Tuesday, 02 January 2018 10:19

በ400 ሚ.ብር የተገነባው “ሮሪ” ሆቴል በሀዋሳ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(5 votes)

በሀዋሳ በ400 ሚ፣ ብር ተገንብቶ ከጥቂት ወራት በፊት ሥራ የጀመረው “ሮሪ” ኢንተርናሽናል ሆቴል ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚመረቅ ተገለፀ፡፡ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ አምስት አመታትን የፈጀውና ፊቱን ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዙሮ የተሰራው ሆቴል ለ230 ሰዎች የስራ እድል እንደፈጠረና ይህ ሆቴል “የአለታላንድ ቢዝነስ ግሩፕ” እህት ኩባንያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት አቶ ሀብታሙ ሲላ “አለታላንድ ኮፊ” የተባለ ታዋቂ የቡና ላኪ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ የፕላስቲክ እና ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በመክፈት ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠሩ ባለሀብት መሆናቸውን የሆቴሉ ገበያና ሽያጭ ጥናት ሀላፊ አቶ ሚሊዮን በላይ ገልፀዋል፡፡
ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ማሟላት የሚጠበቅበትን መስፈርቶች እንደሚያሟላ የሚነገርለት ሮሪ ኢንተርናሽናል ሆቴል፤ የተለያየ ደረጃ ያላቸው 100 የመኝታ ክፍሎች፣ የእስያ፣ የአውሮፓና የባህል ሬስቶራቶች ኬክና ፒዜሪያ ቤቶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የህፃናትና የአዋቂ መዋኛ ገንዳዎች፣ የህፃናት መጫዎቻ ቦታዎች ዘመናዊ ጂምናዚየም፣ የወንድና የሴት የውበት ሳሎኖች፣ ስቲም፣ ሳውና ጃኩዚ፣ 5 የተለያየ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ በመጠናቀቅ ላይ ያለ ግራውንድ ቴኒስ ያሟላ መሆኑን የገበያና ሽያጭ ጥናት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን በላይ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የሆቴሉ ስም “ሮሪ” በሲዳሞኛ “ሩጥ አሸንፍ፣ ብለጥ ከፍ በል” ማለት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2266 times