Saturday, 13 January 2018 15:09

ቴዲ አፍሮ በባህር ዳር ስቴዲየም እሁድ ይዘፍናል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

 - “የኮንሰርት ጥያቄውን በታላቅ አክብሮት ተቀብለነዋል” - የክልሉ መንግስት
           - “ስለፍቅር፣ ስለአንድነት፣ ስለኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት ነው”

    “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን 5ኛ አልበሙን በቅርቡ ለህዝብ ያቀረበው ዝነኛው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት በጥምቀት ማግስት እሁድ በባህር ዳር እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
ድምፃዊው ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኘለትን “ኢትዮጵያ” አልበሙን ካወጣ በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን ኮንሠርት ለማዘጋጀት ለባህርዳር አስተዳደር ፅ/ቤት ያቀረበው የፍቃድ ጥያቄ፣ ያለ አንዳች ቢሮክራሲና እንግልት አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን የቴዲ አፍሮ ማናጀር አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ኮንሠርቱ በባህርዳር ከተማ አስተዳደርና በክልሉ መንግስት እውቅና ማግኘቱን የጠቆሙት የአማራ ክልላዊ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ኮንሠርቱ ስለ ሠላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ አብሮነትና ስለኢትዮጵያዊነት የሚቀነቀንበት በመሆኑ፣ የክልሉ መንግስት ጥያቄውን በታላቅ አክብሮት እንደተቀበለው አስታውቀዋል፡፡
ኮንሠርቱ ሊሠሩ የታቀዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች አካል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ንጉሡ፤ የባህርዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ኮንሠርቱ ይሣካ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ኮንሠርቱ በጥምቀት ማግስት፣ እሁድ ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም 80 ሺ ያህል ተመልካች በሚይዘው የባህርዳር ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን በኮንሠርቱ ላይ የባህርዳርና አካባቢዋ ነዋሪዎች፣ ከመላ ሃገሪቱ የሚመጡ የሙዚቃ አፍቃሪዎችና ዓለማቀፍ ቱሪስቶችን ጨምሮ ከ30 እስከ 40 ሺ የሚገመቱ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ጌታቸው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
አርቲስት ቴዲ አፍሮ በበኩሉ፤ በፌስ ቡክ ገፁ ስለ ኮንሠርቱ ባሰፈረው ማስታወሻ፤ “ወደ ሙዚቃው አለም ከገባሁበት በተለይም የመጀመሪያ አልበሜ ከሆነችው ‹አቡጊዳ› ጀምሮ በቅርብ እስካሣተምኩት… ኢትዮጵያ አልበሜ ድረስ ከፍተኛ ፍቅር የለገሠኝን የሙዚቃ አፍቃሪ ለማስደሰት ከአቡጊዳ ባንድ ጋር ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ሲሆን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን ለመገናኘት ያብቃን” ብሏል፡፡
ለኮንሠርት ጥያቄው ፍቃደኝነታቸውን በመግለፅ ትብብር ላደረጉለት ለአማራ ክልላዊ መንግስት፣ ለባህርዳር ከተማ አስተዳደር ም/ቤት እና ለባህርዳር ከተማ ወጣቶች ምስጋናውን አቅርቧል- አርቲስቱ፡፡
የኮንሰርቱ መግቢያ ዋጋ ለመደበኛ 350 ብር፣ ለቪአይፒ 1 ሺህ ብር መሆኑን የድምፃዊው ማናጀር ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ቴዲ አፍሮ ለኮንሰርቱ ምን ያህል እንደተከፈለው ከመግለፅ ግን ተቆጥበዋል፡፡
በሌሎች የክልል ከተሞችም ተመሣሣይ ኮንሰርት የማቅረብ እቅድ እንዳለ ጠቁመውም፣ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ በዝርዝር እንደሚገለፅ አስታውቀዋል አቶ ጌታቸው፡፡
የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በባህርዳር እንዲካሄድ መፈቀዱን አስመልክቶ አድናቂዎቹ በማህበራዊ ሚዲያዎች ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ ለኮንሰርቱ ፍቃድ መሰጠቱ እንዳስደሰተው የገለፀው በላይ ማናዬ፤ “የደስታዬ ምክንያት በሀገርህ ስራህን በተደጋጋሚ ለወገናችን ለማቅረብ ጠይቀህ መከልከልህ አግባብ እንዳልነበር ስለምገነዘብ ነው” ብሏል፡፡
በቃሉ ይልማ የተባለ የባህር ዳር ነዋሪ በበኩሉ፤ ቴዲ አፍሮን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ኮንሰርቱን ለመታደም ሲጓጓ እንደነበር ገልፆ፤ “ጥር 13 እስኪደርስ እንቅልፍም አይወስደኝ” ሲል በፌስቡክ ገፁ አስፍሯል፡፡ ዮናታን ጌታቸው የተባለ የአርቲስቱ አድናቂ እንዲሁ ኮንሰርቱን ለፈቀደው የክልሉ መንግስት ምስጋናውን አቅርቦ የተለያየ አመለካከትን የማስተናገድ ባህል መለመድ አለበት ብሏል፡፡
አርቲስቱ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ያዘጋጀው የአልበም ምረቃ ስነ ስርአት “ፍቃድ ያስፈልገዋል” በሚል መከልከሉ የሚታወቅ ሲሆን በተደጋጋሚ ያቀረበው የኮንሠርት ማቅረብ ጥያቄም እንዲሁ በተደጋጋሚ መከልከሉ የሚታወስ ነው፡፡

Read 9084 times