Saturday, 13 January 2018 15:27

በቱኒዝያ ከ600 በላይ፣ በኢራን 3700 ተቃዋሚዎች ታስረዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የቱኒዝያ መንግስት ግብር ለመጨመር ከያዘው አዲስ እቅድ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሰኞ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ፣ ባለፈው ረቡዕ ምሽት ብቻ ከ330 በላይ ዜጎች ለእስር መዳረጋቸውንና ባለፉት ቀናት የታሰሩት ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሱፍ ቻሄድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዜጎችን ለከፋ ጥፋት እያነሳሱ መሆናቸውን በማውገዝ፣ ዜጎች ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ካሊፋ ቺባኒ በበኩላቸው፤ረቡዕ ምሽት በቁጥጥር ስር የዋሉት 330 ሰዎች ተቃውሞውን ያቀናበሩና ግርግሩን ሽፋን በማድረግ የዝርፊያ ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ ናቸው ማለታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ዜጎች በዋጋ መናርና እየከፋ በመጣ የስራ አጥነት በተማረሩበት ወቅት መንግስት በዜጎች ላይ የግብር ጫና ለማድረግ ማሰቡ ብዙዎችን ማስቆጣቱንና በመዲናይቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሳምንቱን ሙሉ በመቀጠል ወደ ሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን፣ የአገሪቱ መንግስትም እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች አሰማርቶ፣ ተቃውሞውን ለማብረድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ተቃዋሚዎች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የደህንነት ቢሮ ህንጻዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ተቋማትን ማቃጠላቸውንና ወደተለያዩ ከተሞች የተስፋፋውና ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻዎችን ጭምር ያጥለቀለቀው ተቃውሞ ተባብሶ በመቀጠሉ መንግስት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በመላ አገሪቱ ማሰማራቱንም ገልጧል፡፡
በቱኒዝያ በ2011 እና በ2015 የተካሄዱ ተቃውሞዎችና ጥቃቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ስምንት በመቶ ድርሻ የሚሸፍኑትን የውጭ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማውደማቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ በኢራን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄዱ ጸረ-መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተሳትፋችኋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ዜጎች ቁጥር 3 ሺህ 700 እንደሚደርስ፣ አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ ማስታወቃቸውን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
በኢራን በተቃውሞ ተሳትፋችኋል በሚል ከተያዙት ዜጎች መካከል አምስቱ በእስር ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል ያለው አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኢራን መንግስት ያሰራቸውን ዜጎች በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥያቄ ማቅረቡን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በእስር ላይ በሚገኙ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ እየደረሰ ነው፣ እስር ቤቶቹ የሚገኙበት ሁኔታም እጅግ አስቸጋሪና ስቃይ የሞላበት ነው የሚለው  አምነስቲ፤ ጉዳዩ በአፋጣኝ በገለልተኛ ወገን  እንዲጣራና በእስረኞች ላይ ግፍ የሚፈጽሙ አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

Read 1526 times