Saturday, 13 January 2018 15:21

የ‘ፋሺን ነገር’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

“--የምር ግን ይሄ የመጥቀስ ታክቲከና ስትራቴጂ ጊዜ አልፎበታል እንዴ! በፊት የሆነች እንትናዬን የፈለጋት ሰው… አለ አይደል… ሰው እንዳይነቃበት ራቅ ብሎ ይጠቅሳታል፡፡ ሳቅ ካለች ‘መርሀ ግብሩ’ ግቡን መታ ማለት ነው፡፡ ከተኮሳተረች ደግሞ “ለአሁኑ አልተሳካም” አይነት ነገር ነው ማለት ነው፡፡--”
         
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ኸረ እባካችሁ ይቺን ልጅ አንድ በሏት!”
“ማንን ነው የምትዪው?”
“ይቺ የእትዬ ቦጋለች ልጅ…”
“ምን ሆነች?”
“እንዴ ብላ፣ ብላ ቀሚሷን ቁርጭምጭሚቷ ላይ ታድርሰው!”
“ምን!  ቀሚሷን ቁርጭምጭሚቷ ድረስ! አበስኩ ገበርኩ፣ ምኑን አሰማኝ እባካችሁ፡፡”
ቀሚስ ቁርጭምጭሚት ሲደርስ “ልጅቷ ተበላሸች” ተብሎ የመንደር ወሬ የሚሆንበት ጊዜ ነበር… አንድ የድሮ እንግሊዝኛ መጽሔት ላይ “በድሬዳዋ ከተማ ሚኒስከርት ለብሰው የተገኙ ሴቶች በፖሊስ ተያዙ” ምናምን የሚል ዜና ነበር፡፡
ዘንድሮ ሚኒስከርት የሚለብሱ ሴቶች፤ “ይቺ ምን አይነቷ ወግ አጥባቂ ነች! ቀሚሷ እኮ መሬቱን ሊጠርግ ምንም አልቀረው” ባይባል ነው! የፋሺኑ ነገር ልንከታተለው ከምንችለው በላይ ሆኖብናል፡፡ (‘ፋሺን’ ከተባለ ማለት ነው!)
በዛ ሰሞን ነው፤ የልጅቱ ጸጉር አሠራር ይሄ ሽቅብ የሚቆለለው አይነት ነው፡፡ (ይቅርታ፣ አጠራሩን ባለማወቅ ነው፡፡) እና በጣም ከመቆለሉ የተነሳ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶች ሁሉ ዘወር ብለው ያዩዋት ነበር፡፡ ያለ ማጋነን…የቁልሉ ርዝመትና ከወገቧ እስከ ግንባሯ ያለው ርዝመት እኩል ሊሆን ጥቂት ሚሊ ሜትሮች ቢቀሩት ነው። የምር የናሳ ሰዎች ቢያይዋት ኖሮ፣ የቁልሉን ጫፍ ለአንቴና መትከያ ይኮናተሯት ነበር፡፡ (የ‘ቢዝነስ’ ሀሳብ ስለሰጠሁሽ ኮሚሽኑን አትርሽኝማ፡፡ መቼም ዘንድሮ ገና “እንደምን አደርክ?” ከተባባልን በኋላ “በል ኮሚሽኗን ግፋ” ሳንባባል አንቀርም።)
እና አንዱ ቀለድኩ ብሎ “አንገትሽ እንዳይሰበር” ምናምን ይላታል፡፡ ምንም መልስ አልሰጠችውም፡፡ በቃ፣ ዘወር አለችና በግልምጫ የእርግማኑን መአት ቆለለችበት…እንደ ጸጉሯ ማለት ነው፡፡
የጸጉር ነገር ከተነሳ…‘አፍሮ ስታይል’ ነገርም በርከት ያለ ይመስላል፡፡ ዘንድሮ መአት ወንድ ጸጉሩን ዞማ ለማድረግ በየውበት ሳሎኑ በሚገባበት ጊዜ አፍሮ መምጣቱ አሪፍ ነው። ጸጉርን ማከርደድ ምን ችግር አለ!…ቢራ እንዲህ ኪስ ላይ ከባድ ጫና በማያሳድርበት ዘመን፣ ጸጉር ለማከርደድ እንጠቀምበት ነበር… አዎ፣ ጸጉርን ማከርደድ ፋሺን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ…‘ ሬይንቦው’ ጸጉርም የዚህ ዘመን ፋሺን ሆነ እንዴ!
እቴ ተማረኩልሽ
በሬይንቦው ጸጉርሽ
--የሚል ግጥም የማይወጣሳ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛ አሁን ‘ፋሺን ተከታዮች’ ነው የምንባለው! ‘ኮራጆች’ ነው የምባለው! “እኔስ ለምን ይቅርብኝ!” ነው የምንባለው! የሆነ ነገር አንድ፣ ሁለት ሰው ካደረገው…የሚስፋፋበት ፍጥነት የሚገርም ነው፡፡ ‘የጉንፋን ወረርሽኝ’ እንኳን እንደዛ በሆነ ፍጥነት አይዛመትም! የተበጫጨቀ ጂንስ መልበስ ከተጀመረ፣ ይሄን ያህል ጊዜ ሆኗል እንዴ! አሁን ትልቁም፣ ትንሹም የተቦተራረፈ ጂንሱን እያደረገ፣ እኛ ግራ ገባን እኮ… ስጋ እንይ ጨርቅ! (ቂ…ቂ…ቂ…) የምር ግን፣ አንዳንድ የ‘ፋሺን’ አይነቶች የ‘ኤጅ ግሩፕ’ ምናምን አይባልባቸውም እንዴ! (አዛውንቱ ሁሉ ባለ ፋሺን ሆኗል… እንዴ ጭራሽ ወላጅና ልጅ በፋሺን መፎካከር የጀመሩ ይመስላል እኮ! አሀ…‘ፕላቲነም ደረጃ’ ወላጅ ሁሉ ገባበት እኮ፤ ለማብራራት ‘ፕላቲነም ደረጃ’ ወላጅ ማለት ስድስት ወይም ሰባት ለዓለም ያበረከተ ነው፡፡)  
ስሙኝማ…በቀደም አንድ ‘የከተማ ሰው’ (አዲስ አበባ መወለድና መኖር ብቻ ‘የከተማ ሰው’ ማሰኘቱ አብቅቷል፡፡ ‘የከተማ ሰው’ መገለጫዎች እየተለወጡ ነውና፡፡) እና ይሄ የከተማ ሰው በመብልም የሆነ የ‘ፋሺን’ ነገር ያለ ይመስላል ሲለን ነበር፡፡ በፊት ያለ‘ፒፐር ስቴክ’ እና ያለ‘ላዛኛ’ የማይነኩ የነበሩ ወጣቶች፤ ወደ ጥሬ ስጋ ሰፈር እየመጡ ነው ሲል ነበር፡፡  
እግረ መንገድ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በዛ ሰሞን የጥሬ ስጋን ፕሮፋይል ከፍ ማድረግ ይገባው የነበረ ነገር ሰምተን ነበር፡፡ ሌላ አገር እንዲህ ነዋ! ለካስ ጥሬ ስጋ፣ ለዶሮ ማነቂያ ብቻ የተሰጠ …አይደለም! ለነገሩ እንኳንም ተነገረን...በየድራፍት ጠረዼዛው የተባባልነውን እኛ ነን የምናውቀው፡፡ (እኔ የምለው…ዘንድሮ ዶሮ አራት መቶ ሀምሳ ብር የገባችበትን ምክንያት የሚያብራራልን ባለሙያ እንፈልጋለን፡፡ ይሄ የዶላር ነገር በዶሮውም መጣ እንዴ!)
“እኛ ጥሬ ጎመን አሮብን፣ እዛ ጥሬ ስጋ ይጨረገዳል!” ለማለት ፈልገን እንዳልሆነ ግንዛቤ ይግባልን፡፡ ምክንያቱ እንዲህ ከታች ተስፈንጥረን ስንሄድ ‘ምቁነት’ ሊመስል ይችላል፡፡ (መሰለ፣ አልመሰለ ምን ለውጥ ያመጣል!…‘ጊዜው’ ለገሚሶቻችን አልተመቸማ! ገሚሶቻችን ምች የመታው ቆስጣ የመሰልነው…ማማር ጠልቶብን አይደለም፡፡ ገሚሶቻችን ከሶማሌ ተራ ተረፈ ምርቶች የተሠራን የምንመስለው ማማር ጠልቶብን አይደለም እኮ!)
በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ልክ ንብረት ይመዘገባል እንደሚባለው… አለ አይደል… የአለቆች የምግብ ምርጫም ይካተተልን። ልክ ነዋ!…በሚመርጡት የምግብ አይነት ትንሽ ስለ ባህሪያቸው “እንደዚህ ነው፣እንደዛ ነች” ለማለት ያስችለናላ!
ለምሳሌ የሆነ ቪ.አይ..ፒ ባለ ወንበር… “ለምሳ ከአንድ ስፔሻል ክትፎ ጋር አንድ ጣባ ሙሉ ቆጭቆጫ እወዳለሁ፣” ቢል … ጉግል ገብተን “ክትፎ በቆጭቆጫ የሚያበዛ ሰው ባህሪይ ምን አይነት ነው?” ብለን እንጠይቃለን። ከዛም የማይሆን ውሳኔ ሲያሳልፍ…
“ድሮስ ቢሆን በአንድ ጊዜ አንድ ጣባ ሙሉ ቆጭቆጫ ከሚጨርስ ምን ይጠበቃል!” ምናምን ማለት እንችላለን፡፡
ደግሞላችሁ… የሆነ ውሳኔ መስጠት የሚያቅተው አለቃ ይኖር ይሆናል፡፡ የምር እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ትንሿን ደብዳቤ ለመፈረም የጸጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ  የሚያስመስለው አይነት አለቃ ለማለት ነው፡፡
“ለመሆኑ ከምግብ ምን ትወዳለህ?”
“ከምግብ በዋናነት የምወደው ገንፎ ነው”
ገንፎ! (ቂ…ቂ…ቂ…) ገንፎ መሆኑን ካወቅን “ድሮስ ገንፎ እየዋጠ ድፍረቱን ከየት ያምጣው!” እንላለን፡፡ በነገራችን ላይ ገንፎ ለምንድነው ከሆነ ከደካማነት ምናምን ጋር የሚያያዘው!
ስሙኝማ…አንድ ሰሞን ራቁታቸውን ሲደንሱ ተያዙ ምናምን -- የከተማችን ትልቅ ወሬ ነበር፡፡ እሱ ነገር…‘ክፉ ነገር’ መሆኑ ቀረ እንዴ! አሀ…አሁን ራቁትነት አውራ ጎዳና እየወጣልን ይመስላላ!… እኛ ዘንድ የመጣው ‘ግሎባላይዜሽን’ ከማርስ፣ ከቬነስ ምናምን ነው እንዴ!
ፈረንጆቹ ‘ኑድ ኮሎኒ’ የሚሏቸው ነገሮች አሉ። በቃ…ሸሚዝ የለ፣ ቀሚስ የለ…ሁሉም “አዩኝ፣ አላዩኝ” ሳይል መለመላውን ‘እንደ ልቡ’ ወዲህ ወዲያ ይላል፡፡ “አየሁባት፣” “አየሁበት፣” ብሎ እርስ በእርስ ማሳበቅ የለማ፡፡ (የማንም ታይቶ የማንም አይቀርማ!) እናማ አንዳንዴ አንዳንድ የከተማችን አካባቢዎች ‘ኑድ ኮሎኒ’ አይነት ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም ነው የሚባለው፡፡
ስሙኛማ…ከጥቂት ጊዜ በፊት የሆነ ነው። ከወጣትነት ክልል ሊወጣ ጫፍ ላይ ያለ ነው። እና የሆነ ካፌ ውስጥ ነው አሉ፡፡ ከርቀት አይቶ የሆነች ልጅ ላይ ቀልቡ አረፈ መሰለኝ። (‘አረፈ’ ነው ‘አኮበኮበ’ የሚባለው!) እናም…ከርቀት እንደ መጥቀስ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ ከጓደኞቿ ጋር በሳቅ ተንፈራፈሩዋ!  መጥቀስ! ያውም በዚህ ዘመን!
የምር ግን ይሄ የመጥቀስ ታክቲከና ስትራቴጂ ጊዜ አልፎበታል እንዴ! በፊት የሆነች እንትናዬን የፈለጋት ሰው… አለ አይደል… ሰው እንዳይነቃበት ራቅ ብሎ ይጠቅሳታል፡፡ ሳቅ ካለች ‘መርሀ ግብሩ’ ግቡን መታ ማለት ነው። ከተኮሳተረች ደግሞ “ለአሁኑ አልተሳካም” አይነት ነገር ነው ማለት ነው። የፎቶሾፕ ፕሮፋይል ፒክቸር መለወጥ አያስፈልግ፣ ኢንስታግራም ምናምን ግራም አያስፈልግ… በቃ በጥቅሻ መልእክቱ ይተላለፋል፡፡
ዘንድሮ የሆነ ሰው ከርቀት አንድ ሁለቴ የሚጠቅሳት እንትናዬ፤ “ውይ ሲያሳዝን፣ የነርቭ ችግር አለበት መሰለኝ” ባትል ነው! አዎ የዚህም ፋሺኑ ተለውጧል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1703 times