎች ሁኔታ እንደማንኛውም ታካሚ ከወቅት ጋር የሚያያዝ ሲሆን በክረምት እና በበጋው ወቅት ከፍና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በክረምት ወቅት እነዚህ ታማሚዎች ያሉበትን አካባቢ አቋርጠው ወደጤና ተቋሙ ለመምጣት ስለሚቸገሩ ባሉበት የሚቆዩ ሲሆን የቅስቀሳ ወይንም ትምህርት የመስጠቱን ነገር ተከትሎም ታካሚዎች ቁጥራቸው ከፍና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከጤና ጣቢያዎች ጋር በመሆን ከአሰላ ሆስፒታል የፊስቱላ ሕክምና ክፍልም እየሄድን አብረን ትምህርት እንሰጣለን፡፡ ፊስቱላ የተባለው የጤና ችግር የሚገጥማቸው በተራዘመ ምጥ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንገድ እርቀት፣ የገንዘብ እጥረት ወይንም ቀደም ሲል ከነበሩ ቤተሰቦች የህይወት ልምድ በመነሳት እቤት መውለድ ትክክለኛው ነገር ነው ብሎ በማሰብ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም አለመሄድ ለችግሩ መንስኤ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ እቤት ውስጥ በተራዘመው ምጥ ቆይታ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ጤና ጣቢያ ብትሄድም በማዋለድ ሂደቱ ላይ ፊስቱላ የሚከሰትበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ደግሞ ፊስቱላ የሚከሰተው በአብዛኛው በመጀመሪያ ልጅ መውለድ ጊዜ ሲሆን እነዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ እርጉዝ የሚሆኑት በአብዛኛው በልጅነት እድሜያቸው የተዳሩና ያረገዙ ሴት ልጆች ናቸው፡፡ ፊስቱላ ብዙ ምክንያ ቶች ቢኖሩትም ቀደም ሲል የጠቀስናቸው በግልጽ የሚታዩ ናቸው፡፡
‹‹…እኔ የመጣሁት ከወላይታ ነው፡፡ ዛሬ 22/አመቴ ነው። ትዳር ከያዝኩ ወደ 7/አመት ይሆነኛል፡፡ ትዳር በያዝኩ ወቅት ወዲያው በአመት ጊዜ ውስጥ ነው ያረገዝኩት፡፡ ምጥ የመጣ ጊዜ ግን በጣም ተቸገርኩ፡፡ ወደጤና ጣቢያ እንዳይወስዱኝ ሩቅ ስለሆነ ይበል ጡኑ ትጎዳለች ብለው እቤት አስቀመጡኝ፡፡ ነገር ግን በአምስተኛው ቀን ትሞታለች ብለው በቃሬዛ ተሸክመው ወሰዱኝ፡፡ ጤና ጣብያ ስደርስ ልጄ ሞቶ ነበር፡፡ እኔም ሳልሞት ለጥቂት ነው የተረፍኩት። ከዚያም ወደቤቴ መለሱኝ፡፡ ሌላ ችግር ደግሞ ተከሰተ። ሽንቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ከሶስት አመት በላይ ሽንቴ ሲፈስ ይህ የእግዜር ቁጣ ነው ብለው ዝም ብለውኝ ነበር፡፡ በሁዋላ ግን ትምህርት የሚያስተምሩ ሐኪሞች ሲመጡ ጉዋደኛዬ የሆነች የጎረቤት ልጅ ጠቁማ ካለሁበት ድረስ መጥተው አዩኝ፡፡ ከዚያም በቀጥታ ወደሐምሊን ፊስቱል ሐኪም ቤት እንድመጣ ተደረገ፡፡ አሁን ሕክምና ተደርጎልኝ ድኛለሁ፡፡ በጊዜው ግን እንዴት አድርጌ እራሴን እንደማጠፋ ነበር የማስበው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን …ስንት አመት ከተሰቃየሁ በሁዋላ አሁን ድኛለሁ፡፡››
በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮፕያ ታካሚ  
አንዲት ሴት ቅድመ እርግዝና ምርመራ አድርጋ …በእርግዝናዋ ጊዜ ክትትል ሳታቋርጥ ወደሕክምና ተቋም ሄዳ በሰለጠነ ባለሙያ የምትወልድ ከሆነ …ፊስቱላ አይከሰትም። በየትኛውም አቅጣጫ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ በተጉዋዳኝ የፊስቱላ መኖርንም እየቀነሱት ይመጣሉ፡፡
ዶ/ር ፈቃደ አየናቸው

Read 3980 times