Saturday, 06 January 2018 12:39

ስለ ኢህአዴግ መግለጫ ምን ተባለ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከ17 ቀናት ስብሰባ በኋላ ያወጣው መግለጫ ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት የነበረውን ያህል የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀ መናብርት በስብሰባው የተደረሰበትን ውሳኔ በዓይነቱ ልዩና ታሪካዊ ብለውታል፡፡ ሌሎችስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና የህግ ባለሙያዎች መግለጫውን በተመለከተ የሰነዘሩትን አስተያየት አሰባስቦ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

          “ህብረተሰቡ የሚጠብቀው ተግባራዊ እርምጃዎችን ነው”
             አቡበከር አለሙ (የቀድሞ የሙስሊሞች ጉዳይ መፅሄት አምደኛ)

   እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ችግር አንፃር፣ የኢህአዴግን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ ስጠባበቅና ስከታተል ነበር፡፡ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፣ ከ17 ቀናት ስብሰባ በኋላ ያወጣው መግለጫ፣ በአብዛኛው ከቀድሞው  የተለዩ ጉዳዮችን የያዘና መልካም ሆኖ ነው ያገኘሁት። ጥሩ ነው የምልበት ምክንያት አንደኛ፣ በሀገሪቱ የተደቀኑ ፖለቲካዊ ችግሮችን አምነዋል፡፡ ምናልባት በኔ አረዳድ ችግሮችን አምነው ሲቀበሉ፣ በኢህአዴግ ታሪክ የመጀመሪያው ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ፣ ለሀገሪቱ የውስጥ ችግሮች ጣታቸውን ወደ ውጪ ኃይሎች ከመቀሰር ይልቅ ዋነኛ ተጠያቂ ራሱ ኢህአዴግ፣ ከዚያም አልፎ የሥራ አስፈፃሚው እንደሆነ ማመናቸው ሌላው በጎ ነገር ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ችግሩ በመፈጠሩ መፀፀታቸውን በመግለጫቸው ማመልከታቸው፤ በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ለተፈጠረው ችግር መላ የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ መጠየቃቸውና ኃላፊነቱን እንወስዳለን ማለታቸው በጎ ነገር ነው፡፡ በአምስተኛ ደረጃ የተፈጠሩትን ችሮች አምነው፣ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ተቀብለውና ተፀፅተው፣ ይቅርታም ጠይቀው፣ ይሄን ጉዳይ ለማስተካከል በአደባባይ ቃል መግባታቸው፣ ከዚህ በፊት እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ሆኖም ግን በዋናነት ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው፣ ይህ በመግለጫው የተንፀባረቀው በሙሉ በተግባር ሲተረጎም ነው ሚዛን የሚያገኘው። ህብረተሰቡም ለመግለጫው ክብደት የሚሰጠው በተግባር ሲተረጎም ነው፡፡ ከዲሞክራሲ ስርአት ግንባታና ከልማት ጋር በተገናኘ በርካታ ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተግባራዊ ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ የመሳሰሉ ህገ መንግስቱ የደነገጋቸው መብቶች በሙሉ በተግባር ሊታዩ፣ ሊዳሰሱ በሚችል መልኩ መተግበር አለባቸው። ይሄ ካልሆነ ግን ያው እንደተለመደው መግለጫ ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ህብረተሰቡ አሁን የሚጠብቀው ተግባራዊ እርምጃዎችን ነው፡፡

--------
              “መግለጫው አዲስ ነገር አላመጣም”
                አቶ ተሾመ ተ/ሃዋሪያት (የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ)

   የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ፣ ከ17 ቀናት በላይ የሀገሪቱን ችግሮች ገምግሞ፣ መፍትሄ ለማስቀመጥ ያደረገው ስብሰባና በመግለጫው ላይ የተንፀባረቀው፣ ከተጠበቀው አንፃር፣ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የሀገሪቱን ችግር በቅጡ ያየና የተገነዘበ አይደለም፡፡ የመግለጫውን ይዘት ላየ፣ አንዳንድ ተስፋ የሚፈነጥቁ ነጥቦች ቢኖሩትም፣ በተለይ በዲሞክራሲያዊ መብቶች አከባበር፣ በመድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታና በመልካም አስተዳደር ረገድ ጠንካራ አቋም አልተንፀባረቀም። በ2008 ዓ.ም በጥልቀት ታድሰናል ተብሎ ከተሰጠው መግለጫ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ አንድም አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ ፕሬዚዳንቱ በ2009 ዓ.ም በፓርላማው ያደረጉት ንግግር ነበር፤ ያንን ንግግር እንኳ ገዥው ፓርቲ በቅጡ መሬት ማስረገጥ ያልቻለ ነው፡፡
 ከ17 ቀናት ስብሰባና ሀገሪቱ በቋፍ ላይ ባለችበት ወቅት፣ ይህ የተለመደ መግለጫ መውጣቱ፣ ወደ መፍትሄው አያደርሰንም፡፡ ለደረሰው ነገር በሙሉ ሥራ አስፈፃሚው ሃላፊነት እንደሚወስድ ከተገለጸ በኋላ ድርጅቶቹ ተገማግመው እርምጃ ይወስዳሉ ይላል፡፡ ይሄ የተምታታ ነገር ነው፡፡ አንዴ ሥራ አስፈፃሚው ኃላፊነት ወስዶ ይቅርታ ካለ በኋላ፣ ከብሄራዊ ድርጅቶች የምን የግምገማ ውጤት ነው የሚጠበቀው? በመድብለ ፓርቲ፣ በሲቪክ ሶሳይቲ ረገድ በመግለጫው የተጠቀሰው ወደ ተግባር የሚለወጥ ከሆነ መልካም ነው፡፡ በሚዲያው በኩል ግን ማስፈራሪያ ውስጥ ነው የተገባው፡፡ ይሄ መጪውን ጊዜ ለሚዲያው ፈታኝ ሊያደርገው ይችላል፡፡

---------

            “ኃላፊነት መውሰድ ያለ ተጠያቂነት የተንፀባረቀበት ነው”
              አቶ ተመስገን ዘውዴ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

    በግጭቶቹ የሰው ህይወት ከጠፋ፣ ሀገራዊ ውድመቶች ከደረሱ በኋላ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ተሰብስቦ ያወጣውን መግለጫና የደረሰውን ጥፋት ስናመዛዝን፣ ለደረሰው ጥፋትና ውድመት የሚመጥን መግለጫ አይደለም፡፡ ኃላፊነት የኛ ነው ከተባለ፣ ማን ነው ለዚህ ተጠያቂው? የሚለው ይከተላል፡፡ ኃላፊነት መውሰድ ከተጠያቂነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ዝም ብሎ በጅምላ፤ “እኛ ለዚህ ተጠያቂ ነን” ብቻ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የበርካቶች ክቡር ህይወት ጠፍቷል፡፡ ለዚህ ጥፋትና ውድመት ተጠያቂው በግልፅ ታውቆ፣ ለህግ ሊቀርብ ይገባ ነበር፡፡ እነሱ ግን  የሰለቸንን “ኃላፊነት እንወስዳለን” የሚል ነገር ነው እንደገና ያሰሙን፡፡ ህዝብ የሚጠብቀው ለዚህ ለደረሰው ጥፋትና ውድመት ተጠያቂ አካል ይፋ ተደርጎ፣ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ነው፡፡ አሁን ግን ተጠያቂነት አልተቀመጠም፡፡ እስካሁንም ተጠያቂ የሆነ አካል አላየንም፡፡ ህጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው አመራሮች ስለመኖራቸው ሰምተን አናውቅም፡፡
እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ያወያየኋቸው ሰዎች ያረጋገጡልኝም፣ ተጠያቂነት የሌለበት፣ የተሰለቸ አይነት መግለጫ መሆኑን ነው፡፡ በመግለጫው ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ እንወያያለን ተብሏል፡፡ ይሄ መልካም ቢመስልም ያው እንደተለመደው፣ በራሳቸው መስመር ውስጥ ያሉትን ሰዎች ብቻ ሰብስበው የሚያወያዩ ከሆነ ውጤት አልባ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የነበረው ልምድ እንደሚያሳየን፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ኢህአዴግ በሚያዘጋጀው ውይይት ላይ እንዲሳተፉ አይፈለግም፡፡ የራሱን አስተሳሰብ ሊያራምዱ የሚችሉ ሰዎችን ብቻ የማወያየት ልምድ ነው ያለው፡፡ የሚበጀው ግን የተለዩ ሃሳቦች ያላቸውን ሰዎች ማወያየት ነው፡፡ ይሄ ነው ውጤት ሊያመጣ የሚችለው፡፡ ለዚህች ሀገር ሰላምና ዲሞክራሲ መስፈን፣ የተለየ ሃሳብ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን ዜጎች፣ ወደ ጎን ትቶ፣ የተሰለቸውን አካሄድ የሚከተል ከሆነ፣ አዙሪቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ሃገር አንድነት የሚያስቡ ሰዎች ካሉ፣ ሰላምና አንድነትን ለማስፈን ጊዜው አሁን ስለሆነ፣ ስለ አገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ረገድ ሊተጉ ይገባል እላለሁ፡፡

---------


          “ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ብቻ በቂ አይደለም”
            አቶ ተክሌ በቀለ (ፖለቲከኛ)

    ይሄ መግለጫ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ከተሰጡ መግለጫዎች ብዙም ልዩነት የለውም። 17 ቀናት የፈጀ ስብሰባ ውጤትም አይመስልም። ምናልባት በሰፊው ተነጋግረው፣ ለህዝብ መግለፅ ያልፈለጉት ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ መግለጫ ላይ የተወሳሰበ ፖለቲካዊ ችግር እንዳለ ማመናቸው፣ በጎ ነገር ነው፡፡ ለችግሩም ኃላፊነቱን መውሰድ ያለብን እኛ ነን ብለው፣ የኢትዮጵያ ህዝብን ይቅርታ መጠየቃቸው፣ መረጋጋትንና የልብ ቀናነትን ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ችግር መኖሩን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ችግሮቹ ምንድን ናቸው? የችግሮቹ መንስኤዎችስ? የሚሉት ከእነ መፍትሄያቸው ነጥረው መውጣትና ከባለድርሻ አካላት ጋር መፍትሄ ለማበጀት መንቀሳቀስ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ከዚህ በፊቱ ይህን መግለጫ አውጥተው ተግባር ላይ ሳያውሉ መቆየት ደግሞ የበለጠ ጥሩ አይሆንም፡፡ ሌላው በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የታሰሩ ዜጎች በሙሉ መፈታት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ጥፋተኛው መንግስት ራሱ መሆኑን አምኗልና ነው፡፡   


------------


             “ግልፅ የችግሮች ትንታኔና መፍትሄ ያልተንፀባረቀበት ነው”
               አቶ በላይ ማናዬ (ጦማሪና ጋዜጠኛ)

    ሃገር እመራለሁ የሚለው አካል፣ ሃገሪቱ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ረጅም ጊዜ የፈጀ ስብሰባ ሲያደርግ፣ ምን አዲስ ነገር ሊወስን ይችላል የሚል ጉጉት ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የድርጅቱን ባህሪ በቅርብ ለሚከታተል ሰው፣ ችግሮችን አድበስብሶ በማለፍ የሚታወቅ ስለሆነ፣ የተለየ አዲስ ነገር  በግሌ አልጠበኩም፡፡ ሆኖም  ሀገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር፣ የተወሰነ ነገር መጠበቅ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በመግለጫው አብዛኛው ሰው የጠበቀውን ያገኘ አይመስለኝም፡፡
መግለጫውን ደጋግሜ ለማንበብ ሞክሬያለሁ። በእጅጉ ማድበስበስ የሞላበት፣ አዲስ ሃሳብ ያልተንፀባረቀበት እንዲያውም ጥልቅ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ያመላከተ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ግልፅ የችግሮች ትንታኔና መፍትሄ አላገኘሁበትም። አንዴ “ችግሮቹን ተረድተናል፣ ኃላፊነቱንም እኛ እንወስዳለን፤ ይቅርታም እንጠይቃለን” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “በጣም የሚያስጎመጅ የእድገት ተስፋ ጅማሮ ላይ ነን” ይላል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሚጋጩ ናቸው፡፡ ሌላው ኃላፊነት እንወስዳለን ይላል፡፡ ግን ኃላፊነት መውሰድ ማለት ምን ማለት ነው? ከኃላፊነት እንለቃለን ነው? በህግ ለመጠየቅ ዝግጁ ነን ማለታቸው ነው? ከመካከላችን ይሄን ችግር የፈጠሩ ሰዎችን ለይተን፣ በፍ/ቤት እንጠይቃለን ነው? እኒህን ዓይነት ጥያቄዎች የሚፈጥር መግለጫ ነው፡፡ የችግሮቹ መፍትሄዎች ብለው ያስቀመጧቸው ነጥቦች ደግሞ እስካሁን ለተፈጠረው ችግር መንስኤ የሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ መግለጫው፣ የሀገሪቱን ቁልፍ ችግሮች ያልተረዳና የሃሳብ ምክነት እንዳለ ጎልቶ የወጣበት ነው፡፡
ከመግለጫው አንዳንድ ይዘቶች በተለይ ሚዲያን በተመለከተ የተጠቀሱ ጉዳዮች ለበለጠ አፈና መዘጋጀታቸውንም ነው የሚያሳየው፡፡ “ፀጥታውን እናስከብራለን፣ ችግሩን እንቀለብሳለን” ሲሉ ጥያቄዎችን መመለስ ላይ ሳይሆን እርምጃ መውሰድ ላይ ለማተኮር መዘጋጀታቸውን ነው የሚጠቁመው፡፡ በአጠቃላይ መግለጫው፣ በቀጣይ የሚካሄደውን የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ አቅጣጫም ከወዲሁ ያመላከተ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

Read 2255 times