Saturday, 06 January 2018 12:24

ኦ… ደስታ ሆይ ወዴት ነሽ?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ singofbird@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

  ‹‹The world is a comedy for those who think, and a tragedy for those who feel.›› - ሆራስ (የሮማን ገጣሚ)

   እንደ ባይተዋር መንገደኛ፣ ራሳችሁን ከዝብርቅርቁ ሂደት፣ ይህችን ዓለም ብታጠኗት ልክ የለሽ ኢ-ፍትሃዊነት እንደከበባት ትታዘባላችሁ። እጅግ የሚገርመው ይሄው የኢ-ፍትሃዊነት ገፅ፣ በሰው ሰራሽም ይሁን በተፈጥሮአዊ ስሪቱ ዳብሮ፣ ሚሊዮን ምንትስ ጊዜ የተጠላለፈ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ በጨርቅ ኳስ በሚጫወቱ ትንንሽ ሕፃናት መካከል እንኳን ልብ ያላልነው፣ ያልተረዳነው የኢ-ፍትሃዊነት ገፅታ አለ፡፡
…በእርግጥ የሰው ልጅ  ሰው የመሆን መንደርደር፣ ደስታን በመፈለግ ስንኩል ድምዳሜ ከታጀበ፣ ስንፍና ይሆናል፡፡ በእርግጥ እናንተ ደስተኞች ናችሁ! ሦስት ሰዓት ሙሉ በጨዋነት ቆሜ ታክሲ የምጠብቀውን እኔን፣ በኃይል ቀድማችሁ ስለተሳፈራችሁ ተኩራርታችኋል። ወይም ከአስፓልት ማዶ አጥሩ ጥግ ለተቀመጠችው ምስኪን እህታችሁ፣ ጥቂት ሳንቲሞች ልትሰጧት ስለቻላችሁ፣ ልባችሁ ሐሴት አድርጓል፡፡ ጫማዎቻችሁ ከእኔ በተሻለ ጽዱ ስለሆኑ፣ የመብለጥ ስሜት ይሰማችኋል፡፡ ሌላም ሌላም…
እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ደስታን የመፈለግ ከንቱ ቅዠት፣ የሰነፎች የሕይወት ትርጓሜ ነው። እመኑኝ፤ እዚህ ቤት በድምቀት የሚዘፈንበት የደስታ ምክኒያት ሌላ የሆነ ቦታ፣ የሆነ ሰው ልብ ውስጥ የሚፈጥረው ጥልቅ ሐዘን አለ። ምክንያቱም ራሱን ችሎ ብቻውን የሚቆም ልሙጥ ደስታም ሆነ ሀዘን የለም፡፡ አንዳንዴ ይሄ የኢ-ፍትሃዊነት ጥልፍልፎሽ ድንገት ቢከስም ዓለምም በቅፅበት ሟሽሻ እንደምትጠፋ ይታሰበኛል። ዓለም ህልውናዋን ጠብቃ እስከ ግሳንግሷ እምትሽከረከረው፣ በኢ-ፍትሃዊነት ዛቢያ ላይ ነዋ፡፡ አርስቶትል እንዲህ ይላል፡- ‹‹የትሮይ ጦርነት ታሪክ ሙሉ በሙሉ አሳዛኝ እንደሆነ የሚታሰባቸው ሰዎች የገባቸው የታሪኩ ግማሽ ብቻ ነው፡፡›› አዎ እዚህ ቤት በጥልቀት የሚያስለቅሰው ሰበብ፣ እዚያ ቤት ለመሳቅ በቂ መነሻ አለው፡፡ ምክንያቱም ደስታ የምትናጠቋት እንጂ የምትፈጥሯት አይደለችም፡፡ የአሸናፊው ፍንደቃ፤ ያለተሸናፊው ሀፍረት፣ ውርደትና ለቅሶ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ ከላይ ከላይ ስታየው ቢመስልህ እንኳን እመነኝ፤ ራሱን ችሎ ለብቻው የሚቆም፣ ልሙጥ ደስታም ሆነ ሐዘን የለም። በበኩሌ  በእነዚህ ሁሉ ትብታብ የሕይወት ድሮች እየተዳኙ፣ ደስታን የማሳደድ መፍገምገም፣ ከሰውነት ወደ ቢራቢሮነት የመቅለል ሂደት ሆኖ ይታሰበኛል፡፡
ደስታ እንዲህ ርካሽ ነች። ማንም የሚለጋት፣ ፈጥና የምትጠወልግ፣ ወደ ባዶነት የምትከት የውድቀት ሠንሠለት!... አዎ የሰው  ልጅ የሕይወት ዘመን ግብ ደስታን መሻት ነው የሚሉ፣ እነሱ ሰነፎች ናቸው። በመተዋወቅ ውስጥ መለያየትን፣ በእያንዳንዱ ወዳጅነት ውስጥ ጠላትነትን፣ በውበት ውስጥ ጎደሎ ማንነትን፣ የሚያስደስት ሙዚቃ አጋማሹ ሙሾ መሆኑን ማየት ካልቻልክ፣ ሕይወት ገና አልገባችህም ማለት ነው፡፡ ወዳጄ ሆይ፤ ላንተ ሊመስልህ ይችላል እንጂ ለዘለዓለም ባለበት ፀንቶ የሚቆይ አንድም ነገር የለም፡፡ ዛሬ ፈክታ የምታያት የምታሳሳ ፅጌረዳ አበባ፣ ከወራት በኋላ ደርቃ እሾኋን ብቻ ታገኛለህ፡፡ ዛሬ የምታመልክባቸው ሐይማኖቶች፣ ትናንት ከእነሱ በፊት የበቀሉ ጣዖታትን ደምስሰው የመጡ ናቸው፡፡ ነገ እነሱም ጣዖታት ተብለው ላለመጣላቸው ማረጋገጫ ልትሰጠኝ አትችልም፡፡
መቼም የአንተ ህልውና ራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ መሆኑን አትስተውም፡፡ ግን አንተ ብልህ ነህ፡፡ መደሰት ትፈልጋለህ አይደል፡፡ ስለዚህ የእኔን የብልጣብልጥ መንገድ ተወውና በራስህ የየዋሁ መንገድ ተጓዝ፡፡ ሲሾሙህ እልልል በል። ተደሰት፣ ቦርቅ፣ ፈንድቅ፣… ሲሽሩህ ነፍርቅ። አልቅስ፣ ተላቀስ፣ ተለቃቀስ፣… ሕይወት የመጫወቻ ካርዶቿን ሁለት ገጾች እየገለባበጠች እያሳየች እንደምትሸነግልህ እስኪገባህ ድረስ ይህን የየዋህነት መንገድህን ቀጥልበት፡፡ ብቸኛው ሰው በመሆን የተጣለብህን ስቃይ ማምለጫ መንገድህ፣ ይሄው የየዋህነት (ምናልባትም የድንቁርና) መንገድ ብቻ ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ዓለምን በደስታ የተሞላች የሽርሽር ቦታ አድርገው ሲያስቧት ይገርመኛል። የእኔ እውነት ግን ይለያል፡፡ የሚያስደስት፣ ተስፋን የሚሰብክ ሙዚቃን ከሰማሁ በኋላ በልቤ ላይ ታትሞ የሚቀረው ጥልቅ ሐዘን ብቻ ነው። ይህንን ሰው በመሆን ብቻ የሚጣልብልንን የሐዘንተኝነት ስሜት፣ ንቃቱ ላልገባቸው ማብራራት ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ብቻ ነው። ነገሩ በብዙ መፍገምገም፣ በማያቋርጥ ሐሰሳ፣ በጥልቅ መንዘፍዘፍ፣ ከድርብርብ ዓመታት በኋላ የሚደረስበት እንጂ የሚተነተን አይደለም፡፡
ደግሞስ የትኛውም ዕውቀት በቃላት ሊያብራሩት የሚቻል አይደለም እኮ፡፡ በጥልቅ የነፍስ ስርቻ ላይ የታተመ ሲሆን ደግሞ የትንተና ሂደቱ አታካች ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ሊያስብ፣ ሊያውቅ፣ ሊጠበብ፣ ሊወድ ከፈለገም ሊጠላ ይችላል፡፡ ከዚህ ዕምቅ የስሜት እቶኑ ውስጥ በቃላት ሊገልፅ የሚችለው ጥቂቱ ብቻ ነው። ቃላት እኮ ደካማ ናቸው፡፡ ቢሆንም በቃላት እንዲህ እንላለን… ሰው የመሆን መፍገምገም ምንድን ነው? መደሰትስ ምን ማለት ነው? ህልውና ለምን ኖረ? ጊዜ ይሉት ረቂቅ የወናነት ሁነት ከህልውና ጋር ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል?…  ለእነዚህ ጥያቄዎች የምታገኘው የምናልባት መልስ የሚያስበረግግ እንደሆነ እነግርሃለሁ፡፡ ግን ማምለጫ የለህምና እየደነበርክ፣ እየበረገግክም መጠየቅህን ትቀጥላለህ።
ንቃት ይህንን ተከትሎ የሚመጣ ሂደት ነው። አንተ የነቃህ ከሆንክ፣ ከየትኛውም አስደሳች ሂደት በኋላ በልብህ ታትሞ የሚቀረው ትልቅ ሐዘን ብቻ ነው፡፡ ለምን አልከኝ? ግሩም ጥያቄ አነሳህ… ምክኒያቱም አንተ ግዞተኛ ነህ፡፡ ሙሉ ሆና ባልተፈጠረች ዓለም፣ ሙሉነትን ባለማቋረጥ ሙሉነትን እንድትሽት ተደርገህ የተሰራህ ግዞተኛ ነህ፡፡ የማይረካ ስሜትህን፣ የማይገታ ፍላጎትህን፣ የማይታገስ ረሃብህን፣ መቋጫ የሌለው ብቸኝነትህን እያባበልህ እንድትኖር ተግዘሃል፡፡
እናስ የሠው ልጅ የሕይወት ዘመን ግብ ምንድን ነው? ካላችሁ መልሴ እኔም አላውቀውም ይሆናል። ሆኖም ጥቂት የምናልባት ድምዳሜዎችን አላጣም። ልብ አድርጉ! እውቀቶቻችን፣ አስተውሎቶቻችን መረዳቶቻችን የምናልባት ናቸው። ምናልባት ግን የሠው ልጆች የሕይወት ዘመን ግብ በኑባሬያቸው ላይ የሚመላለሰውን ጎዶሎ ማንነት መፈለግ ይሆን? ወለፈንዴነቱን መለየት? በመጨረሻው ሰዓት እንደ እስቲቭ ጆብስ ድንጉጥ እንሰሳ ከመሆን ወጥቶ ሞትና ሕይወትን መሞገት? ወይስ ለመኖራችን ሌላ የትርጉም ከፍታ መተለም? ... ሆኖም ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ ግን የሚያስበረግግ እንደሆነ እነግራችኋለሁ። ግን ተሸሽቶ የት ይደረሳል? ማምለጫስ የታል?
ይህ ሁሉ የሚገባህ የነቃህ ከሆንክ ብቻ ነው፡፡ ካልነቃህማ ልክ እንደ ልጅነታችን ጀላቲ ሲገዙልህ ሁሉ እየፈነደቅህ፣ ዓለም የሽርሽር ጉዞ ነች ብለህ ልትሰብከን ትሞክር ይሆናል፡፡ በበኩሌ ይሄኛው ሕይወት ከዚህኛው ይሻላል በሚል የደንቆሮ ፍርድ የማስቀመጥ ፍላጎት የለኝም፡፡ ምርጫውን ላንተ ትቻለሁ፡፡ የትኛውም የሕይወት ዘይቤ ከሌላኛው አቻው የሚሻልበት የራሱ ለዛ አለው። የቱንም ያህል አስፀያፊ መሰሎ ቢታየን እንኳን… አንድ ነገር ግን እውነት ነው፡፡ እንዴትም ኑር የት፣ አንተ አዋቂና የነቃህ ከሆንክ ከየትኛውም አስደሳች ሂደት በኋላ በልብህ ታትሞ የሚቀረው ጥልቅ ሐዘን ብቻ ነው፡፡ አንድ ነገር ግን ልለምንህ…አደራ! መንቃትን የተጠናና የሞተ ቲዎሪ በመሸምደድና ዲግሪ በመደራረብ እንዳትለካው፡፡ ወዴት ወዴት… የመንቃት መንገዱ ሌላ… የነፍስ መቃተቱ የት ሄዶ?
ወዳጄ፤ ሰው መሆንን ከሻትክ ደስታን ሳይሆን ጊዜን አሸነፍ፡፡ ጊዜን ካሸነፍክ ደስታም ሆነ ሐዘን ለአንተ ተረቶች ሆነው ይታዩሃል፡፡ ምርጫውን ግን ላንተ ተውኩት፡፡ በመጨረሻ በዊሊያም ሼክስፒር ቋንቋ ‹‹የተቀረው ዝምታ ነው›› እልሃለሁ፡፡

Read 2162 times