Saturday, 06 January 2018 12:22

በቅሎ የጠፋበት የተሰቀለ ኮርቻ ገልጦ አየ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

    ጥንት፣ ዛሬ እየፈረሰ ባለው ማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ታስረው ይመጡ ነበር፡፡ የገና ሰሞን ከታሠሩት ውስጥ ጥቂቶቹን ዛሬ እንይ፡፡ ተረት ይምሰሉ እንጂ ዕውነተኛ ባህሪያት ናቸው፡፡ በበዓል ማሠር የተለመደ ነበር!
ሁለት ዕብዶች ነበሩ፡፡ አንደኛው ፒያሳ ደጎል አደባባይ እየዞረ፡-
“ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ሃ/ማርያም ሀቀኛ ኮሙኒስት ናቸው!
ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ሃ/ማርያም ሀቀኛ ኮሙኒስት ናቸው!”
እያለ ቀኑን ሙሉ አደባባዩን ሲዞረው ውሎ፤ ወደ ማታ ላይ ሲቪል የለበሱ ሰዎች አሥረው ወደ ማዕከላዊ ያመጡታል፡፡
“ጥፋቴ ምንድን ነው?” ሲል መርማሪውን ይጠይቃል፡፡
መርማሪውም፤
“ይህንን፤ ዓለም ያወቀውን ዕውነት የምትደጋግመው ነገር ቢኖርህ ነው!”
“ምን ዓይነት ነገር?”
“በውስጠ-ሚሥጥር “ሀቀኛ ኮሙኒስት አይደሉም” ብለህ ህዝቡን ለመቀስቀስ ነው! ነቅተንብሃል” ብሎ “አንዱ ክፍል አስገቡት” በማለት አዘዘ፡፡
ሁለተኛው ዕብድ የመጣው ደግሞ በአንድ የቀበሌ ስብሰባ ላይ፤
“መንግሥት እስከ መቼ ነው ጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ የሚባለው? ለምን ቋሚ አናደርገውም?” ብሎ በጠየቀው መሠረት፣ ህዝቡ በዚሁ ጉዳይ ሲጨቃጨቅ በመዋሉ፤ ህዝብን ለአመፅ የሚቀሰቅስ ፀረ-አብዮት ተግባር ነው” ተብሎ ነው፡፡
ሁለቱ ዕብዶች ዳማ ይጫወታሉ፡፡ አንደኛው ሌላኛውን በልቶት አንዲት ጠጠር ብቻ ቀርታዋለች፡፡ ያቺን ጠጠር በንጉሥም፣ በወታደርም መብላት ይችላል፡፡
ተሸናፊው፤ እየደጋገመ፤
“በወታደር አልበላም፡፡ በንጉሥ እንድትበላኝ ትገደዳለህ” ይለዋል፡፡
አሸናፊው ዕብድ፤
“የእኔ ወንድም፤ አንዴ ሞት ከተፈረደብህ፣ በቺቺ ግደሉኝ፣ በክላሽ ግደሉኝ፣ በሽጉጥ ግደሉኝ እያልክ ምን ያጨቃጭቅሃል?” አለው፡፡
ሌላኛው፤
“አሄሄ ሌላ ሸውድ! የንጉሥ አገዳደልና የወታደር አገዳደል አንድ መሰለህ? ንጉሥ፤ አንድ አንተን ብቻ ገሎ እፎይ ብሎ ይተኛል፡፡ ወታደር ግን አንድ አንተን ብቻ ገድሎ ዝም አይልም፡፡ ቂም ይይዙብኛል ብሎ ዘመድ አዝማድህን ሁሉ ይፈጃል፡፡ ለዚህ ነው በንጉሥ እንድትበላኝ ትገደዳለህ የምልህ!”
*      *      *
በሀገራችን ታሪክ እሥር ቤት ረዥም ዕድሜ ካላቸው ፍሬ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት ደግሞ በዓይነቱ ለየት ያለ ነው፡፡ ከፖሊስ ጣቢያ፣ ከቀበሌና ከፍተኛ እንዲሁም ከደርግ ጽ/ቤት እሥር ቤቶች ይልቅ ልዩ ባህሪ ያለው የማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት ነው፡፡ በአፍ-እላፊ (መንግሥትንና መሪን በመስደብ) በእግር- እላፊ (በእግር ድንበር ተሻግሮ መሄድ) በእጅ እላፊ (በስርቆት)፣ በልብ- እላፊ (ያሰበ ይቀጣል የሚለውን ህግ በመድፈር)… ብዙ እላፊዎች አሉ፡፡ የእላፊ ወንጀሎች በፖለቲካ ከመታሠር፣ በአረንጓዴው ዘመቻ  (በምርት ዘመቻ) ከመታሠር፣ በነብስ ግድያ፣ ጫካ ገብቶ እስከ መታገል ከሚፈጠሩ እስሮች ይለያሉ፡፡ ማዕከላዊ፤ ሰውና ዕድሜን አይመርጥም፡፡ ለፆታና ቀለም አያደላም፡፡ ማዕረግ አይለይም- ከየማዕረጉ ያሥራል። ዕብድም ከተገኘ ይታሠራል፡፡
በዚህ ምክንያት አንዳንድ ተሳላቂዎች፣ ዲሞክራሲያዊ እሥር ቤት ነው ይሉታል! ሌላው ባህሪው “የአደራ እሥረኛ” የሚባሉ እሥረኞችን ማጎሩ ነው፡፡ ማንም እማይነካቸው፣ ያስቀመጣቸው ሰው (ባለሥልጣን) ብቻ፤ ፈቅዶ ወዶ በቃኝ ሲል የሚያስወጣቸው፣ እሥረኞች ናቸው፡፡ በምድር የሰጠሁህን በሰማይ እቀበልሃለሁ ብሎ ነው ማለት ነው፡፡ የገዛ አባላቱ እገዛ መሥሪያ ቤታቸው ማዕከላዊ፤ ባለ ተራ ሲሆኑ የሚታሠሩም አሉ፡፡ የደርግ ኢሰፓአኮ ሥር ያሉ ድርጅቶች የመኢሶን፣ የወዝሊግ፣ የማሌሪድ፣ የሰደድ፣ የኢጭአት ሰዎችም ታስረውበታል፡፡ ማዕከላዊ ሁሉን ጎራሽ ነው፡፡ ለማንም አይተኛም፡፡ ኢትዮጵያ የእሥር ቤትም፣ የእስረኛም፣ ድሃ ሆና አታውቅም፡፡
ከወንጀል ጋር በተያያዘ ሲታሰብ፣ እሥር ቤት መቼም አላስፈላጊ የሆነበት ጊዜ የለም፡፡ ችግሩ የሚመጣው አላግባብ መታሠር ሲመጣ ነው፡፡ በግርፊያ ካላመንክ ወዮልህ መባል ሲከሰት ነው፡፡ የዘገየ ፍርድ ከአለመፈረድ አንድ ነው በሚባልበት ዓለማችን፤ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ ያለ አንዳች ውሳኔ ጨለማ ቤት ሆኖ ዓመታትን መቁጠር ሲኖር ነው ዘግናኝ የሚሆነው፡፡ ዐይንን ተጨፍኖ “ቤርሙዳ” ሲገባ ነው ፍፁም ሰቅጣጭ የሚሆነው፡፡ ለመሆኑ የገራፊዎች የሥራ ልምድ ሌላ ሥራ ለመያዝ ይረዳቸው ይሆን?! ወይስ ወደ ሌላ እሥር ቤት ይዘዋወራሉ፡፡ የሰራተኛ ማስተዳደሪያ መሥሪያ ቤት ሕግ አያውቃቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ወይም አንዳንዴ ይቻላል! ዓመት በዓል ሲመጣ ለእስረኞች ምህረት ማድረግ በየመንግሥታቱ የተለመደ ይመስላል፡፡ ቤተሰብም መቼም ተስፋ ማድረጉ አይቀርምና ይጠብቃል! በዛሬውም የክርስቶስ ልደት ዋዜማ የምሕረት ተስፋ ማግኘቱ፣ የአያሌ ቤተሰቦችን ተስፋ ማለምለሙ፣ ደስታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ማዕከላዊ ሙዚየም ይሆናል የሚለውም ቃል ሲተገበር፣ የማዕከላዊን ውስጣዊ ገፅታ እንደ ጎብኚ የማየት ዕድሉን ህዝብ ማግኘቱ አንድ ፍሬ ነገር ነው! ጥሩ ጅማሬ ነው፡፡ አዝማሚያውን ማስፋፋት ነው። ብዙ ገናዎች፣ መውሊዶች እና ሌሎች በዓላት፤ መልካም ዜና ያመጡልን ዘንድ ተስፋ እናድርግ!!
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” የሚለን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ ሁሉ ነገር በራሱ ጊዜ እንደሚመጣ አስረጅ ማቅረቡ ነው! መልካም ድርጊት የምንፈፅመው ሲጨንቀንና ሲጠበን መሆን የለበትም፡፡ ቀናነት ውስጣችን ሁሌም መኖር አለበት፡፡ ስንቸገር ብቻ ደግ የምንሆን ከሆነ ግን አጉል ተስፋን ነው የምንሰብከው፡፡ በቅሎ የጠፋበት የተሰቀለ ኮርቻ ገልጦ አየ ማለት ይሆናል፡፡ መልካም ገና!!

Read 5355 times