Tuesday, 02 January 2018 10:07

ያልታየ ዕድል!

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 በመረረ ሀዘን ውስጥ እያለፈም ደስተኛ ነበር። በለቅሶ ሸለቆ መሀል፤ በሰቀቀን እንብርት ቆሞም መሣቅ ይችላል፡፡ በተለይ በትዳሩ ደስተኛ ነው። አንድ ልጁ ደመቀ ከመጣ ወዲህ ደሞ በጊዜ ቤቱ ገብቶ የልጁን ሁለት ጥርሶች ፈገግታ ሲያይ፣ ሁሉንም ነገር ይረሳዋል፡፡ ባለቤቱ በቀለችም መልካም ሰው ናት። አንዳንዴ ፊቱን ፀሀይ አክስሎት፣ አሻሮ መሥሎ ሲመጣ፣ ኮቱን ተቀብላ፤ ስማ፣ የሞቀ የእግር ውሃ ታቀርብለታለች፤ ያኔ ደስታው ሀዘኑን ይዳምጠዋል።
ከሠፈር ሲወጣም የሠፈሩን ደብር ተሣልሞ፣ “በቀኝ አውለኝ” ይላል፡፡ ዛሬ ግን በቀኝ አውለኝ ብሎ ወጥቶ ፣ በግራ ነው የዋለው፡፡ የቀጠረው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፣ ያልሆነ ነገር ተናግሮታል፡፡ በዚያ ላይ ጉርሻ የሚባል ነገር አልቀመሰም፤ እንዲያውም ጠዋት ሲወጣ፣ የልጁን ጡጦ ለመቀየርና ካናቴራ ነገር ሊገዛም አስቦ ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡
ቀን አሥር ሰዐት ላይ ነበር ግምገማቸው። የሥራ ባልደረባው ታደለ፣ ከርሱ በፊት ሥራ አስኪያጁ ቢሮ ሲገባ ፈገግ ብሎ ነበር ያየው፡፡ ሲወጣም እንደዚያው ደስተኛ ነበር፡፡
እርሱ ሲገባ ግን የአለቃው ፊት ልክ አልነበረም። ከዚያም “ባለፈው ወር ምሥጉን ሰራተኛ አንተ ነበርክ፤ አሁን ግን ቁልቁል ወርደሃል፤ ስለዚህ የመጨረሻ ማሥጠንቀቂያ ነው፡፡… ሥራህን በደንብ ካልሠራህ የልጅ አባት ነኝ፤… የቤተሰብ ሃላፊ ነኝ---ማለት ተቀባይነት የለውም፡፡” አለው፤ሥራ አስኪያጁ፡፡
ጭንቅላቱ ሁለት ቦታ ተከካ፡፡
“ምንድነው ጥፋቴ?”
“ጥፋትህን እንደማታቅማ አትሁን!”
“እንዴት እያወቅኩ በእንጀራዬ እቀልዳለሁ!?”
አለቃው ጠረጴዛውን በእስክርቢቶ እየቀበቀበ፤ “…የተፈጠረልህ ዕድል አልገባህም፤ ምን ዐይነት ታላቅ ሥራ እንደሆነ  አላስተዋልክም…..”
አቀርቅሮ ዝም አለ፡፡ ሥራ ቢያገኝ፤ መቀየር ይፈልጋል፡፡ ግን ሥራ የለም፤ ሥራውን በግዱ ለምዶታል እንጂ እንደ ጥሩ ዕድል አያየውም፡፡
“ከትናንት ወዲያ ያስቀበርካቸው ሰው ምን እንደሆኑ ታውቃለህ?”
“ጭምጭታ ሠምቻለሁ፣ አሜሪካ ሀገር የኖሩ ፕሮፌሰር ናቸው አሉ…”
”እርሳቸውን የሚያህል፣ ሀገር የሆነ ሰው፣ ለማስቀበር ብቃት አለኝ ብለህ ታምናለህ?”
“በፍፁም!”
“የስንተኛ ክፍል ተማሪ ነህ?”
“አምስተኛ”
“አየኸው ልዩነታችሁን!”
አቀርቅሮ ለአፍታ በዝምታ ከቆየ በኋላ፤ “…ምንድነው ጥፋቴ ግን…?”
“ጥፋትህ…ጥፋትህ?”
በዓይኖቹም በጆሮዎቹም ጠበቀ- መልሱን፡፡
“አንደኛ…”
“አ?
“አስክሬን ተሸክመህ በፈገግታ መዋልህ፤ ያን ያህል የሀገር ዋርካ ወድቆ ጠላትህ የሞተ ይመስል…”
“እኔ ግን ፈገግ አላልኩም፣ እንዲያውም እህትየው በጣም ሲያለቅሱ ሆዴ ባብቶ እንባዬ ሲመጣ.. ሀሳቤን ወደ ትንሹ ልጄ ወሰድኩትና የጥርሶቹ ፈገግታ ሲታሰበኝ፣ ምናልባት ፈገግ ብዬ ይሆናል፡፡ ሌላ ምን ፈገግ የሚያሰኝ ነገር አለ? ያው ልጄ ነው። ለሥራ የሚያበረታኝም፣ የሚያነቃቃኝም እርሱ ነው፡፡ ከወለድኩ በኋላ… ህይወቴ ተለውጧል፡፡”
“ባትወልደው ይሻላል…”
“ለምን ጌታዬ…ፈጣሪ የሰጠኝን…”
“እርሱም እንዳንተ ሬሳ ተሸክሞ የሚሥቅ ጅል ነዋ የሚሆነው!”
ሀዘን ልቡን ሰበረው፡፡ ሥራውን ጥሎ ሊወጣ አስቦ ነበር፡፡ የቤት ኪራዩ፣ የልጁ ነገር፣ የሚስቱ ህይወት..ገታው፡፡
ስድብ ጠገበ፡፡ ዘለፋና ንቀት ፈሰሰበት፡፡
“የዛሬ ስድስት ወር የሞቱት ፕሮፌሰር ወንድም ግን ሸልመውኝ ነበር፡፡…” አለና፤ ከአፉ ያመለጠው ያህል  ደንግጦ ዝም አለ፡፡
“ዕድለኛ ነህ አልኩህ’ኮ!... ከፕሮፌሰሮች ጋር ትውላለህ”
“ኡይ ጋሽዬ --- ሰርግ ላይ እኮ አይደለም፣ ቀብር ላይ ነው፡፡ በለቅሶ ላይ ማንም ይገኛል፡፡ ሥልጣንና ዕውቀትም አይደለም፡፡ የኔ ቢጤውስ ይመጣ የለ!?”
“አይደለማ! አንተ’ኮ… የታላላቅ ሰዎችን አስክሬን ትሸከማለህ፤ የህይወት ታሪካቸው ሲነገር ታደምጣለህ፡፡ ላንተ ዩኒቨርሲቲ ነው ይሄ ዕድል!... እኔ አሜሪካ የኖርኩት፣ የሰው ሽንት ቤት እያጠብኩ ነው--”
“ሬሳ መሸከም ዕድል ነው ጋሼ?”
“የማንም ድሃ ሬሳ እንዳይመስልህ… የምትሸከመው..”
“…ቄሱ፤ ከሞተ አንበሳ በህይወት ያለ እንትን ይሻላል ነበር ያሉት--”
“በቃ ዝጋ!  ልታስተምረኝ ነው!”
ሀገር ቤት ሄዶ ሚስቱን በቀለችን ያገባበት ቀን ትዝ አለው፡፡ ሙሽራ ሆኖ ኮትና ሱሪ አድርጎ፣ ቬሎ ያጠለቀች ሚስቱን ዐይነ ርግብ ገልጦ ሲስማት፣ እልልታው አሰከረው፡፡ እልልታና ሣቅ ከረሳ ቆይቷል፡፡ ውሎው ለቅሶ ነው፤ ቀብር ነው፡፡ ድንግርግር አለው፡፡ ሙሾውን እንደ ዘፈን ለምዶታል፤ ብዙ ግጥሞችም ያውቃል፡፡ በተለይ ከባላገር የመጡ አልቃሾች፣የሚደረድሩት ቅኔ ያሥደንቀዋል፡፡
ኸረ ሚዜው ደሃ ነው፤ ሽቶው ውሃ ነው፡፡
ክንዱን በክንድዋ ቆልፎ ወደ መኪና ሲገባም ተዐምር ነበር የሆነበት፡፡ በልቡም ሥራ ሊቀይር አሥቦ ነበር፡፡ ሚስቱ እስካሁን ሥራውን አታውቅም፡፡ መርካቶ የሚሠራ ነው የሚመሥላት፡፡ አንዳንዴ በጎ ሰዎች አግኝተው፣ ጉርሻ የሰጡት ቀን፣ ሥጋ ይዞ ሲገባ፤ ብርቱካን ሲሸምት-- በለስ የቀናው ይመሥላታል፡፡
አንዴ በተለይ ሚኒስትር የነበሩ ሰው ቀብር ላይ አስከሬናቸውን ተሸክሞ ሄዶ፣ ሥርዐተ ቀብር ከተፈፀመ በኋላ ስለ ሰውየው ታሪክ ሲሰማ፣ እንባውን መቆጣጠር አቃተው፡፡ ጓደኞቹ ሁሉ የጎሪጥ እያዩ በትዝብት አላገጡበት፡፡ ኋላ እንደሚተርቡት አሰበ። ግን ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡
በተለይ ሰውየው በየገጠሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ያደረጉትን ጥረት፤ ከሥራ ጊዜያቸው በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው ሳይቀር፤ የገጠር ትምህርት ቤቶችን እየጎበኙ፣ ጎበዝ ተማሪዎች እንዲሸለሙ በማድረግ፣ የድሀ ልጆችንም በግላቸው እየረዱ፣ የህይወት ዘመናቸውን እንደፈፀሙ ሲሰማ አለቀሰ፡፡
“የዚህ ዐይነት ሰው ቢገጥመኝ፣ዛሬ እኔ እዚህ አልገኝም ነበር፡፡” ብሎ ነው - ለራሱ ያለቀሰው፡፡
መጨረሻ ላይ የሚኒስትሩ ወንድም ወደ ቤት ሊመለሱ ሲሉ፣ በእጅ ምልክት ጠሩትና፣ በጆሮው “አንተ ትልቅ ሰው ነህ፤ ልብህ እንዴት እንደተነካ አይቻለሁ፤ ወንድሜ እንዳንተ ላሉት ምስኪኖች ኖሮ የሞተ ወገን ወዳድ ነበር!” ብለው አምስት መቶ ብር በትንሽ ፖስታ ጠቅልለው በእጁ አሥያዙት፡፡ ደነገጠ፡፡ ድንጋጤው ለረጅም ሰዓታት አልለቀቀውም ነበር፡፡ የዛሬ ወር ገደማ---
እጁን የኋሊት አድርጎ በሀሳብ ጭልጥ እንዳለ፤ “ይህ የመጨረሻ ዕድልህ ነው!... አሁን መሄድ ትችላለህ!” አለው አለቃው፡፡ መረረው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያ ሁለት ጥርሶቹን ብልጭ የሚያደርግ ልጁ ትዝ አለው፡፡ የህይወቱ ተስፋ፣ የመኖሩ ጉልበት እርሱ ነው፡፡
ባለቤቱ በተራዋ ፊቱ ድቅን አለችበት፡፡ እያሰላሰለ  አጎንብሶ ሲወጣ፤
“ምን አለህ?...ምን አለህ?” አሉት ጓደኞቹ፡፡
መልስ አልሰጠም፡፡ “በቃ፤ ከዛሬ ጀምሮ ሬሳ አልሸከምም!” ብሎ በቀጥታ ወደ ቤቱ አመራ፡፡
 ቤት ሲሄድ፤ “ምነው በዛብህ! ሥራ የለም እንዴ?”
በዝምታ ፊቱን ወደ ግድግዳ መልሶ ተኛ፡፡ ልጁም አልጋው ጥግ ላይ ተኝቷል፡፡
እንቅልፉ እምቢ ሲለው፣ ጉርሻ የተቀበለበትን ፖስታ ድንገት ከኪሱ አገኘው፡፡ ለካ ውስጡ ያላያት ብጣሽ ወረቀት ነበረች፡፡  
“እንዳንተ ላለው ሀገር ወዳድ ወጣት፣ ልቤና በሬ ክፍት ነው፡፡ ደስ ባለህና ሥራ በፈለግህ ጊዜ “አድማስ” የተባለው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ብቅ በል፡፡ ስልጠና ላዘጋጅልህ ፍቃደኛ ነኝ--”
እንደ እብድ ብድግ ብሎ ከቤቱ ወጣ፡፡ ለካስ ዕድል አለ!!

Read 2728 times