Saturday, 13 January 2018 15:12

የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ የግምገማ ውጤት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ለአንድ ዓመት ይዘልቃል ብሎ ያወጣውን የፀጥታ ዕቅድ የአንድ ወር ቆይታ በተመለከተ ባለፈው አርብ ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ግምገማ የተደረገ ሲሆን የግምገማውን ውጤት አስመልክቶም ባለፈው ማክሰኞ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከአንድ ሰዓት በላይ በፈጀውና ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የፀጥታ ዕቅዱ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
በፀጥታ እቅዱ እንደ ችግር ከተጠቀሱት አንደኛው የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፤ባለፈው 1 ወር ውስጥ የዜጎችን እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶችን ማስቆም መቻሉን አስታውቀዋል። በዩኒቨርሲቲዎችም ከፍተኛ ግጭቶች መፈጠራቸውን አስታውሰው፣ ይሄን ግጭት ለማባባስም ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት መታየቱን ጠቁመዋል፡፡ ብሄርና ዘርን ማዕከል ያደረጉ ግጭቶች መፈፀማቸውንና በዚህም ህይወት መጥፋቱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዋና ዋና መተላለፊያዎች ላይ ያለው የፀጥታ ችግር መቀረፉን፣ ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ ባሉ አካባቢዎች አሁንም የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች እንዳሉ መገምገሙን አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡
በሽብርተኛነት የተረፈጁ ድርጅቶችንና በትጥቅ መንግስትን ለመጣል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን አርማ በመያዝ ባለቤታቸው ያልታወቁ ሰልፎች ሲካሄዱ እንደነበር ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ ሁኔታ አሁን  እየቀነሰ ቢመጣም በት/ቤቶችና በአንዳንድ አካባቢዎች ህገ ወጥ ሰልፎቹን ለማስቀጠል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ  ህግ የማስከበር ስራዎች እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡  
“በዘመናችን ተማሪ ተማሪን እስከ መግደል ተደርሷል፤ ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ተማሪዎች በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፤ በሂደቱ ውስጥም በአንዳንድ አካባቢዎች የዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር አካላትም መሳተፋቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ አክለውም የፀጥታ አካላት ሁኔታውን ባያረጋጉት ኖሮ ዘግናኝ እልቂት ይፈጠር ነበር ብለዋል - ሚኒስትሩ፡፡ ግጭቶቹ ያጋጠሙት በኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ በሚገኙ  18 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ነው ተብሏል፡፡  
በግጭቶቹ የተሳተፉትም በትምህርት ውጤታቸውና በስነ ምግባር የተባረሩ ተማሪዎች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን  በዚህ ሂደት የተሳተፉ ኦሮሚያ ላይ ብቻ 980 ተማሪዎች፣ ትግራይ ላይ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ 41 ተማሪዎች መገኘታቸውንና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል - ሚኒስትሩ፡፡ አሁን በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራ የተጀመረ ሲሆን ሁኔታዎች ወደ ግጭት የማያመሩበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯል ማለት አይቻልም፤ ቀሪ የቤት ስራዎች አሉ ብለዋል- ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፡፡   
በሌላ በኩል ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በአሶሳ፣ ቶጎ ጫሌ፣ ጋምቤላ፣ መተማ መስመሮች ላይ በተደረገ ፍተሻ 270 ክላሺንኮቭ፣ 200 ሽጉጦች፣ 65 ሺህ የክላሽ ጥይትና 1 ሺህ ያህል የመትረየስ ጥይት በቁጥጥር ስር ውሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንዳንዱ የጦር መሳሪያ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል የተያዘ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም አዋጅ ለማውጣት መንግስት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  
የኦሮሚያ ሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ላይ የተፈጠረውን ግጭት ጉዳይ በማብራሪያቸው ያካተቱት አቶ ሲራጅ፤ መጀመሪያ ግጭቱ ሲፈጠር የሁለቱ ክልሎች በጠየቁት መሰረት የፌደራል የፀጥታ አካላት በመሃል መግባታቸውንና የሁለቱ ክልል የፀጥታ አካላት ከአካባቢው እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በግጭት ተጠርጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር በማዋልና የህግ የበላይነት የማስከበር ሁኔታ በሚፈለገው መጠን አለመሄዱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ያሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በሚደረግ ጥረት የክልል አመራሮች የትብብር ማነስና ደንታ ቢስነት ታይቷል ብለዋል፡፡ በሶማሌ ክልል  ማዘዣ ከወጣባቸው 29 ተጠርጣሪዎች መካከል 12 ያህሉ ብቻ መያዛቸውን፣ በኦሮሚያ በኩል ማዘዣ ከወጣባቸው 26 ግለሰቦች ውስጥ ደግሞ 3 ያህሉ ብቻ መያዛቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት የተዘረፉ እንስሳት እንዲመለሱ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ሲራጅ፤ ከሃገር ሽማግሌዎች ጋርም ምክክሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል። የመጠጥ ውሃን በጋራ መጠቀም እንዲሁም  የገበያ ቦታዎችን የመጋራት ሁኔታ የተጀመረባቸው አካባቢዎችም እንዳሉ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም  አሁንም ግጭትና የሰው ህይወት መጥፋት በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰተ መሆኑን አልሸሸጉም፤ቀሪ የፀጥታ ማስበር ስራዎች እንደሚቀሩ በመግለጽ፡፡ መንግስት ይሄን ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ የቤት ስራውን እንደሚሰራም አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡
አስቀድሞ የፀጥታ እቅዱ ሲዘጋጅ ሁሉም የክልል ርዕሰ መስተዳደርና የፀጥታ አመራር በተገኙበት መሆኑን በመግለጫቸው የጠቆሙት አቶ ሲራጅ፤ ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብተው ከክልሉ መንግስት እውቅና ውጪ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉት የፀጥታ አካላትም በክልሉ እውቅና የገቡ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፌደራልና የክልል ፀጥታ አካላት በአንድ እዝ ስር በመግባባት ስራቸውን እየሰሩ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት የብሄር ተዋጽኦና ስብጥርን አስመልክቶ የሚቀርበውን ሃሜት በተመለከተም ከጋዜጠኞች የተጠየቁት አቶ ሲራጅ፤ “በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም በሀገሪቱ ካለ ተቋም በላቀ ሁኔታ የሁሉንም ብሄረሰብ ውክልና የያዘው መከላከያ ነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡  
በትግሉ ወቅት ከነበሩት የተወሰኑ ተቀንሰው ከሁሉም ክልሎች የተውጣጣ ሰራዊት ተገንብቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ከህዝቡ ጋር የሚመጣጠን ውክልና አለ ብለዋል፡፡ ምናልባት መጠኑ አነስተኛ ሊሆን የሚችለው በአፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላና ሃረሪ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእነዚህም ክልሎች የሚፈለገው ደረጃ ላይ  ለማድረስ እየሰራን ነው ብለዋል - አቶ ሲራጅ፡፡
ብዙ ጊዜ እላይ ካሉ ጥቂት መኮንኖች ጋር ተያይዞ ቅሬታ እንደሚቀርብ ነገር ግን ከታች ባለው ክፍተት እንደማይታይ የገለጹት አቶ ሲራጅ፤ ይህንንም ለማስተካከል በየጊዜው አመራሮችን የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው፤ በዋናነት መታየት ያለበት ግን የሠራዊቱ አስተሳሰብና አመለካከት ነው ብለዋል፡፡ ሠራዊቱ የራሱን ሀገር ዜጎች በብሄር ለይቶ አያይም ሲሉም አክለዋል - ሚኒስትሩ፡፡

Read 998 times