Saturday, 06 January 2018 12:30

የመኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች የአሜሪካ ቆይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ እና የመኢአድ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በዛብህ ደምሴ፤ በአሜሪካ የአራት ወራት ቆይታ አድርገው ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ የአሜሪካን ቆይታቸውን አስመልክተው ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም፣ ጉዟቸው ስኬታማ እንደነበር የፓርቲዎቹ አመራሮች አስታውቀዋል፡፡ ለመሆኑ ምን ዓይነት ስኬት ነው የተቀዳጁት? የዳያስፖራን ፖለቲካ እንዴት አገኙት? በአሜሪካ ከማን ጋር ተወያዩ? ምንስ አተረፉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡  

   እርስዎ እና የመኢአድ ፕሬዚዳንት ላለፉት 4 ወራት በአሜሪካ ያደረጋችሁት ቆይታ ዓላማው ምን ነበር?
በአሜሪካን ሃገር የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የሚባል ማህበር አለ፡፡ እነሱ የፖለቲካ እንቅስቃሴያችንን እንድናስረዳ ባቀረቡልን ግብዣ መሠረት ነው የሄድነው፡፡ ከሄድን በኋላ ዋሽንግተንን ማዕከላችን አድርገን፣ የተለያዩ ስቴቶች በመጓዝ፣ አላማችንን በማስረዳት፣ ሃገር ውስጥ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ገለፃ አድርገንላቸዋል። በዚህ መሃልም የፖለቲካ ትግሉን ለማገዝ የሚረዳ የፋይናንስ ድጋፍ አግኝተናል፡፡ በቆይታችን በዋናነት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የመኢአድ፣ የቀድሞ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎችን በማሰባሰብ፣ ጠንካራ የድጋፍ ሰጪ ቻፕተር በዋሽንግተን አጠናክረዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከቅንጅት መፍረስ በኋላ የመጀመሪያ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ ለኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲዎች፣ ለሴኔትና ለኮንግረስ ተጠሪዎች አስረድተናል፡፡
ከኮንግረስ አባላት ጋር ያደረጋችሁት ውይይት በምን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር?
ያገኘናቸው ሰዎች በአሜሪካ ፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዳይሬክተር ከሆኑት እንዲሁም ረዳት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ፣ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዴስክ ኃላፊ ከሆኑ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተናል፡፡ ይህ ከሦስት  ሰዎች ጋር ያደረግነው ውይይት ጠንካራ ነበር፡፡ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ነገር እኛ ከምናስበው በላይ ያውቃሉ፡፡ እንግዲህ በእኛ እምነት፣ የህዝቡ ነፃነት በራሱ በህዝቡ እጅ ነው ያለው፡፡ ማንም ተረድቶና ታግዞ የሚፈልገውን ሙሉ ነፃነት ያገኘ የለም፤ ህዝቡ ነው በራሱ ትግል የራሱን ስርአት መፍጠር ያለበት። የእኛ ዋናው ነጥብ፤ የአሜሪካ መንግስት ወዳጅነት መፍጠር ያለበት፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንጂ ከአገዛዙ ጋር እንዳልሆነ መግለፅ ነበር። “ወዳጅነታችሁ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው መሆን ያለበት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቁሙ” ነው ያልናቸው፡፡  
እነሱም ስርአቱ ያለበትን ሁኔታ ተረድተዋል። ኢትዮጵያ ላይ ችግር ቢፈጠር ካለችበት ቀጠና አንፃር ሊከተል በሚችለው ጉዳይ ዙሪያም ተወያይተናል። እነሱም በሚገባ ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ ያውቃሉ፡፡ በሚገባም ተረድተውናል፡፡
የፋይናንስ ድጋፍ ከዳያስፖራው ማግኘታችሁ በፖለቲካ ሥራችሁ ላይ ጫና አይፈጥርባችሁም?
ከዚህ ቀደምም እንደዚህ ያሉ ድጋፎች ይደረጋሉ። ድጋፍ የሚሰጡ አካላትም የእኛን ፕሮግራምና የፖለቲካ ዓላማ በሚገባ የተረዱ ናቸው፡፡ ባይረዱት ወይም የኛን አላማ ባይፈልጉ አያግዙንም ነበር። ስለዚህ እነሱ ናቸው ዓላማችንን ደግፈው የረዱን እንጂ እኛ አላማችንን እንቀይራለን ብለን አይደለም። ድጋፍ ሲያደርጉ ደግሞ እኛን ሳይሆን የህዝቡን የፖለቲካ ትግል ብለው ነው፡፡ ስለዚህ በኛ አካሄድ ላይ ምንም ተፅዕኖ አያሳርፍም።
ከኢትዮጵያውያን ጋር ባደረጋችሁት ውይይት ምን ተገነዘባችሁ? በተለይ ዳያስፖራው የወቅቱን የሃገሪቱን ሁኔታ እንዴት ነው የሚረዳው?
እኛ ያገኘናቸው ሰዎች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን የሚደግፉትን ነው፡፡ የሰማያዊንና የመኢአድን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚደግፉትን ነው ያገኘነው። ብዙ አይነት ሰው ነው በአሜሪካ ያለው፡፡ የትጥቅ እንቅስቃሴን የሚደግፍ አለ፣ ምን አገባኝ ብሎ ዝም ብሎ ኑሮውን የሚኖር አለ፡፡ እኛ ያገኘናቸውና ወደ ስብሰባችን የመጡት ግን የኛን የሰላማዊ ትግል አላማ የሚደግፉትን ነው፡፡ በእነዚህ ደጋፊዎቻችንና ሃገር ውስጥ በሚካሄደው እንቅስቃሴ መካከል የመረጃ ክፍተት እንዳለ ተረድተናል፡፡ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያውያኑ ሲናገሩ የተረዳነው፤ ሃገሪቱ ውስጥ ህዝቡ እርስ በእርስ መከፋፈል እንደተፈጠረና አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ያለመኖሩን ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በተቻለን አቅም ህዝቡ እንዳልተከፋፈለ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም አንድነቱን ጠብቆ ያለ መሆኑን፣ በቀላሉ የማይበታተን መሆኑን አስረድተናቸዋል፡፡ አሁን ለምሳሌ በኦሮሚያና በአማራ መካከል የተጀመረው ግንኙነት አንዱ ማሳያችን ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን ለሀገሪቱ መፍትሄ እንደማያመጣ፣ በዚያው ልክ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲም እንደሌለ ተወያይተናል፡፡
አሁን ግን ሰማያዊና መኢአድ በመዋሃድ እንዲሁም የቀድሞ አንድነት አባላት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ በመቀላቀላቸው፣ ለቀጣዩ ምርጫ አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ ለመፍጠር እየተንቀሳቀስን መሆኑን አስረድተናቸዋል፡፡ ስለዚህ ህዝቡ አንድ ከሆነና ጠንካራ ተቃዋሚ ከፈጠርን፣ ለውጥ እናመጣለን የሚል እምነት እንዳለን ገልጸንላቸዋል። አንድ ያረጋገጥነው ነገር፣ እዚያ ያለው የፖለቲካ መንፈስ፣ የሃገር ቤት ነፀብራቅ መሆኑን ነው፡፡ ድጋፉ ትልቅ ነው፣ በአሜሪካን ሃገር ያለው፡፡
የመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች መዋሃድ እንዲሁም የቀድሞ አንድነት አመራሮች ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀል ምን የተለየ ነገር ይፈጥራል?
እኛ እምነታችን ጠንካራ አማራጭ ኃይል መሆን ነው፡፡ ይሄን ደግሞ እንደምናደርገው፣ ጅምራችን አመላካች ነው፡፡ ቀደም ሲል “ተቃዋሚዎች አማራጭ ሃሳብ የላቸውም” ነበር የሚባለው፤ አሁን ደግሞ “አማራጭ ፓርቲም የለም” እየተባለ ነው። ገዢው ፓርቲ በዚህ መሃል ነው ስልጣኑን ይዞ መቀጠል የሚፈልገው፡፡ ይሄ አካሄድ ግን ለሀገሪቱ አይጠቅምም። ስለዚህ አማራጭ ሀይል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አማራጭ ኃይል ለመሆን ደግሞ ሰዎችን ድርጅትን ማሰባሰብ ይጠይቃል፡፡ ይሄን ለማድረግ ከተጣላነው ጋር ሳይቀር መታረቅ አለብን። የፈለገ ቅሬታ ቢኖርብን፣ ቅሬታውን ለህዝብ ሲባል መተው ይኖርብናል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተሰባሰብን አስቸጋሪ ነው፡፡
ቀጣዩ እንቅስቃሴያችሁ ምንድን ነው የሚሆነው?
እንግዲህ በሰላማዊ  ትግል ውስጥ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ፣ አምባገነን የሚባለውን መንግስት ህዝቡ እንዲጠላ ማድረግ ነው፡፡ ይሄን ሥራ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ሳይሰራ፣ ህዝብ በራሱ ጊዜ ገዥውን ፓርቲ  ተቀይሞታል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለው የሰላማዊ ትግል መርህ ደግሞ ጠንካራና ህዝቡ የሚያምነው አማራጭ ሆኖ መውጣት ነው፡፡ እንግዲህ አሁን እየሰራን ያለነው፣ ህዝቡ የሚያምነው ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረት ላይ ነው፡፡ እኛ ያስቀመጥነው ሌላው መርህ፣ ትግላችን ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ነው የሚል ነው፡፡ ሌላው እንደፈለገ ይሁን ዋናው ትግላችን ከኢህአዴግ ጋር ነው፡፡ ሌላው ጠላትነትን በማስወገድ፣ በተሰራው ላይ በመጨመር  መሄድን ነው መርህ ያደረግነው፡፡ አሁን የነፃ አውጪ ዘመን ላይ አይደለንም፤ ነፃነቱን ግለሰቡ ራሱ የሚወስድበት ዘመን ላይ ነው ያለነው።
መኢአድ በፓርቲዎች ድርድር መሳተፉ፣ ሰማያዊ ደግሞ የድርድሩ ተሳታፊ አለመሆኑ--- የውህደት ሂደታችሁ አለመግባባት አልፈጠረባችሁም?
ትልቁ መሻሻል ያለበት ይሄ ጉዳይ ነው። ከልዩነታችን ይልቅ ለምን አንድ በሚያደርገን ነገር ላይ ማተኮር አይቻልም? የኛ መርህ፣ አንድ የሚያደርገን ነገር እናጉላ የሚል ነው፡፡ መኢአድ በድርድሩ መሳተፉን፣ ምናልባት እስረኞች ከተፈቱ በሚል ከሆነ፣ በቅንነት ነው የምናየው፡፡ በዋናነት ግን አብረን መስራት በምንችለው ላይ ትኩረት ማድረግ ስለፈለግን ነው፡፡ ግን አሁንም አቋማችን እውነተኛ ድርድር ይካሄድ የሚል ነው፡፡
ፓርቲያችሁ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” በሚል ህዝባዊ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይቱ ምን ያህል ውጤታማ ነበር?
እርግጥ እኔ እዚህ አልነበርኩም፤ ነገር ግን እከታተል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት አይኑር እንጂ ምሁር አለ፡፡ እኛም ይሄን ውይይት ስናዘጋጅ፤ እነዚህ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች ምን ይላሉ የሚለውን ለማመላከት ነው፡፡ ባሰብነው ልክ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል።

Read 882 times