Saturday, 06 January 2018 12:34

ፀፀት፣ ይቅርታ፣ ማስጠንቀቂያና ብዥታዎች..... በኢህአዴግ መግለጫ

Written by  በታምራት መርጊያ
Rate this item
(1 Vote)

    የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ከታህሳስ 3 ቀን ጀምሮ ለ17 ቀናት ሐገሪቱ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ፣ ሰፊ ግምገማ ማካሔዱን   ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም  ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
የአቋም መግለጫው እንደሚያትተው፣ ድርጅቱ አሁን በሐገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ላለው ቀውስ ሙሉ ሀላፊነቱን እንደሚወስድ ጠቅሶ፤ ለችግሮቹ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ከፍተኛ አመራሩ ወይም ስትራቴጂክ አመራሩ እንደሆነም አምኗል።
“.....ድርጅታችን ኢህአዴግ የትግልና የለውጥ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት በማሽቆልቆል ውስጥ የቆየችውን አገር ለሩብ ምእተ አመት በእድገትና የለውጥ ጎዳና እንድትገሰግስ ያደረገውን ጥረትና የተመዘገቡትን ህዝባዊ ድሎች ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረጉም የተሰማውን ከልብ የመነጨ ፀፀት ይገልፃል...” ብሏል - ኢህአዴግ።
ድርጅቱ አክሎ እንደገለፀው፡- ”....ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከዚህ በመነሳት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መላ የአገራችን ህዝቦች በከባድ ተጋድሏቸው ያስመዘገቧቸውን ድሎች ጠብቆና አስፍቶ ለማስቀጠል ባለመቻሉ፤ እንዲሁም በድርጅታችን ውስጥም ሆነ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ልዩ ልዩ ችግሮችን በጊዜና በከፍተኛ የሃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ባለመቻሉ ለደረሰው ጉዳት ሙሉ ሃላፊነቱን ከመውሰድ በተጨማሪ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች ልባዊ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡”
ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ባካሔደው ግምገማ ላይ በመመስረት ስምንት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ አጣዳፊ ችግሮችን እየፈታ፣ ለዘላቂ ለውጥ መስራት እንዳለበት መወሰኑን ጠቁሞ፣ ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማስፈን እንዳለበት በማመን፣ “በየአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት፣ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት የማወክ እንዲሁም የሕዝቡን የዕለት ተለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ የቡድንም የተናጠልም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ይደረጋል..” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በአጠቃላይ ድርጅቱ እንደ ችግር ለየኋቸው በሚል ከጠቀሳቸው በርካታ ጉድለቶች መካከል  በአለፍ ገደም የተወሰኑትን እንመልከት፡-
በከፍተኛው አመራር ደረጃ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦት ስር መስደድ፣
መርህ አልባ ቡድናዊ ትስስር፤ በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነት ኢህአዴግና አባል ድርጀቶቹን የማዳከም ውጤት ማስከተሉ፣
የዴሞክራሲ መጥበብና አድርባይነት መስፋፋት፣
በርከት ባሉ የሐገሪቱ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት እየደፈረሰ፣ ሁከት የዕለት ተለት ክስተት እየሆነ መምጣት፣
የአስተሳሰብ ብዝሃነት በአግባቡ እንዲገለፅ የሚያደርግ ተጨባጭ ሁኔታ እየተዳከመ መምጣት፣
ችግሮችን በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ማስተካከል የሚገባው ድርጅቱ፤ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ያሳየው ዳተኝነት፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ችግር እንዲገጥመው ማድረጉን፣
የዴሞክራሲ ምህዳርን በማስፋት ረገድ ድርጅቱ ሊወስደው ይገባ የነበረውን እርምጃ ከመውሰድ አንፃር ሰፊ ክፍተት መኖር፣
ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁነኛ ድርሻ ካላቸው ተቋማት መካከል የሃገራችን ሚዲያና ፕሬስ በሚገባው ደረጃ ነፃነታቸው ተጠብቆ፣ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ የተደረገው እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣት፣
በዚህ ረገድ የታየው ዘገምተኛ ዕድገት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልልም ይሁን በፌዴራል ያሉ የህዝብ የሚዲያ አውታሮች፣ ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው የማይሠሩበት ሁኔታ እያመዘነ፣ የህዝቡን ሰላምና አብሮ የመኖር ገንቢ ባህል የሚሸረሽሩ ሰበካዎች የሚሰጥባቸው፣ ብሎም ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ አጥፊ ቅስቀሳዎች የሚካሄድባቸው እየሆኑ መምጣታቸው፣
አመራሩ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በመገንባትና በህገ መንግስታዊ ስርዓት ዙሪያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እየተገባው፣ የህዝብ የተደራጀ ሲቪል እንቅስቃሴን አለማጠናከር፣
በአገራችን መንግስታዊ ዴሞክራሲ ዋስትና የሚኖረው ከአዋጅ አልፎ ህዝብ በተደራጀና ንቁ አኳኋን ሲሳተፍና ሲጠቀምበት ቢሆንም፣በዚህ ረገድ የተደረገው እንቅስቃሴ፣ የሲቪል ማህበረሰቡ ተሳትፎ መሆን በሚገባው ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያስቻለ አለመሆን፣
የህልውና ጥያቄ የሆነውን መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴ፣ በአመራር ድክመት ምክንያት ለበርካታ ችግሮች መጋለጥ፣
የህዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማስፋት፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለማንገስና ውጤታማና ቀልጣፋ አስተዳደር ለመገንባት የተደረጉ ጥረቶች ያስገኙትን መልካም ፍሬ መጠበቅና ማስፋት አዳጋች ሆኖ መቆየቱ፣
በዚህ የተነሳ ከፍተኛ የህዝብ ምሬት መፈጠር፣
.የህግ የበላይነት የማስፈን ድክመት በመታየቱ፣ በሙስናም ሆነ በሌሎች ጥፋቶች ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችን በወቅቱና ህጋዊና አስተማሪ በሆነ መንገድ መጠየቅ ሳይቻል መቆየቱና  ዜጎች በህገ መንግስቱ ዋስትና ያገኙ መብቶቻቸውን የሚጥሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ፣ መሆን በሚገባው ደረጃ አለመፈፀሙ፣
የአፈፃፀምና የስነ ምግባር ችግሮችን አስተማማኝና ውጤታማ በሆነ መንገድ የማረምና የማስተካከል ጉድለት፣
ሃገራዊ ራዕይና የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን በሚያጠናክር መልክ በማስኬድ ረገድ ቁጥራቸው የማይናቅ ጉድለቶች በአመራሩ መፈፀሙን፣
ህዝበኝነት (Populism)፣
በህብረተሰባችን ዘንድ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ ልማታዊ አስተሳሰብና በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ አንድነት በማጠናከር ረገድ የተሰራው ስራ፣ መሆን የሚችለውን ያህል ውጤት ሳያመጣ መቅረቱ፡፡
--የሚሉ ጉድለቶችን ሥራ አስፈፃሚው መለየቱን ይጠቁምና፤ “ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች በተራዘመ ትግል የተገነባችውን አገር ለአደጋ ማጋለጥ የጀመሩት ጉድለቶች በዋነኛነት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ድክመቶች ናቸው” ሲል አፅንኦት ሰጥቶ ይገልፃል፡፡
በአጠቃላይ ይህ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ፤ በብዙ መልኩ ለትርጉም የተጋለጠና ብዥታን የፈጠረ እንደሆነ መግለጫውን ተከትሎ፣ የተለያዩ ወገኖች ከሰነዘሯቸው አስተያየቶች መረዳት ይቻላል፡፡
በዚህ ረገድ የበርካቶችን ትኩረት ከሳቡ የመግለጫው ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹን በናሙናነት ብንመለከት፤ ለምሳሌ እንደ ችግር ተለዩ ከተባሉት ጉድለቶች ውስጥ “መርህ አልባ ቡድናዊ ትስስር እና በግልጽነትና በመርህ ላይ ተመስርቶ ከመተጋገል ይልቅ መርህ አልባ ግንኙነት” ተብሎ የተጠቀሰው ጉዳይ፣ የየትኛውን ቡድናዊ ትስስር ለማመላከት እንደተሞከረና እንደተፈለገ፥ ይህ ጉድኝትና ትስስር በምን ዐይነት መልኩ እንደተከሰተ እንዲሁም ሊያመጣ የሚችለው ጉዳት ወይም ያመጣው ጉዳት ካለም የዚህ ጉዳት ምንነት በግልፅና በዝርዝር ባለመቀመጡ ምክንያት በርካቶች በራሳቸዉ መንገድ የየራሳቸውን ትርጉም እንዲሰጡት ተገደዋል፡፡
በሌላ በኩል “ሕዝበኝነት (Populism)” ተብሎ የተለየው ችግር፣ ኢህአዴግ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለየኋቸው ከሚላቸው ችግሮችና በአሁኑ መግለጫውም ከደገማቸው ድርጅታዊ ችግሮቹ መካከል በአይነቱ በአንፃራዊነት የተለየ ከመሆኑ አኳያ፤ ምን አይነት መልክ እንዳለው ተብራርቶ አለመቅረቡ፣ አሁንም ሕብረተሰቡን ግር እንዲሰኝ ያደረገ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በተጨማሪም በመግለጫው ላይ በጥቅሉ “በየአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት፣ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት የማወክ እንዲሁም የሕዝቡን የእለት ተለት እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉሉ የቡድንም የተናጠልም እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ይደረጋል” ተብሎ የተገለፀው የመፍትሔ አቅጣጫ እንዴትና በምን ዐይነት ሁኔታ የሚከናወን  እንደሆነ አሻሚነቱ አያጠራጥርም። ይሁንና ይኽ ሰላምን የማስከበር ሂደት የፀጥታ ሐይሎች በመጠቀም እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ፣ በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 51 የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባራት ንዑስ አንቀጽ 14 (ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሐገሪቱን መከላከያ ሰራዊት ያሰማራል) እና አንቀጽ 52 የክልል ስልጣንና ተግባር /ንዑስ ዐንቀጽ ሰ (ክልሉ የክልሉን የፖሊስ ሐይል ያደራጃል፣ ይመራል፣ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ያስከብራል) በሚለው አግባብ ላይ በመመስረት ይሁን ወይም በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት እንደሚደረገው፣ የፌዴራል የፀጥታ ሐይሎችን ወይም የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሐይሉን እንዲሁም የክልል የፀጥታ አካላትን በእዝ አስተዳደር ስር በማስገባት የሚከናወን ተግባር ይሁን በመግለጫው ላይ የተብራራ ነገር የለም። ከላይ ከተጠቀሱት ቢሆኖች ወይም አፅመ ታሪኮች (Scenarios) መሐል የኋለኛው የሚሆን ከሆነስ ዳግም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ ይሆን የሚለው ጉዳይም እንዲሁ ብዙዎች ላይ ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም። እንደሚታወቀው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካልታወጀ በስተቀር፣ የሐገሪቱ ገዢ ህግ የሚሆነው ህገ መንግሥቱ እንደሆነ ጥያቄ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም።
ሌላው ከዚህ መግለጫ ጋር ተያይዞ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ፣ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ መደረሱን ከመግለጹ ጋር ተያይዞ፤ ድርጅቱ ለወሰደው ሐላፊነት የሚወስደው ምን ዐይነት የተግባር አፀፋ እንደሆነ በግልፅ አልተቀመጠም። በዚህ ረገድ በግልፅ እንደሚታወቀው ለአንድ ጥፋት ሐላፊነት የወሰደ አካል፤ ወይ ለጠፋው ጥፋት ካሳ ይከፍላል፤ አለያም አጥፊው አካል ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣትን ይቀበላል። በመንግሥትም ደረጃ ቢሆን ለጥፋቱ ተጠያቂ የሆነው አካል ከመንግስታዊ ስልጣኑ ከመነሳት እስከ በህግ ተጠያቂ የመሆን ዋጋ ሊከፍል ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሐላፊነት መውሰዱ ቃላዊ ከመሆን ያለፈ ፋይዳም ትርጉምም አይኖርም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ መግለጫ በኋላ ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በአራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀመንበሮች፣ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በተሰጠ መግለጫ፤ “በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ፣ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ  እንዲለቀቁ ተወስኗል” ተብሏል። ምናልባት ይህ ውሳኔ ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ ይጠበቁ ከነበሩ  እርምጃዎች መካከል የታየ፣ ተስፋ ሰጪና አበረታች የተግባር ውሳኔ ሳይሆን አይቀርም።
ለማጠቃለል ያህል ሐገሪቱን በመምራትና ሕዝቡን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ፤ ስህተቱን አምኖ መፀፀቱና ሕብረተሰቡን ይቅርታ መጠየቁ፣ በአዎንታዊም በበጎ ጎኑም የሚታይ  መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አደናጋሪና ብዥታን የፈጠሩ እንዲሁም ለትርጉም የተጋለጡ ከላይ የተጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች የመግለጫውን ነጥቦች እንደገና በመፈተሽ፤ ለሚመራውና ወክየዋለው ለሚለዉ ሕዝብ ግልፅ በሆነና በተብራራ መልኩ በድጋሚ ሊያቀርባቸው ይገባል። ምክንያቱም ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚጀምረው ከዚህ አይነት ድርጊት ከመሆኑም ባሻገር፤ ሕብረተሰቡ የራሱ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ጉዳዩን በዝርዝር የማወቅ መብት እንዳለው ኢህአዴግ መገንዘብ  ይገባዋል።
በመጨረሻም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በእስር ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞችን ለመፍታት የወሰነውን አበረታች ውሳኔ በተግባር ላይ አውሎና ሌሎች የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ሊመልሱ የሚችሉ ውሳኔዎች እያሳለፈና እየተገበረ፣ ሀገሪቱን ከገባችበት ፖለቲካዊ ቀውሶች በማውጣት፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር የሚካሄድባት ሐገር እንድትሆን ማድረግ ይጠበቅበታል።
መልካም ዓውደ ዓመት!!

Read 1859 times