Tuesday, 02 January 2018 10:22

ከዩኒቨርሲቲ ምሁርነት እስከ ኢንቨስተርነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጆችን አስተምሬያለሁ
          • ህንፃ ሰርቶ የሚያከራይ ድርጅት አለን - ካፒታሉ 40 ሚ. ብር ደርሷል
          • የጥርስ ክሊኒኩ የፈጠረው መነሳሳት ሃብት አፍርቶልኛል

   አቶ እንግሊዝ ብያን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት እዚሁ አዲስ አበባ ተ/ሃይማኖት አካባቢ ነው፡፡ እድገታቸው ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ አዲስ ዓለምና ይርጋጨፌ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በከፍተኛ ነጥብ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ቢያገኙም አልዘለቁበትም፡፡ በአሜሪካ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደዚያው አቀኑ፡፡ በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ እንግሊዝ፤ እዚያው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡
ደርግ አብዮት አፈንድቶ የመንግስት ለውጥ ባደረገ ማግስት፣ በ1968 ዓ.ም ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡ ሆኖም በተማሩበት የፖለቲካል ሳይንስ ዘርፍ ለመስራት እንዳልቻሉ ያወሳሉ። ለረጅም አመታትም የሃገሪቱን የግብርና ዘርፍ ከመሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዱ እንደሆኑ የሚናገሩት ምሁሩ፤ ደርግ ከወደቀ በኋላም ከቅጥር ወጥተው በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማሩ፡፡ የመጀመሪያ ኢንቨስትመንታቸውም የጥርስ ክሊኒክ ነበር፡፡ ከዚያስ?  የ77 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ እንግሊዝ ብያን፤ ከረጅሙ የህይወት ጉዟቸው ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጥቂቱን ጨልፈው አውግተውታል፡፡

   ከፖለቲካል ሳይንስ ምሁርነት እንዴት ወደ ጥርስ ክሊኒክ  ኢንቨስትመንት ገቡ?
በነገራችን ላይ ክሊኒኮቹ ቦሌ እና ብስራተ ገብርኤል የጥርስ ክሊኒክ ይባላሉ፡፡ ክሊኒኮችን ብቻ ሳይሆን የጥርስ ሃኪም የሆኑ ሁለት ልጆችንም አፍርቻለሁ፡፡ ሁለቱ ልጆቼ፣ የጥርስ ህክምና ዶክተሮች ናቸው፡፡ እኔ የተማርኩት ደግሞ ፖለቲካል ሳይንስ ነው፡፡ በወቅቱ ፖለቲካል ሳይንስ የተማርኩት ፓርላማ ለመግባት ይጠቅማል በሚል ነበር፡፡ በተማሪነት ዘመኔ፣ የተማሪዎች ህብረት አመራርም ነበርኩ፡፡ ፖለቲካል ሳይንስ ባጠናም ወደ ሀገር ቤት ስመለስ ግን ጥቅም የለሽ ነው የሆነው፡፡
እንዴት ማለት? አልተጠቀሙበትም?
ለአንድ ቀን እንኳ በፖለቲካል ሳይንስ አልሰራሁም፡፡ የደርግ ሰዎች እንድሰራበት ቢጠይቁኝም ሁኔታው ስላልተመቸኝ አልሰራሁበትም፡፡ በቀጥታ የገባሁት ወደ ግብርና ስራ ነው፡፡ በፖለቲካው ውስጥ ባለመሳተፌ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ደርግ “የግብርና ባለሙያዎችን የሸረሸራችሁት እናንተ ናችሁ” በሚል ፈርጆን፣ ከጥቃት ያዳኑን አቶ ኃይሉ ሻወል ናቸው፡፡ በወቅቱ የግብርና ስራው በፖለቲካ ጫና ውስጥ ነበረ፡፡
በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሯቸው ታዋቂ  ኢትዮጵያውያን ነበሩ ይባላል?
እንዴ! በደንብ እንጂ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጆችን አስተምሬያለሁ፡፡ እንደውም ንጉሡ ከስልጣን ሲወርዱ፣ ልኡል መኮንን ወደ እንግሊዝ ሃገር እንዲሻገር የረዳሁት እኔ ነኝ፡፡ ሌሎችም አሉ፤ ዛሬ በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ በርካታ ናቸው፡፡
ግን ፖለቲካል ሳይንስ ተምረው እንዴት የጥርስ ክሊኒክ ለመክፈት አሰቡ?
ሰው በባህሪው ፈር አውጥተንለት፣ እንደ ውሃ በተቀደደለት ቦይ ብቻ የሚፈስ አይደለም። የኔም ህይወት እንዲሁ ነው፡፡ አስቀድሞ ወደ አሜሪካ ለትምህርት ስሄድ፣ ወላጆቼ ረድተውኝ ወይም አግዘውኝ አይደለም፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በእግዚአብሔር ኃይልና በራሴ ጥረት ነው ጥሩ ተማሪ ሆኜ የመጣሁት፡፡ ከ5ኛ ክፍል ወደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪነት የተሻገርኩት በ4 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ስኮላርሺፑም ሲደርሰኝ አንድ ዓመት እዚህ ሰርቼ፣ የሚያስፈልገኝን አሟልቼ ነው የሄድኩት፡፡ በአሜሪካ በነበረኝ የትምህርት ቆይታም ላመጣሁት ከፍተኛ ውጤት፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጌራርድ ፎርድ ሜዳሊያ ሸልመውኛል። ሽልማት አገኘሁ ብዬ ግን የስኬት ጫፍ አድርጌ አልወሰድኩትም ነበር፡፡ ዶክትሬቴንም ጀምሬ ነበር፤ በዚያው ዩኒቨርሲቲ፡፡ በኋላ የእናት ሀገር ጥሪ ሲቀርብ በደስታ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ አገሬ መጣሁ፡፡ ግን ስመጣ የጠበኩትን አላገኘሁም። ከዚያም በ1983 የመንግስት ለውጥ ሲደረግ፣ የተመሰረተው የሶዶ - ጎርደና ህዝብ የፖለቲካ ድርጅትን ተቀላቀልኩ፡፡ በኋላም ድርጅቱን ለቅቄ ጡረታዬን አስከብሬ በተቀመጥኩበት፣ አንድ የጥርስ ሃኪም መጥቶ፤ “እኔ አክማለሁ፤ እርስዎ ገንዘብ ያምጡ” አለኝ፡፡ እሺ ብዬ ያለችኝን ገንዘብ አውጥቼ፣ የቦሌ የጥርስ ክሊኒክን አቋቋምን፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ የጥርስ ክሊኒክ ነበር ያቋቋምነው፡፡
መጀመሪያ ላይ ገቢው እንዴት ነበር?
 እንዴ ምን ይነገራል! በቃ 40 ዓመት ለፍቼ ያላገኘሁትን ገንዘብ ነው ከጥርስ ሃኪም ቤቱ ያገኘሁት፡፡ በጣም ስኬታማ ነው የሆንኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ከክሊኒኮቹ በተጨማሪ በሌሎች ቢዝነሶች ላይም መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ዋልታ አክሲዮን ማህበር የሚባል ከወዳጆቼ ጋር የመሰረትነው ድርጅት አለን፡፡ ህንፃ ሰርቶ የሚያከራይ ነው፡፡ ካፒታሉ 40 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ለመግባት በመንገድ ላይ ነን፡፡ በግሌ ጣሊያኖች ትተውት የሄዱት አንድ ታፔሰሪ ድርጅት ገዝቼ፣ አሁን ጥሩ ገቢ እያገኘሁበት ነው፡፡ በወር እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ይሰራል፡፡ ምናለፋህ ብቻ … የጥርስ ክሊኒኩ የፈጠረው መነሳሳት ሃብት  አፍርቶልኛል፡፡ ግን ሁሌ ቅር የሚለኝ … ጥሩ ፀሐፊና ፈላስፋ ሆኜ ሳለ፣ በዚህ በኩል አለመግፋቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የህይወት ታሪኬንና ተሞክሮዬን እየፃፍኩ ነው፡፡
በቅርቡ የወጣውን “ክስታንኛ - አማርኛ - እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት”፣ በ300 ሺ ብር ወጪ ያሳተሙት እርስዎ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡ ከፍተኛ ወጪ ነው --- እንዴት ሊያሳትሙት ተነሳሱ?
በመጀመሪያ የክስታኔ ልማት ማህበርን ነው ያቋቋምኩት፡፡ ይሄ ማህበር ደግሞ የሶዶ ጎርደና ህዝብ የፖለቲካ ድርጅት መፍረስን ተከትሎ የተቋቋመ ነው፡፡ እዚህ የልማት ማህበር ውስጥ ካሉ ትልልቅ እቅዶች አንዱ ደግሞ የማህበረሰቡን ቋንቋ ማሳደግ ነው፡፡ ቋንቋውን ለማሳደግና ለትውልድ ለማስተላለፍ ደግሞ አንዱ መሳሪያ መዝገበ ቃላት ማሳተም ነው፡፡ በዚህ አላማ ነው 3 መቶ ሺህ ብር ወጪ አድርጌ መዝገበ ቃላቱን ያሳተምኩት። የማህበረሰቡን ባህልም ለማጥናት ሞክሬያለሁ፡፡ ይህን መዝገበ ቃላት ማሳተም ያስፈለገውም ህዝቡ እንዲጠቀምና የምርምር መሳሪያ እንዲሆን ነው፡፡
የቋንቋ ነገር ከተነሳ አይቀር---- የክስታኔና የኦሮሚኛ ቋንቋ ተቀላቅሏል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እውነት ነው?
መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው፣ በሀገራችን ያልተቀያየጠ ብሄር የለም፡፡ ክስታኔንም ብንወስድ ሶስት አራተኛው ከኦሮሞ ጋር የተቀላቀለ ነው፡፡ አንድ አራተኛው ደግሞ ከአማራና ከተለያዩ ብሄሮች ጋር ተቀላቅሏል፡፡ እኔ ለምሳሌ አያት ቅድመአያቶቼ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ የአብዛኛው ክስታኔ የዘር ሃረግም ሄዶ ሄዶ፣ የኦሮሞ ዝርያ ይገኝበታል፡፡ ይሄ የመጣው ደግሞ በጋብቻ ነው። ክስታኔ ከኦሮሞ፣ ኦሮሞ ከክስታኔ ጋብቻ ይፈፅማል። ስለዚህ የክስታኔና የኦሮሚኛ ቋንቋ መቀላቀል አይገርምም፡፡

Read 2718 times