Tuesday, 02 January 2018 10:30

በ2017 የዓለም ስፖርት 17 ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የሚዘጋጀው የዓለም ኮከብ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ምርጫ ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ፊፋ እና ፍራንስ ፉትቦል በጋራ ላለፉት 5 የውድድር ዘመናት ሲያዘጋጁት የነበረው የወርቅ ኳስ ሽልማት ስለተቀየረ ነው፡፡ በአዲስ ስያሜ The Best FIFA Football Awards™ ተብሎ በፊፋ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በምርጫው ተጨዋቾች፤ አሰልጣኞች፤ ደጋፊዎች፤ ደጋፊዎች እና የመገናኛ ብዙሃን አባላት ተሳትፈዋል፡፡ በ2016 ‹‹ዘ ቤስት ፊፋ ፉትቦል አዋርድስ›› ላይ በወንዶች ክርስትያኖ ሮናልዶ በሴቶች ደግሞ ካርሊ ልሎይድ የዓመቱ ምርጥ  ተጨዋቾች ሆነው ሲሸለሙ በወንዶች የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ የነበሩት ክላውድዮ ራኒዬሪ እንዲሁም በሴቶች ሲልቪያ ኒይድ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኞች ሆነው በዙሪክ በተካሄደ ደማቅ ስነስርዓት ተሸልመዋል፡፡
እንግሊዝ በሁለቱ የፊፋ የወጣት እና የታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖች የዓለም ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ በደቡብ ኮርያ በተዘጋጀው የፊፋ ሀ20 የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በህንድ በተዘጋጀው የፊፋ ሀ 17 ሻምፒዮና ላይ ነው፡፡ ለ2018 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአውሮፓ አገራት በተካሄደ የምድብ ማጣርያ አንድም ጨዋታ ሳትሸነፍ ማሸነፍ የቻለችው ጀርመን በ2017 የፊፋ ኮንፌደሬሽን ካፕ ድልን በማግኘት ሻምፒዮናቷን ለማስጠበቅ እንደምትሰለፍ አመልክታለች፡፡
በ2016 / 17 የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በዚነዲን ዚዳን የሚሰለጥነው የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ለ12ኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው የጣሊያኑን ጁቬንትስ 4ለ1 በማሸነፍ ነበር፡፡ በዚህ ድልም ሻምፒዮንስ ሊገ በአዲስ ፎርማት መካሄድ ከጀመረ በኋላ በሁለት ተከታታይ የውድድር  ዘመናት በማሸነፍ ሻምፒዮናነቱን ለማስጠበቅ የቻለ የመጀመርያው ክለብ ሆኗል፡፡ ከዚህ ታሪካዊ ስኬት በኋላም ሪያል ማድሪድ በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የብራዚሉን ግሬሚዮ 1ለ 0 በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በ2017 ሪያል ማድሪድ 5 ዋንጫዎችን የሰበሰበ ሲሆን ከአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ከፊፋ የዓለም ክለቦች ሁለት ዋንጫዎች ጋር በተጨማሪ የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ፤ የስፓኒሽ ሱፕር ካፕ እና የአውሮፓ ሱፕር ካፕ 3 ዋንጫዎችን በመቀደጃቱ ነው፡፡
ክርስትያኖ ሮናልዶ ከሪያል ማድሪድ ጋር በስፔንና በአውሮፓ ደረጃ ከሰበሰባቸው አምስት ዋንጫዎች ባሻገር በአዲስ መልክ የተካሄደውን የፊፋ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ምርጫ አሸንፎ በተጨማሪም ለአምስተኛ ጊዜ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን ከፍራንስ ፉትቦል በመቀበል ከሜሲ ጋር እኩል ሊሆን በቅቷል፡፡
የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አምበል ኔይማር ባርሴሎናን በመልቀቅ ወደ ፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዠርመን የተዛወረበት 264 ሚሊዮን ዶላር የዝውውር ሂሳብ  በዓለም እግር ኳስ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኔይማር ስለዝውውሩ ሲናገር ‹‹ በህይወቴ ከባዱ ውሳኔ ነበር፡፡ ወደ ፒኤስጂ የተዛወርኩት አዳዲስ ዋንጫዎች አዳዲስ ፈተናዎችን ለመሞከር እንጅ ለገንዘብ አይደለም፡፡›› ብሎ ነበር፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች ከሜዳ ውጭ ካለው ከፍተኛ ገቢ የማስገኘት አቅም ጋር ዝውውሩ የሚያያዝ ነው ብለዋል፡፡
በባርሴሎና ክለብ እየተጫወተ ምንም አይነት ዋንጫ ሳያገኝ 2017 ያሳለፈው ሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲናን ባለቀ ሰዓት ለራሽያ 21ኛው ዓለም ዋንጫ በግል ብቃቱ በማሳለፍ ተሳክቶለታል፡፡
ጣሊያንና ሆላንድ በ2018 ራሽያ ወደ የምታስተናግደው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ሳያልፉ ቀርተዋል፡፡ ጣሊያን ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ሲያዳግታት ከ60 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ሆላንድ ደግሞ በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ እንዳመለጣትና በዓለም ዋንጫ ለሶስት ጊዜያት ተፋላሚ እና በ2014 በብራዚሉ ዓለም ዋንጫ 3ኛ ደረጃ ማግኘቷ ይታወቃል፡፡
በርካታ ታላላቅ ተጨዋቾች ጫማቸውን የሰቀሉበትና ከየብሄራዊ ቡድኖቻቸው በጡረታ የተገለሉበት ዓመትም ነበር። ከእግር ኳስ ስፖርት ከተሰናበቱ ተጨዋቾች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የ39 ዓመቱ ጣሊያናዊ ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን ነው፡፡ በጣሊያን ብሄራዊ ቡድን እና  በሴሪኤ ከፍተኛ ስምና ክብር ያተረፈው የኤኤስ ሮማ ክለብ ተጨዋች ፍራንቸስኮ ቶቲ በ40 ዓመቱ እግር ኳስን በመሰናበት ጫማውን ሰቅሏል፡፡ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ምሰሶ ተብሎ የሚወደሰውና በባየር ሙኒክ ክለብ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበረው ፊሊፕ ላህም እንዲሁም በስፔን ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በእንግሊዝ እና ስፔን ክለቦች ስኬታማ ተጨዋች ሆነው ያሳለፈው ዣቪ አሎንሶ ጫማቸውን ከሰቀሉ እውቅ ተጨዋቾች ይጠቀሳሉ። በጣሊያንና በብራዚል ብሄራዊ ቡድን ከዚያም ባሻገር በስፔኑ ላሊጋ እና በጣሊያን ሴሪኤ ከፍተኛ ስኬት የነበራቸው ምርጥ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ብራዚላዊው ሪካርዶ ካካ እና ጣሊያናዊው አንድሬ ፒርሎ የመጨረሻ የተጨዋችነት ዘመናቸውን በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ ካሳለፉ በኋላ ጫማቸውን ሰቅለዋል፡፡ ጣሊያንንና ሆላንድ ከዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ከቀሩ በኋላ በርካታ ተጨዋቾች ከብሄራዊ ቡድን ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ከጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ራሳቸውን ካገለሉት የ34 ዓመቱ ዴል ሮሲ እና የ33 ዓመቱ ጆርጂዮ ቼሊኒ ሲጠቀሱ ከሆላንድ ብሄራዊ በድን ደግሞ አርያን ሮበን ናቸው፡፡
ጋቦን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካሜሮን በፍፃሜው ጨዋታ ግብፅን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ ይሁንና በ2018 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ላይ በመጨረሻ ጨዋታ በናይጄርያ ተሸንፋ ሳታልፍ ቀርታለች፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አማካኝነት በ2017 መግቢያ ላይ በተካሄደው የዓመቱ ኮከብ ተጨዋቾች ሽልማት የ2016 የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተሸለመው የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድንና የእንግሊዙ ክለብ ሌስተር ሲቲ ተጫዋች የሆነው ሪያድ ማህሬዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል   ከአፍሪካ ውጭ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በመጫወት ልዩ ስኬት ያስመዘገበው ደግሞ ጋቦናውያን አጥቂ ፒዬር ኦቢምያንግ ሲሆን በ2016/17 የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ31 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በመጨረሱ ነው፡፡ ከኦቢምያንግ በፊት ይህን ማሳካት የቻለው አፍሪካዊ ጋናዊው ቶኒ ዮቦሃ ለአይንትራክት ፍራክፈርት በተጫወተበት ወቅት ነው፡፡
ግብፃዊው መሀመድ ሳላህ ከጣሊያኑ ክለብ ኤኤስ ሮማ ወደ እንግሊዙ ሊቨርፑል ሲዛወር የተከፈለው 34.3 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ታሪክ ለአፍሪካዊ ተጫዋች አዲስ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ መሃመድ ሳላህ በአሁኑ ወቅት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን በ15 ጎሎቹ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ እየመራ ሲሆን ግብፅን ለ31ዓመታት ወደራቀችበት የዓለም ዋንጫ እንድትመለስ ካበቁ ተጫዋቾች ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የእንግሊዟ ለንደን ከተማ ያስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲሆን በዚሁ ሻምፒዮና ላይ ሁለት የዓለማችን  ታላላቅ አትሌቶች በተለያየ መንገድ ስንብት ማድረጋቸው ይታወሳል። የዓለማችን የአጭር ርቀት ንጉስ የሆነው  ጃማይካዊው ዮሴያን ቦልት በሻምፒዮናው የመጨረሻውን የ100 ሜትር ውድድር ካደረገ በኋላ በአጠቃላይ ከስፖርቱ በጡረታ የተሰናበተ ሲሆን፤ ከለንደን በፊት በተካሄዱት ሶስት የዓለም ሻምፒዮናዎች እና ሁለት ኦሎምፒኮች በረጅም ርቀት ተፎካካሪ አጥቶ የነበረው እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ ደግሞ በትራክ ላይ የመጨረሻውን ውድድር በ5ሺ ሜትር ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያዊው ሙክታር ኢድሪስ ተሸንፎ ከትራክ ሩጫ በይፋ ተሰናብቷል፡፡ በተያያዘ በስፖርት ኮንሰልንተሲ የተሰራ  ጥናት  እንዳመለከተው ከ200 አገራት የተወከሉ 3300 አትሌቶች የተሳተፉባቸውን 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ፓራ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በ20 ቀናት ውስጥ ያስተናገደችው የለንደን ከተማ ለኢኮኖሚዋ 107 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘቷን ነው፡፡  በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ስታድዬም መግቢያ 705 ሺ ትኬቶች መሸጣቸው በጊኒስ ዎርልድ ሪከርድ መዝገብ ሰፍሯል፡፡ በ2017 በተካሄዱ የማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች ብዙም አልተሳካላቸውም። ዋና ዋናዎቹን ማራቶኖችን ያሸነፉት ኬንያውያን ናቸው፡፡ ይሁንና በረጅም ርቀት ሩጫ የዓለማችን የምንግዜም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ ግን ተሳክቶላታል፡፡ በለንደን ማራቶን በ2ኛ ደረጃ ስትጨርስ ያስመዘገበችው 2፡17፡26 የሆነ ጊዜ አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ሊሆን ሲበቃ  ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈችበት የቺካጎ ማራቶን ደግሞ አሸናፊ ነበረች፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ወንዶች ምድብ ትልቅ የማራቶን ውጤት ያስመዘገበው በዱባይ ማራቶን ለማሸነፍ የቻለው ታምራት ቶላ ነው፡፡
በዓለም የቴኒስ ስፖርት ታላላቆቹ ራፋኤል ናዳልና ሮጀር ፌደረር ስኬታማ የውድድር ዘመን አሳልፈዋል፡፡  ራፋኤል ናዳል የፍሬንች ኦፕንና የዩኤስ ኦፕን የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮናዎችን ሲያሸንፍ፣ ሮጀር ፌደረር ደግሞ የአውስትራሊያ ኦፕንና የዊምብሌይን ሻምፒዮናን አሸንፏል፡፡ በተያያዘ ፎጀር ፌዴረር በሜዳ ቴኒስ ተጨዋችነት ያገኘው የገንዘብ ሽልማት ዘንድሮ ከ110 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ የዓለምን ስፖርት በከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ ሰብሳቢነት እንዲመራ ያደረገው ሲሆን በ2017 ብቻ ከሽልማት ገንዘብ ያገኘው 11.7 ሚ. ዶላር ነው፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ኢንቨስት ያደረጉ ቻይናውያን ባለሃብቶች ብዛት  28 ደርሷል፡፡ ትልቁ የኢንቨስትመንት ውል የቻይናው ግሩፕ የጣሊያኑን ክለብ ኤሲ ሚላን  በ710 ሚሊዮን ዮሮ መግዛቱ ነው፡፡  በእንግሊዝ ፕሮሚየር ሊግ በሚወዳደረው ሳውዝ ሃምፕተን 80 በመቶ ድርሻን ቻይናዊው ጋኦ ሼንግ ከገዛ በኋላ በሊጉ ያሊ ቻይናውያን ባለሀብቶች ብዛት 6 ደርሷል፡፡
በጂያኒ ኢንፋንቲኖ የሚመራው ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ በ2026 እኤአ ላይ በሚካሄደው ዓለም ዋንጫ የተሳታፊ አገሮች ብዛት ከ32 ወደ 48 እንዲያድግ የወሰነ ሲሆን፤  በማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ደግሞ በ2019 እ.ኤ.አ ላይ ካሜሮን በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ አገራትን ብዛት ከ16 ወደ 24 አሳድጎታል፡፡
ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2024 ፓሪስ በ2028 እኤአ ደግሞ የሎስ አንጀለስ ከተሞች 33ኛው እና 34ኛው ኦሎምፒያዶችን እንደቅደም ተከተላቸው እንዲያስተናግዱ መርጧቸዋል፡፡
በቦክስ ስፖርት ፍሌይድ ሜይዌዘር በላስቬጋስ ኮነር ማክሪጎር ገጥሞ የተከፈለው 100 ሚሊዮን ዶላር የዓመቱ ከፍተኛ የስፖርት ክፍያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡

Read 2395 times