Saturday, 13 January 2018 15:05

ሁለት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 14 የሽብር ፍርደኞች ከእስር ተፈቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   “የተፈታነው የእስር ጊዜያችንን ጨርሰን እንጂ በምህረት አይደለም”

    ከሙስሊም ጉዳዮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል ተፈርዶባቸው የነበሩ ጋዜጠኛ ዳርሠማ ሶሪና ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድን ጨምሮ 14 የኮሚቴው አባላት የፍርድ ጊዜያቸውን አጠናቀው ሰሞኑን ከእስር ተለቀዋል፡፡
እስረኞቹ የተፈቱት በቅርቡ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሣለኝ፤ ለተሻለ ሃገራዊ መግባባት የታሰሩ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች በምህረት ወይም በይቅርታ መንግስታቸው እንደሚፈታ ከመግለፁ ጋር ተያይዞ እንዳልሆነ ተገልጿል።
“የተፈታነው በይቅርታ ወይም በምህረት አይደለም፤ ፍርዳችንን ጨርሰን በአመክሮ ነው” ያሉት ተፈቺዎቹ፤ ከእስር እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈፀመባቸው ተናግረዋል፡፡  ከእስር ሊፈታ ቀናት ሲቀሩት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ድብደባና በሠንሰለት የመታሠር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመበት የገለፀው ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድ፤ ድርጊቱ የተፈፀመበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢህአዴግ አመራሮች የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ ባሉ ማግስት እንደሆነ ጠቁሟል።
እነ ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድን ጨምሮ 20 ግለሰቦች፣ ከ3 አመት በፊት ክስ የተመሠረተባቸው፤ የሽብር እንቅስቃሴ ተሣታፊ ሆናችኋል እንዲሁም የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በእነ አቡበከር አህመድና በእነ ኤልያስ ከድር መዝገብ ያሉ ተከሳሾችን በሃይል ለማስፈታት ተንቀሳቅሳችኋል በሚል ነበር፡፡
ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድ በበኩሉ፤ ህገ ወጥ ሚዲያ ላይ ሠርተሃል የሚል ክስም ቀርቦበት እንደነበርና በኋላ ሲጣራ፣ የሚሠራበት የሚዲያ ተቋም ህጋዊነቱ በመረጋገጡ፣ በሽብር ክሱ ጉዳዩ እንደቀጠለ ለአዲስ አድማስ አስረድቷል፡፡ የአቃቤ ህግን ክስ አንከላከልም ማለታቸውን ተከትሎ ፍ/ቤቱ በተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሣኔ መስጠቱን ያስታወሰው ጋዜጠኛ ካሊድ፤ 5 ዓመት ከ6 ወር እስራት ተፈርዶበት እንደነበርና በኋላም ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠይቀው፣ የእስር ጊዜያቸው እንደተቀነሠላቸው ይገልፃል፡፡ አብዛኞቹ ተከሳሾችም በይግባኝ ጥያቄያቸው ከ3 ዓመት እስከ 4 ዓመት ከመንፈቅ የሚደርስ የእስር ቅጣት ቅነሣ  እንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሁለት አመት ከ11 ወር ከታሰረ በኋላና የአመክሮ ጊዜው ከ1ወር በላይ አልፎ መፈታቱን የጠቆመው ጋዜጠኛ ካሊድ፤ መንግስት እስረኞችን ለመፍታት ከመወሰኑ ጋር የኛ ጉዳይ አይገናኝም ብሏል፡፡ በመዝገቡ ተከስሰው ከነበሩ 20 ግለሰቦች መካከል አንደኛዋ አስቀድማ በዋስትና ስትፈታ፣ 8 ግለሰቦች ከዝዋይ፣ እነ ጋዜጠኛ ካሊድን ጨምሮ 6 ግለሰቦች ከቃሊቲ መፈታታቸውንና የቀሩት 5 አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ ካሊድ መሃመድ በ2004 ዓ.ም ከሚሰራበት “ሬዲዮ ቢላል” ጋር በተያያዘ ታስሮ በ7 ሺ ብር ዋስ መውጣቱም ታውቋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ከ1987 ጀምሮ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዲሁም እስከታሰሩበት ጊዜ ድረስ በ “ቢላል” ሬዲዮ ላይ ሲሠሩ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 5545 times