Saturday, 13 January 2018 14:58

ህጻናት ለውጭ ሀገር ጉዲፈቻ እንዳይሰጡ ተከለከለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከ4 ዓመት በላይ አነጋጋሪና አከራካሪ ሆኖ በቆየው የውጭ ሃገር የህፃናት ጉዲፈቻ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ህፃናት በጉዲፈቻ ለውጭ ሀገራት ዜጎች እንዳይሰጡ የሚከለክለውን አዋጅ ሰሞኑን አፅድቋል፡፡
የምክር ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ቢቢሲ እና ዘ ጋርዲያንን ጨምሮ በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን ሁነኛ መነጋገሪያ ያደረጉት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው እ.ኤ.አ በ2013 አሜሪካዊያን ጥንዶች ለማሳደግ የወሰዷትን ህፃን፣ በጭካኔ ከገደሉ በኋላ በተፈጠረ ቁጣ ነው ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፀደቀው አዋጁ፤ ህፃናትን ከእንግዲህ ለውጭ ሀገር ዜጎች በማደጎነት መስጠት እንደማይቻል የሚደነግግ ሲሆን ህጉን በሚጥሱት ላይ  ቅጣት ማስቀመጡም ታውቋል፡፡
ይህን አዋጅ ለመደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት በማደጎነት ለውጭ ሀገር እየተሰጡ ባሉ ህፃናት ላይ የሚደርሱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ከእንግዲህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ህፃናት በተወለዱበት ሀገር ቋንቋውን፣ ባህሉን እየተማሩ ብቻ ነው ማደግ የሚችሉት የተባለ ሲሆን ወላጅ አልባ ህፃናትም በሃገር ውስጥ የማሳደጊያ ማዕከል የሚያድጉበት እድል እንደሚፈጠር ተጠቁሟል፡፡ የሃገር ውስጥ የጉዲፈቻ ባህልም እንዲስፋፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በአዋጁ ላይ ሰፊ ሃተታ ያቀረቡት ቢቢሲ እና ፎክስ ኒውስ፤ ኢትዮጵያውያን ህፃናትን በማደጎነት በመውሰድ ጉልህ ድርሻ ባላት አሜሪካ ዘንድ ውሳኔው ቅሬታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ የማደጎ ልጆችን ከሚያሳድጉ አሜሪካውያን መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ልጆች እንዳሏቸው የተመለከተ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2017 ባሉት 18 ዓመታት ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ህጻናት  በማደጎነት ወደ አሜሪካ ተወስደዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ህጻናት ደግሞ በዋናነት ወደ ስፔን፣ ፈረንሳይና ጣሊያን በማደጎነት ሲወሰዱ ነበር ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ህፃናትን ለውጭ አገራት ዜጎች በማደጎነት በመስጠት ከሚታወቁ  አስር የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረችም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡   

Read 1851 times