Print this page
Saturday, 06 January 2018 12:43

በዓልና ኪስ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

 እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!
              
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“አጅሬው ባዶ እጅህን መጣህ?”
“ባዶ እጅህን መጣህ ማለት ምን ማለት ነው?”
“በጉስ የታለ?”
“የትኛው በግ፣ አደራ የሰጠሽኝ በግ አለ እንዴ?”
“በአንተ ቤት አሹፈህ ሞተሀል፡፡ ዓመት በዓልን ያለ በግ ልናልፍ ነው…”
“በቃ በሚቀጥለው ዓመት በዓል እንገዛለና…
ምናምን ተብሎ የሚነሳው ጭቅጭቅ፣ ባልና ሚስትን ለወራት ሊያኳርፍ ይችል ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ሳይለወጥ አይቀርም…
“ገና ስገባ ምነው እጅ፣ እጄን አየሽ?”
“አይ ድንገት ተሳስትሀ በግ ይዘህ መጥተህ እንደሁ ብዬ ነው፡፡”
“እውነት! ኑሮ ራሱ ሳር ያጣች በግ አድርጎኛል በግ ልጎትት! እንደውም ምን አለ በዪኝ … በሚቀጥለው በዓል በጉ እኔን እየጎተተ ባይመጣ!”
“ዘንድሮ ለማንም ስጦታ አልሰጥም” ሲል ነበር፣ አንድ የምናውቀው ሰው፡፡ ሳይቸግረው በተለይም ገና በመጣ ቁጥር ለተወሰኑ ቤተዘመዶቹና ጓደኞቹ ይቺንም፣ ያቺንም ስጦታ እየገዛ መስጠት አስለምዶ ነበር፡፡ ዘንድሮ አይደለም ለስጦታ ለታክሲም እየቸገረ ነው፡፡
የስጦታ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለሴት ጓደኛው ስጦታ ሊገዛላት የሆነ ሱቅ ይሄዳል፡፡ ባለሱቋንም፣
“ለሴት ጓደኛዬ ስጦታ ልሰጣት እፈልጋለሁ። ምን ብሰጣት የምትደሰት ይመስልሻል?”  ሲል ይጠይቃታል፡፡
“ትወድሀለች?” ትለዋለች፡፡  
“አዎ፣ እንደምትወደኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡”
“እንግዲያው ምንም ነገር ብትሰጣት ደስ ይላታል፡፡”
እናማ…“ለእኔ የሚሰጠኝ ስጦታ ይሄ ነው ወይ!” ብላ ሱናሚ የምታስነሳ ጓደኛ ካለቻችሁ ‘ፍቅሩ’ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል ማለት ነው! የእውነት ግን የወደደ ሰው ምንም ነገር ቢሰጡት ደስ ይለዋል! እንደውም ብዙዎቻችን የመዋደዱን ነገር የምንመዝነው በስጦታው ውድነት ሳይሆን ይቀራል!
ስለ ስጦታ አንድ እንጨምርማ…ሴትዮዋ ባሏ ሁልጊዜ ስለሚያመሽ ዘወትር ትበሳጫለች፡፡ ነገሩ ሁሉ የማትችለው ደረጃ ላይ እየደረሰባት ነበር። ገና ሊደርስ አካባቢ አንድ ጓደኛዋ እንዲህ ብላ ትጠይቃታለች፡-
“ለልጆችሽ ለገና ስጦታ ምን ትሰጫቸዋለሽ?”
እሷም እንዲህ ብላ ትመልሳለች…“አባታቸው በዋዜማው ማታ አምስት ሰዓት ላይ ቤት ሳይገባ ካመሸ፣ ለልጆቼ የምሰጣቸው ስጦታ አዲስ አባት ነው” ብላ አረፈችው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የዘንድሮ የበዓል ገበያ ቀዘቀዘ እንዴ?  ኤግዚቢሽን ማእከሉም የገበያ ውርጭ የመታው ይመስላል… ጋዜጦች ላይ እንዳነበብነው፡፡ ሹሮ ሜዳም የባህል አልባሳት ገበያ የቀዘቀዘ ይመስላል…ሬድዮ ላይ እንደሰማነው፡፡ ከመገናኛ ብዙኃኑ ይልቅ የሚነግረን ሁነኛ ምንጭ አለን፣ ኪሳችን! … እጃችንን በከተትን ቁጥር ጠብታ ውሃ የሌለበት በርሜል ውስጥ የከተትነው የሚመስለን ኪሳችን!
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል……ኑሮ ከባድ ነው፡፡ በበዓል ዋዜማ እንደዛ ማለቱ ጥቁር ምላስ የሚያሰኝ ቢሆንም…እውነቱ ግን የወጪ ነገር በጣም፣ እጅግ በጣም ከባድ ሆኗል። እርስ በእርሳችን ስናወራ “ሰዉ ግን እንዴት ነው የሚኖረው!” እንባባላለን፤ ግራ አየገባን፡፡ ለነገሩ ብዙም ምስጢር የለውም…ሰዉ የሚኖረው እንደ እኛ ነዋ! እንደ እኛ የጓዳውን በጓዳ ሸፍኖ፣ በአደባባይ ግን መልኩን በአፍተርሼቭና በሻዶ አሳምሮ፣ የደላው መስሎ ነዋ የሚኖረው!
ስሙኝማ…ቀደም ባለው ጊዜ በዓል በመጣ ቁጥር ሰዋችን ያለ የሌለውን ያራግፍ ነበር፡፡ አሁንም ብዙ ቀላል የማይባል እንደዛ አይነት ሰው አለ። ግን አብዛኛው ሰው እንዴት ብሎ! አንደኛ ነገር እንደዛ የሚያሰኝ ፍራንኩም ከየት መጥቶ፣ ሁለተኛ ነገር… “አበዳሪ ወይ ተበዳሪ ቀድሞ ይሞታል” በሚል ከዘመድ፣ ጓደኛ እንዳይበደር ሁሉም ገንዘብ የሚሰጠው ፈላጊ ነው፡፡ እዛኛውም ቤት ችግር አለ፡፡
በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ የደላውም መአት ነው፤ ገንዘቡን ምን ላይ እንደሚያደርግ ግራ የገባው፣ ገንዘብ የሚያስገኘውን ነገር ሁሉ አግኝቶ ስለጨረሰ… አለ አይደል… ‘ኑሮ የሰለቸው’ አለ… እዚቹ ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ እኔ የምለው…ዘንድሮ የብዙ ባለገንዘቦች አኗኗር…አለ አይደል…አገሪቷ አንድም ሰው ከድህነት ወለል በታች ያለባት አይመስልም! በአደባባይ ገንዘብ የሚበተንባቸውን ነገሮች ስናይ… “ይሄ ሁሉ እዩልኝ ያስፈልጋል!” እንላለን፡፡ እናም ገና ለገና የገንዘብ ቦርሳችን ስለወፈረ ዘላለሙን እንደደለበ ይኖራል ብሎ ማሰቡ ልክ አይሆንም፡፡ ለቀሪውና ላልተመቸው ወገን ማሰብም ያንን ሰው የሚያሳጣው ምንም ነገር አይኖርም፡፡
በነገራችን ላይ…‘የወንድምህ ጢም ሲላጭ ጢምህን ውሀ አርስ’ የሚሏት ነገር አለች… ያንተም ጢም ሊላጭ ይችላልና፡፡ ብዙዎቻችን ያኛውን ቤት ዳዋ ሲመታው፣ የእኛ እንደሞላ የሚከርም ይመስለናል፣ የዛኛው ቤት መሶብ ፍርፋሪ ሲጠፋበት የእኛ መሶብ እንደሞላ የሚኖር ይመስለናል፣…እዛኛው ቤት በመከራ በቀን ሁለቴ ሲበላ እኛ ቤት ለዝንተዓለም በቀን… አለ አይደል... ከተፈለገ ሰባቴም፣ ከተፈለገ አስሬም መመገብ የሚቻል ይመስለናል፡፡ ብቻ ሁልጊዜም ያኛው ቤት የሱናሚ አቅም ባለው የችግር አውሎ ነፋስ ሲመታ፣ የእኛን ቤት ስስ ወረቀት የሚያነቃንቅ ነፋስ እንኳን የሚነካው አይመስለንም፡፡ እኛ ሀገር ውድቅት ቅርብ፣ በጣም ቅርብ ነች፡፡
እግረ መንገዴን የሆኑ የምግብ ዝግጅቶች ስናይ ወይ ስለ ምግብ ዝግጅት ስንሰማ የሚመክሩን ምክሮች አሉ …ለጠቅላላ እውቀት አሪፍ ናቸው፡፡ ሰውነታችን በየቀኑ ከፕሮቲኑም፣ ከካርቦሀይድሬቱም ከቪታሚኑም ከምናምኑም የተወሰነ እንደሚያስፈልገው ሲነገረን ጥሩ ነው…ምንም እንኳን ‘ሰበር መረጃ’ ባይሆንም፡፡ እኛ እኮ የቸገረን የዶሮ ስጋ ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት እንዳለው ሳይሆን ዶሮዋን ቤታችን የምናስገባበት አቅም ነው። በየቀኑ የተለያዩ ፍራፍሬዎች ጭማቂ መጠጣቱ ለጤና ተስማሚ መሆኑን እስከ ዛሬ ምስጢሩ ሳይገለጽልን ቀርቶ ሳይሆን የቸገረን ፍራፍሬውን ቤታችን የምናስገባበት አቅም ነው፡፡
በየቴሌቪዥን ጣቢያው የተለያዩ የምግብ አዘገጃጀቶች ማየታችን አሪፍ ነው…በነገራችን ላይ ኩችናዎቹና ማብሰያ እቃዎቹ ራሳቸው ‘ሲያምሩ!’ ችግሩ ለብዙዎቻችን እንሞክርው ብንል ቢያንስ የአስር ቀን የቤት በጀታችንን ማወጣት ሊያስፈልገን ነው፡፡ አንዳንዱ ምግብ ላይ እኮ አትክልት ተራ ግማሹ የሚገባበት ነው የሚመስለው!
አንድ ሰሞን ከተማችን ውስጥ ‘ወተት ጠጡ’ ምናምን በሚሉ ትላልቅ፣ የሚያማምሩ ፖስተሮች ተጥለቅልቆ ነበር፡፡ ወተት ምን ያህል ለሰውነታችንና ለጤናችን ጠቃሚ እንደሆነ የሚነግሩን ማስታወቂያዎች ማለት ነው፡፡ እኔ የምለው…እኛ የወተት ጠቃሚነትን መች አጣነው! “ወተቱ ከጓዳ፣ እሸቱ ከጓሮ” እየተባለ የሚዘፈንባት አገር እኮ ነበረች! ከመሀላችን  “በየወረዳው ለአንድ ሰው በሳምንት ሁለት ሊትር ወተት በነጻ ይታደላል” ምናምን የሚል ማስታወቂያ የጠበቁ ቢኖሩ አይገርምም፡፡ እናም ለእኛ አቅም የሚመጥን ምክርና በአቅማችን ልንሞክረው የምንችለው የምግብ አሠራር ይቅረብልንማ!
በዓልና ኪስ የሚቀራረቡበትን ዘመን ያምጣልንማ!
መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1568 times