Print this page
Saturday, 13 January 2018 15:28

ፊጣ ባይሳ የዓለም ኮከብ ለመሆን የበቃ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 በአምቦ ከተማ የተወለደው ፊጣ ባይሳ ፤ ከእነ ኃይሌ የቀደመ የሩጫ ታሪክ አለው፡፡ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የትራክ ሩጫዎች፤ በአገር አቋራጭ ውድድሮች በኢትዮጵያ ሩጫ ታሪክ በፈርቀዳጅነት የሚጠቀስ  የቀድሞ አትሌትና ኦሎምፒያንም ነው፡፡  ፊጣ ባይሳ  በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ  ኢትዮጵያን በመወከል፤ ፈር ቀዳጅ  ድሎችን ካስመዘገቡ የ እጅግ ጠንካራና ቀደምት  አትሌቶች አንዱ ነው፡፡ በተለይ   በ5000 እና በ10000 ሜትር  በኦሎምፒክ፤ በዓለም ሻምፒዮና   ፤  በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ፤ የሃገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ  ውድድሮችለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በማሸነፍ  ብዙ ተብሎለታል፡፡          
በዓለም አቀፍ ውድድሮች በውጤታማነት ጎልቶ መውጣት የጀመረው ከ1991 እ.ኤ.አ አንስቶ ሲሆን በጃፖን ቶኪዮ በተደረገ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዩና በ5ሺ ሜትር  የብር ሜዳልያ እንዲሁም በግብጽ ከተማ ካይሮ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳልያ ካገኘ በኋላ ነው፡፡፡፡  በ1992 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በቦስተን በተከናወነ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 3ኛ በመውጣት ከወሰደው የነሐስ ሜዳልያ በተጨማሪ፤ በካናዳ  በተደረገ ኮንትኔንታል ካፕ ላይ በ10ሺ ሜትር አገሩንና አፍሪካን በመወከል አሸንፎም  የወርቅ ሜዳልያ ፤ በ1993 እ.ኤ.አ በጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ በተደረገ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች  በመካፈል በ10 ሺ ሜትር 2 የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡በ1992 እኤአ ላይ የስፔኗ ከተማ ባርሴሎና ባስተናገደችው ኦሎምፒክ ላይ ነው አስደናቂ ስኬቱ የተጀመረው፡፡   በስፔን ከተማ ባርሴሎና በተደረገው ኦሊምፒክ  ደራርቱ ቱሉ በሴቶች 10ሺ ሜትር ለአፍሪካ ፈርቀዳጅ ውጤት አስመዝግባ ስታሸንፍ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያገኘው ትኩረት ቀላል አልነበረም፡፡ በዚሁ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት የትራክ ላይ ውድድሮች  ለፊጣ  ባይሳ   የነበረው ግምትም የላቀ ነበር፡፡ በተለይ በ10ሺ ሜትር እንደሚያሸንፍ  የዓለም  የስፖርት ሚዲያዎች ብዙ ዘግበውለታል፡፡ በተለያዩ የስሌት ቀመሮች የተሰሩ የኮምፒውተር ትንበያዎችም ድሉን ለሱ ነበር የሰጡት፡፡ የወርቅ ሜዳልያው ድል ሳይሳካለት ቀረ፡፡  ከኦሎምፒክ መልስ በሰጠው ቃለምልልስ  ‹‹..ምን እንደሆንኩ አላውቅም እግሬ ውሃ ሆነ…››  ብሎ ነበር፡፡
በ5ሺ ሜትር ግን ማጣርያዎቹን በብቃት በማለፍ የነሐስ ሜዳልያን ሊጎናፀፍ ችሏል፡፡ በኦሎምፒክ  መድረክ ለ2ኛ ጊዜ ለመሳተፍ የበቃው  ደግሞ በ2000 እኤአ የአውስትራሊያዋ ሲድኒ ባዘጋጀችበት ወቅት ሲሆን አትሌት ሚሊዮን ወልዴ የወርቅ ሜዳልያ በወሰደበት የ5ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር የጨረሰው በ4ኛ ደረጃ ነበር ፡፡
በ1993 እኤአ ላይ በ5ሺ ሜትር 43 ዓለም አቀፍ  ውድድሮች 41 በማሸነፉ በዓለም ዙርያ ተደንቋል፡፡  በዚያን ጊዜ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አማካኝነት የዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫ ባይካሄድም የዓመቱ ምርጥ ብቃት ያሳየ አትሌት የሚል ክብር ተሰጥቶታል፡፡  
በሩጫ ዘመኑ ከተሳተፈባቸው አስደናቂ ውድድሮች አንዱ በ1999 እኤአ ላይ ቤልግሬድ ከተማ ውስጥ Belgrade Race Through History የከተማዋን ታሪካዊ ስነህንፃዎች በሚያካልሉ ጎዳናዎች የተደረገው ሲሆን ታዋቂውን ኬንያዊ አትሌት ፖል ቴርጋት በሰከንድ ልዩነት ቀድሞ በመግባት ያሸነፈበት ነው፡፡
ኤአርአርኤስ በድረገፁ ባሰፈረው መረጃ መሰረት 40 ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ውድድሮች በማሸነፍ በይፋ የሚጠቀስ ከሽልማት ገንዘብ በድምሩ 78050 ዶላር እንደተከፈለው ነው፡፡
1 ጊዜ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮን፤ በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች፤ በዓለም ሻምፒዮና 1 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች እንዲሁም በኦሎምፒክ 1 የነሐስ ሜዳልያ   ክብሮችን መጎናፀፉ የላቀ ስኬቶቹ ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡ በሩጫ ዘመኑ የተጎናፀፋቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የመጀመርያው የወርቅ ሜዳልያ ክብሩ በመላው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሲሆን፤ ኢትዮጵያንና አፍሪካን ወክሎ ደግሞ በኮንትኔንታል ካፕ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር ሊጎናፀፍ ችሏል፡፡
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ ልምድ ያለው ሲሆን ትልቁ ውጤቱ በ1992 ቦስተን ላይ በተደረገ የዓለም ሻምፒዮና ሶስተኛ ደረጃ ያገኘበት ነው፡፡
በትራክ 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ከፍተኛ ስኬት ያገኘ አትሌት ቢሆንም በ1500 ሜትር፣ በ3000ሜትር ፤ በጎዳና ላይ ሩጫዎች በሆላንድ፤ በጀርመን፤ በፈረንሳይ እና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች እንዲሁም በአሜሪካ በርካታ ውድድሮችን ሊያደርግ ችሏል፡፡ የመጨረሻው ውድድሩ በ2002 እኤአ በፈረንሳይ ኒስ የተሳተፈበት የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን የ21 ኪሜትር ርቀቱን 1:05:23 በሆነ ጊዜ ሸፍኖታል፡፡
ፊጣ ባይሳ ሩጫን ካቆመ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በኢንቨስትመንት ተሰማርቶ ትኩረቱንም በዚያው ላይ አድርጎ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቶች የውጤት ታሪክ አስገራሚ እውቀት ያለው ቢሆንም በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ በክብር እንግድነት እየተጋበዘ አስተያየቶችን ከመስጠት ባሻገር ወደ ስፖርቱ ያለው ቅርበት የተወሰነ ነው፡፡

ምርጥ ሰዓቶቹ
1500 ሜትር - 3:35.35 (1999 እኤአ)
3000 ሜትር - 7:35.32 (1996)
5000 ሜትር - 13:05.40 (1993)
10,000 ሜትር - 27:14.26 (1992)
8 ኪሎ ሜትር - 22:22 (2000)
5 ማይል - 22:29 (2000)

Read 4426 times