Print this page
Tuesday, 02 January 2018 10:29

ጆርጅ ዊሃ የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ሊሆን ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ከ22 ዓመታት በፊት የዓለም፤ የአውሮፓና የአፍሪካ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የተሸለመው የ51 ዓመቱ  ጆርጅ ዊሃ የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመርጧል፡፡  ትናንት በመላው ዓለም በተሰራጩ ዘገባዎች እንደተጠቀሰው የላይቤሪያ የምርጫ ኮሚሽን ከ2 ሚሊዮን በላይ ላይቤርያውያን የተሳተፉበት ምርጫ ጊዜያዊ ቆጠራ ይፋ ሲያደርግ በሁለተኛ ዙር ምርጫው ጆርጅ ዊሃ 68.1 በመቶ ድምፅ በማግኘቱ አሸናፊነቱን ሊያረጋግጥ ችሏል። ከወር በፊት ተካሂዶ በነበረው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ  እሱና ዋና  ተፎካካሪውና የላይቤርያ ምክትል ፕሬዝደንት   ጆሴፍ ቦዋኪን  ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ ባለማምጣታቸው ነበር  ሰሞኑን ምርጫው በድጋሚ የተካሄደው፡፡
የምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ከታወቀ በኋላ ጆርጅ ዊሃ በትዊተር ገፁ “ውድ ላይቤሪያውያን አሁን ስሜታችሁ ይገባኛል፤ ዛሬ የተሰጠኝን ወሳኝ ሚናና ግዙፍ ሃላፊነት ጠንቅቄ አውቃለሁ። ለውጡ ተጀምሯል“ ብሎ ፅፏል፡፡ የቀድሞ ክለቡ የሆነው የፈረንሳዩ ፒኤስጂ በበኩሉ በክለቡ ኦፊሴላዊ ቲውተር ገፅ ላይ ‹‹ጆርጅ ዊሃን የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ከመሆኑ በፊት እናውቀዋለን፡፡ ለፒኤስጂ የምስራች ነው…›› በሚል ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
በጆርጅ ዊሃ መመረጥ በላይቤርያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ እና በትውልድ ከተማው ጂብላርተር ጎዳናዎች ደጋፊዎቹ ደስታቸውን በብዛት በመውጣት የገለፁ ሲሆን አዲሱ ፕሬዝዳንታቸው አገራቸውን ከጦርነት እንዲያርቅ፤ በመንግስት አስተዳደር የተንሰራፈውን ሙስና እንዲያጠፋ፤ ለዜጎች የስራ እድሎችን እንዲፈጥርና የጤና አገልግሎት እንዲያስፋፋ የሚፈልጉ መሆናቸውን ሲኤንኤን አውስቷል፡፡
ከላይቤርያዋ ከተማ ጅብላርተር ጎስቋላ መንደሮች ተገኝቶ በዓለም እግር ኳስ ከፍተኛውን ክብር ሊያገኝ የበቃው ጆርጅ ዊሃ በስፖርቱ ዓለም ካለው የገዘፈ እውቅና እና ክብር ባሻገር ያን ያህል የፖለቲካ ልምድ ስለሌለው ለአገሪቱ አይመጥናትም በሚል የተቹም አሉ፡፡ የተጨዋችነት ዘመኑን ካበቃ በኋላ ከ2011 እኤአ ጀምሮ በቢዝነስ አመራር እና  በህዝብ አስተዳደር ሁለት ዲግሪዎችን ለመያዝ የበቃው
ዊሃ በላይቤርያ ፖለቲካ ያለው ብቸኛው ልምድ የዋና ከተማዋ ሞኖሮቪያ ሴናተር ሆኖ ነለ ዓመታት ያገለገለበት ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የዩኒሴፍ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ሆኖ ላለፉት 20 ዓመታት በተለያዩ ሰብዓዊ እና የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ተመስግኗል፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን  ከአሜሪካ ነፃነታቸውን አግኝተው ወደ አፍሪካ በመጡ ጥቁር ህዝቦች  የተመሰረተችው ላይቤሪያ 4.6 ሚሊዮን ሕዝብ ያለት ሲሆን፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ስታደርግ በ73 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ጆርጅ ዊሃ የላይቤርያ 25ኛው ፕሬዝዳንት ሆኖ ስልጣኑን የሚረከበው በአፍሪካ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ለ12 ዓመታት በስልጣን ላይ ከቆዩት ኤለን ጆን ሰርሌፍ ነው፡፡
ጆርጅ  ዊሃ የላይቤርያ ፕሬዝዳንት ለመሆን አስቀድሞ በሁለት ምርጫዎች ተወዳድሮ ነበር፡፡ የመጀመርያውን ምርጫ የተሳተፈው ከ12 ዓመታት በፊት ሲሆን በኤለን ጆን ሰርሌፍ የተሸነፈ ሲሆን፤ ከ6 ዓመታት በፊት ደግሞ ወደ ምርጫ ከገባ በኋላ የወከለው ‹‹ኮአሊሽን ኦፍ ዴሞክራቲክ ቼንጅ››ፓርቲ ከውድድር በመውጣቱ አልተሳካለትም ነበር፡፡
በእግር ኳስ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ዘመኑ በፈረንሳዮቹ ሞናኮ ፒኤስጂና ማርሴይ፤ በጣልያኑ ኤሲ ሚላን እና  በእንግሊዞቹ ቼልሲና ማን ሲቲ የተጫወተው ጆርጅ ዊሃ በ1995 እ.ኤ.አ. ላይ በአንድ የውድድር ዘመን የአፍሪካ፣ የአውሮፓ እና የዓለም እግርኳስ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኖ በመሸለም ከፍተኛ ስኬት ያገኘ አፍሪካዊ ተጨዋች ነው፡፡ በፈረንሳዩ ሞናኮ ከ1988 እስከ 1992 103 ጨዋታዎች 47 ጎሎች፤ ከ1992 እስከ 1995 በፒኤስጂ 96 ጨዋታዎች 32 ጎሎች፤ ከ1995 እስከ 2000 በኤሲሚላን 114 ጨዋታዎች 46 ጎሎች፤ በ2000 በውሰት ቼልሲ 11 ጨዋታዎች 3 ጎሎች እንዲሁም በማንችስተር ሲቲ 7 ጨዋታዎች 11 ጎሎች፤ በ2001 በማርሴይ 11 ጨዋታዎች 5 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡ ከፈረንሳዩ  ሞናኮ ጋር የኩፕ ደፍራንስ ዋንጫን ፤ ከፒኤስጂ ጋር የሊግ1፣ የኩፕ ደፍራንስ እዝና የኩፕ ደ ሊግ 3 ዋንጫዎች፤ ከኤሲ ሚላን ጋር ሁለት የስኩዴቶ ክብሮችን እንዲሁም ከቼልሲ ጋር የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫንም አሸንፏል፡፡

Read 1918 times