Print this page
Saturday, 13 January 2018 15:00

የሰዓሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ለመንግስት ጥሪ አቀረቡ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

  ውሳኔው በአሜሪካ ቅሬታ መፍጠሩ ታውቋል

         · “ላለፉት 15 ቀናት ህዝቡ ቤተክርስቲያኗን 24 ሰዓት እየጠበቀ ነው”
         · የደብሩ ሂሳብ ሹም ህዝቡን በሽጉጥ አስፈራርቷል ተባለ
          
    የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ማሪያምና የቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል ምዕመናን፤ በደብሩ ለተከሰተው ችግር መንግስት ጣልቃ ገብቶ እልባት እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የችግሩ ዋና መንስኤ በደብሩ አስተዳዳሪ፣ በደብሩ ሂሳብ ሹምና የቁጥጥር ባለሙያ እየተፈፀሙ ያሉ ህገ ወጥ አሰራሮች መሆናቸውን ምዕመናኑ ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት ጽ/ቤት አቤቱታቸውን ባቀረቡት አቤቱታ አመልክተዋል፡፡
በደብሩ በዋናነት እንደ ችግር የተጠቀሱት ነጥቦች፡- ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን ባወጣው ህግ መሰረት፤ አንድ አጥቢያ የሚመራው ከምዕመናን፣ ከካህናትና ከሰንበት ት/ቤት ተውጣጥቶ በተመረጠ ሰበካ ጉባኤ ቢሆንም ደብሩ በተለይ ከ2006-2008 ዓ.ም የደብሩ አስተዳዳሪዎች በህዝብ ተሳትፎ የተመረጠውን ህጋዊ ሰበካ ጉባኤ በመበተን፣ ያለሰበካ ጉባኤ በምክትል ሊቀ መንበር ብቻ ሲመራ መቆየቱ፣ የቤተ ክርስቲያኑ የገንዘብ አገባብና አወጣጥ ግልፅነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ ላለፉት አራት ዓመታት ምንም አይነት የሂሳብና የስራ ሪፖርት ቀርቦ አለማወቁ፣ በቤተ ክርስቲያኑ እየተከናወነ ያለው ልማት በቃለ አዋዲው መሰረት የልማት ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ በዕቅድና በሥርዓት ሊሰራ ሲገባው ከህግ ውጭ በአስተዳደር ኃላፊነት ላይ በሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ግልፅነት በጎደለው መንገድ እየተሰራ መሆኑ፣ በደብሩ እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች ህገ ወጥና ከቤተ ክርስቲያኗ ማስተር ፕላን ውጭ ከመሆናቸውም በላይ የቤተ ክርስቲያኑን ገፅታ እያበላሹ መሆኑን  ምዕመናኑ ይገልፃሉ፡፡
 የቤተ ክርስቲያኗ የቦታ ይዞታ ሰባካ ጉባኤ በሌለበትና ግልጽነት በጎደለው መንገድ በድብቅ ለግለሰቦችና ለተለያዩ ድርጅቶች ለረጅም ዓመታት በኪራይ መልክ እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ምዕመናኑ፤ ይሄ አካሄድ በደብሩ ለአንድ ዓመት ብቻ በውል የሚሰጠውን የኪራይ አሰራር በግልፅ የሚፃረር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪና ሌሎች ኃላፊዎች በቤተ ክርስቲያን ከተቀመጠላቸው ስልጣንና ከቃለ ዓዋዲ ውጭ ያለ መመሪያ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውርስ ያገኘችውንና በስሟ ካርታ የወጣለትን ጉርድ ሾላ አካባቢ የሚገኝ 169 ካ.ሜ ስፋት ያለው መሬት ያለ አግባብ በመሸጥ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት አባክነዋል ሲሉም ምዕመናኑ ይከሳሉ፡፡ በሌላ በኩል በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተገነቡት ሱቆች በህጋዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኗ ገቢ ሊያስገኙ ሲገባ፣ በካቴድራሉ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ሱቆቹን በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቸው ስም በመቀራመትና ተከራ በማስመሰል ለግል ጥቅም በማዋል ላይ መሆናቸውን ምዕመኑ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የደብሩ አስተዳዳሪ በቢሯቸው 285 ሺህ ብር የሚያወጣ ጃኩዚ፣ እጅግ ዘመናዊ አልጋ፣  በዘመናዊ እቃዎች የተደራጀ ማዕድ ቤት መገንባታቸውን የገለፁት ምዕመናን፤ በዚህም ቢሮ ሳይሆን ሆቴል መምሰሉ የቤተክርስቲያኗን ህግና ሥርዓት ይጋፋል ብለዋል አስተዳዳሪው፡፡ በህዝብ ሲጠየቁም “ለእኔ ሳይሆን ቅዱስ ፓትሪያርኩ ሲመጡ የሚያርፉበት ጭምር ነው” በማለት ራሳቸውንና ህዝባቸውን በህግና በስርዓት የሚመሩትን ፓትሪያርክ፣ በህዝብ ለማስጠላት ሙከራ አድርገዋል ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መላዕከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሀን፣ የቤተክርስቲያኗን አገልጋዮች “በ40 ቀን ውስጥ የትዳር አጋር ፈልጋችሁ ካላገባችሁ እርምጃ ይወሰድባችኋል” በማለት አገልጋዮችን ጭንቀት ውስጥ በመክተት ለችግር መዳረጋቸውንም ምዕመናኑ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የአካባቢው ምዕመን ተቃውሞ ማንሳቱን ተከትሎ፣ ሃላፊዎቹ የወርቅ መስቀሎችንና ንዋየ ቅድሳትን ከግምጃ ቤት ወደ ግል መኖሪያ ቤታቸውና ቢሯቸው አሽሽተዋል የሚሉት ምዕመኑ፤ ተጨማሪ ዘረፋን ለመከላከል የዋና አስተዳዳሪውን፣ የሂሳብ ሹሙንና የቁጥጥር ሰራተኛውን ቢሮ ከታህሳስ 20 ቀን 2010 ጀምሮ በማሸግ፣ ላለፉት 15 ቀናት ህዝቡ በፈረቃ ቤተክርስቲያኑን ለ24 ሰዓት እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
 ፖሊስ  ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን እንዲመረምር ቢጠየቅም ህግ አይፈቀድልኝም በማለት ጣልቃ ሳይገባ በመቅረቱ ህዝቡ ቢሮዎቹን ለማሸግ መገደዱን የጠቆሙት ምዕመናን፤ ቢሮዎቹ የታሸጉ ዕለት ሂሳብ ሹሙ ከቢሮ እንዲወጡ ሲጠየቁ፣ ሽጉጥ በማውጣት ህዝቡን እንዳስፈራሩ ገልፀው፣ የዛኑ ዕለት ማታ ዋና አስተዳዳሪው መኪና በሀይል እያበረሩ ቤተክርስቲያን በመግባት፣ ቢሯቸውን ሊከፍቱና እቃ ሊወስዱ ሲሞክሩ ምዕመናን ተሯሩጠው በመያዝ በሰላም ከግቢው እንዲወጡ ቢጠየቁም አሻፈረኝ በማለታቸው፣ በወጣት ምዕመናን መጠነኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አዲስ አበባ አገረ ስብከት በተለያየ ጊዜ ሄደን ከቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ አገረ ስብከት፣ ከምዕመናንና ከመንግስት ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ እንዲጣራ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም ያሉት ምዕመናን በአሁኑ ወቅት የካቴድራሉ ዋና አስተዳደር የሆኑት መላዕከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሀን፣ ዋና ፀሐፊው ሊቀ አዕላፍ ዕፁብ የማነ ብርሀንና ሂሳብ ሹም ሊቀ ትጉሀን ዘርዓብሩክ አብርሀ ከሀላፊነታቸው እንዲነሱ፣ በቀጣይም ምዕመናን አቤቱታ ያቀረቡባቸውን ችግሮች አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም፣ ያለ ህግና ያለ ሰበካ ጉባኤ ትዕዛዝ በዝግ አዳራሽ የተቋቋመው ህገ-ወጥ ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ፣ በቃለ አዋዲው መሰረት አዲስ እንዲመረጥና የውጭ አዲተር ተቋቁሞ፣ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ገቢና ወጭ ኦዲት እንዲደረግ ሲሉ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ይህንንም ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ ይመለከታቸዋል ለተባሉ 21 መሥሪያ ቤቶች በግልባጭ አሳውቀዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ዋና አስተዳዳሪ መምህር ጎይቶም ዘንድ በተደጋጋሚ ብንደውልም “ስብሰባ ላይ ነኝ” በማለታቸው ሃሳባቸውን ለማካተት አልቻልንም፡፡ በተመሳሳይ የደብሩን አስተዳዳሪ በስልክ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ጥረታችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Read 4293 times