Saturday, 06 January 2018 13:12

“ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የከፋው የደህንነት ስጋት ተጋርጦብናል” - የጃፓኑ ጠ/ ሚ ሺንዞ አቤ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ጃፓን በታሪኳ ከፍተኛውን የ46 ቢ. ዶላር ወታደራዊ በጀት አጽድቃለች

    የሰሜን ኮርያ ጸብ አጫሪነት ጃፓንን ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በታሪኳ አይታው የማታውቀው እጅግ የከፋ የደህንነት አደጋና ስጋት እንደጋረጠባት የገለጹት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፤ዜጎችን ከጥፋት ለማዳን ሲሉ የጦር ሃይላቸውን በተለየ ሁኔታ እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡
“እየተባባሰ የመጣው የሰሜን ኮርያ ጦር ናፋቂነት፣ አገሬን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አይታው በማታውቀው እጅግ የከፋ የደህንነት ስጋት ውስጥ ከትቷት ይገኛል፤ የህዝቤን ህይወትና ሰላማዊ ኑሮ ከሰሜን ኮርያ ሊቃጣ ከሚችል ጥቃት ለመታደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጽናት እቆማለሁ!” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ - ሮይተርስ እንደዘገበው፡፡
ሰሜን ኮርያ፤ ጃፓንና አለማቀፉ ማህበረሰብ የያዘውን የሰላማዊ መንገድ አቅጣጫ እያሰናከለችና በጸብ አጫሪነት አመሏ አካባቢውን ውጥረት ውስጥ እየከተተች መቀጠል አትችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጃፓን የሰሜን ኮርያን ጥቃት ለመከላከል የጦር ሃይሏን ከመቼውም ጊዜ በተለየ እንደምታጠናክር መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአካባቢው አገራት በሰሜን ኮርያ እምቢተኝነትና ጦር ጠማኝ አቋም ሳቢያ የገቡበት ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱ ያሳሰበው የጃፓን መንግስት፤ባለፈው ወር ላይ ለጦር ሃይሉ 46 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ወታደራዊ በጀት ማጽደቁንና ይህም በአገሪቱ ታሪከ ከፍተኛው እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
የተመድ ማዕቀብና አለማቀፉ ማህበረሰብ ማስጠንቀቂያ ቅንጣት ታህል ድንጋጤ ያልፈጠረባት ሰሜን ኮርያ፤፣  በተለይም ባለፈው መስከረም ወር ላይ ስድስተኛውንና ትልቁን የሚሳኤል ሙከራ ማድረጓንና በህዳር ወርም አሜሪካን መምታት የሚችል የረጅም ርቀት ድንበር ተሸጋሪ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወኗን በይፋ ማስታወቋን ተከትሎ በአካባቢው አገራት የነበው ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1397 times