Print this page
Saturday, 21 April 2012 16:18

ትንሳዔ ለሁላችን!

Written by  ሳባውዲን ኑር
Rate this item
(0 votes)

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለእርሱ አልሆነም”

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1÷1-5

የገነትን ሥርዓት ያፈረሰው የመጀመሪያው አዳም የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጠቀ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነቱን በረከት ከመነጠቁ ጋር አብሮ ምድራዊ በረከቱም ኮሰመነ - ጫጨ፡፡ በመሪር ላቡና ወዙ አዳሪ ሆነ፡፡ እንዲያዛትና እንዲገዛት የተሰጠችው ምድር ጉልበቱንና ዕውቀቱን የምትፈትን ሆነች፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ የአዳም የስህተት ምርጫ ነበር፡፡

“ሞትን እንዳትሞቱ ከዚህች ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ” የሚል ምክርና ምርጫ ተነግሮት ነበር - አዳም፡፡

የበሰለን ፍሬ የመብላትና ያለመብላት አልነበረም ጉዳዩ - ለገዛ ፈጣሪ ኃይልን፣ ዕውቀትንና ፈቃድን የማስገዛትና ያለማስገዛት እንጂ፡፡ አዳም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ምርጫው መንፈሳዊና ምድራዊ ሞት ሆኗል፡፡ መንፈሳዊ ሞት ምድራዊውንም ሞት ያስከተለ አስከፊ መከራም ነበር፡፡

ሰው፤ ፈጣሪ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ አድርጐ የሰራው የእጁ ሥራ ብቻ ሳይሆን ከገዛ እስትንፋሱ ከመለኰቱ ሙቀት ከፍሎ የሰራውም ነበር፡፡ የጥበቡ ሁሉ መጨረሻ፣ የዕውቀቱ ማሟጠጫ ሰው ነበር ማለት ይቻላል፡፡

አዳም በእስትንፋሱ ሰማያዊ በአካሉ ምድራዊ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ምድርን እያስዋበ መልሶ መላልሶ እያበጃት፣ በመንፈሳዊ ኃይሉም እየበለፀገ በደስታ እንዲኖር የአምላክ አላማ የነበረው፤ ግን ተሰናከለ፡፡

ቢሆንም ሰው እንደሌሎቹ ፍጥረታት “ይሁን ይደረግ” በማለት የተፈጠረ አይደለም፡፡ አፈርን አድበልብሎ በአምሳሉ ከመሥራት አልፎም፣ ከእስትንፋሱ እስትንፋስ ተሰጥቶት የተበጀ በመሆኑ ዋጋው ከፍ ይላል፡፡

እንዲህ እንደዋዛ ለፈፀምከው ስህተት ዋጋህን ስትከፍል ኑር የሚሉት አልሆነም፡፡ ከምንም በላይ ውብና መልካም አድርጐ የሰራውን ሰውን በሲኦል ሊተው አልወደደም፤ እግዚአብሔር፡፡ ስለዚህ በአንዳች መንገድ አዳም እንደቀድሞው ንፁህ ሆኖ ሊኖር ይገባዋል፡፡ ከገባበት የስህተት እድፍ መንፃት አለባት፡፡

በእርግጥ ፈጣሪ አምላክ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ነውና ያለአንዳች ጣጣ መለኮታዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ “በቃ ዳግም ይህን ስህተት አትድገም፤ የሰራኸው ኃጥያት ያደረሰብህን መከራ አየኸው አይደል?” ብሎ በምክርና በተግሳጽ ብቻ ወደወጣበት ገነት ሊመልሰው ይችል ነበር፤ ይህን ለማድረግ ፈጣሪ ኃይሉም ሥልጣኑም በእጁ ነበር፡፡ ግና የሰውነቱን መራቆት ላወቀው አዳም እያዘነለት ነው የቆዳ ልብስ ሰፍቶ አልብሶ ከገነት የሸኘው፡፡

እግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣኑንና ኃይሉን በሥርዓት እንዲጠቀምበት ለራሱ ጭምር ሥርዓት ያበጀ አምላክ ነው፡፡ ለሥርዓቱ ቀናኢና መሐላ ያደረገ ነው፡፡ ሥርዓቱ ደግሞ ውብና ስህተት የሌለበት ነው፡፡ ለምሳሌ ምሽትና ንጋት፣ ክረምትና በጋ…የህዋ አካላቶችና ዑደታቸው… ሁሉን የሚመራበትና የሚያስተዳድርበት ሥርዓት አለው፡፡ ለመፍጠር ለመጠበብ የባተለውን ያህል “ለህጌና ለሥርዓቴ ታማኝ ነኝ” ይላል፡፡

አዳም የቱን ያህል ለኃጥያቱ ካሳ የሚሆን ለሥርየት የሚያበቃ ሥራ ሰራ ቢባል እንኳ ሥራዎቹ ሁሉ ተደምረው ለመዳን የሚያበቁ እንዳልሆኑና የአዳምም አቅም ይህን ማድረግ እንደማይችል አምላክ በተረዳ ጊዜ፣ የአዳምን ቅጣት ሊቀጣለት የበረከቱን መርገምት ሊሸከም ለራሱ ቃል ገባ - ወሰነ፡፡ “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሐለሁ” አለው፡፡

እግዚአብሔር አዳምን ሆኖ ዋጋ ሊከፍል የአዳም ተስፋ ሆነ፡፡ ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጠውን ፍቅርና ቦታ፤ የዳርቻውን ወሰን መገመት ይቻላል? ፈጽሞ!

ጊዜው ሲደርስ በፈጣሪ ዘንድ ተስፋና ቃል የሆነው እውነት ተወለደ፡፡ አምላክ ሰው ሆነ ሰውም አምላክ ሆነ! ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለተኛው አዳም ሆኖ ከድንግል ተወለደ፡፡

ከአዳም እስከ ክርስቶስ ባለው የዘመን ሐዲድ ሰው ሊድንበት ሊፀድቅበት የሚቻልባቸው በርካታ የፈጣሪ ህጐችና ትዕዛዛት በነቢያት በኩል ተላልፈዋል፡፡ ግና አልተፈፀሙም፤ ማንም የሚችላቸው አልነበሩም፡፡ ይልቁኑ ሐጢያትና ክፋት ከመንገሱ የተነሳ የጥፋት ውሃ ምድርና ያጠበበት እሳት ዘንቦ፣ ሺህዎችን ያጠፋበት ሁኔታ መከሰቱን ቅዱሳን መፃሕፍት ይገልፃሉ፡፡ ለእግዚአብሔር የተገዙ አንዳንድ ቅዱሳን አስከፊውን ዘመን በጽድቃቸው ቢሻገሩም፣ የእግዚአብሔር አላማ መላውን የሰው ልጅ ማዳን ስለነበር የእነርሱ ጽድቅ ለብቻው በቂ አልነበረም፡፡ በዚህ ፃድቃን በሳሱበት መልካም ሰዎች በሌሉበት አስቸጋሪ ዘመን ነው ክርስቶስ የመጣው፡፡

ሞራልና ሥነ ምግባር በተደመጠጠበት፣ የእግዚአብሔር ቤተመቅደሶች በአባይ ነጋዴዎች በተሞሉበት፣ ካህናት ፈረሳውያንና ሰድቃውያን ይህን የተዝረከረከ ሁኔታ ሊለውጡ ቀርቶ ራሳቸውም እየዳከሩበት ባሉበት ዘመን የመጣው ክርስቶስ፣ ተሰቅሎ ደሙን ለድነት ከማፍሰስ በተጨማሪ የምድሪቱን አጠቃላይ መልክ መለወጥና የሰውን ልጅ መንፈሳዊና ቁሳዊ አስተሳሰብ በአዲስ የመቀየርን ሚና መጫወት ነበረበት፡፡ ይህን ደግሞ ዕውን ለማድረግ መርህ ወይም ፍልስፍና ያሻ ነበር፡፡ የክርስቶስ ፍልስፍና አንድ ነበር - ፍቅር፡፡

እምነት ተስፋ ፍቅር ካሉ ሁሉንም ነገር ከማድረግ የሚያግደን እንደሌለ አስተማረ፡፡ ከምንም በላይ ግን ፍቅር ተራራውን ለማፍለስ፣ ሙታንን ለማስነሳት፣ አጋንንትን ለማባረር፣ በምድራዊ ኑሯችን ልናደርጋቸው የሚገቡንን የሚያስፈልጉንን ሁሉ እንድናደርግ በውስጣችን የታመቁትን ስጦታዎች አውጥተን እንድንጠቀም፣ እምነት ተስፋ ፍቅር መሣሪያዎች መሆናቸውን አወጀ፡፡ እርሱም ይህን የሚያደርገው እምነት ተስፋና ፍቅርን ተላብሶ መሆኑን ተናገረ፡

“ስለምን ትጠሩኛላችሁ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! ማዕበሉን ፀጥ በል በሉት ፀጥ ይላል” አለ፡፡ በውሐ ላይ ተራመደ፣ ከጥንት ፃድቃን ነፍስ ጋር በግላጭ ተነጋገረ፡፡ የቀን ሰራተኞች፣ ጐስቋሎችና ለፍቶ አዳሪዎችን ለክብሩ መረጠ፡፡ አለምን እንዲለውጡ መንፈስ ቅዱስን አልብሶ ሸኛቸው፡፡

እውነት ነው ቀራኒዮ ላይ የተሰቀለው ፍቅር ነው! ዛሬ የሰው ልጆች በሥራቸውና በጽድቃቸው ሳይሆን በደሙ የዳኑት ከፍቅር የተነሳ ነው፡፡ የዘመኑ የፈጣሪ ህግና ሥርዓት መጨረሻ ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር ሁሉ ተችሏል ሁሉ ይቻላል፡፡ በፍቅር ሞት ተችሏል - በፍቅር ትንሳዔም፡፡

ትንሳኤ ይሁን ለኑሯችን፣ ለስኬታችን! ትንሳዔ ይሁን ለአገራችን - በፍቅር አሜን!!

 

 

Read 2948 times Last modified on Saturday, 21 April 2012 16:25