Print this page
Tuesday, 02 January 2018 10:00

“ስኳር ስኳር--- አለኝ” - (ፖለቲካዊ ወግ)

Written by  (ሶ.አ)
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ናችሁልኝ?  ከውጪ ተገዝቶ ወደ ሀገር ቤት ከገባው በርካታ ኩንታል ስኳር ውስጥ ሶስት ሺ ሰባት መቶ ሰባ ሰባቱ መበላሸቱ ከሳምንት በፊት  በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተዘግቧል፡፡ ይሄ ክስተት የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ከወራት በፊት የተወሰኑ ሰዎች ከ40,000 ኩንታል በላይ ስኳር ሲያዘዋውሩና ሊሸጡ ሲሉ ስኳሩ እንደተያዘ ሰምተን ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ስኳር በረሃ ላይ ለሳምንታት በመቆየቱ፣ ለመቅለጥና ለመበላሸት በቅቷል። ከወራት በፊት ጀምሮ ደግሞ ስኳር ከነጭራሹ ከገበያ እንደጠፋች ታውቃላችሁ፡፡ (እንኳን እናንተ እኔም አውቄያለሁ!!)…
በዚሁ ወቅት (የዛሬ ሁለት ወር አካባቢ)… ከጥቅምት 18 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአምቦ ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎችና በታጠቁ ኃይሎች መካከል በተነሳው ግጭት ሰዎች መሞታቸውን አትዘነጉም፡፡ የረብሻው ወይም የተቃውሞው መነሻ ምክንያት ስኳር ጭኖ ያልፍ የነበረ መኪና እንደሆነም ተገልፆ ነበር፡፡ ያኔ ቄሮ መኪናውን አስቁሞ ስኳሩን አራግፏል፡፡ (ርግፍ! እርግፍ!) በዚህ የተነሳ የታጠቁ ኃይሎች፣ ባልታጠቁ ዜጎች ላይ ተኩሰው፣ ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ (ወዳጆቼ፤ ዘንድሮ ሞት እንዴት ቀሏል መሰላችሁ?)
እንግዲህ ስኳርም ፖለቲካ ሆነች ማለት ነው። ትሆናለች እንጂ!... እንዴት አትሆንም?!... ስኳርም ፖለቲካ ናት፡፡ ለነገሩ አሁን ፖለቲካ ያልሆነ ምን ይገኛል? ሁሉም ከቦተለኩት ፖለቲካ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሀገርና ህዝብን የሚመራው መንግስት ነው፡፡ ስለ መንግስት ማውራት ፖለቲካ ከሆነ፣ ስለ ህዝብ ማውራትም ፖለቲካ ነው፡፡ ስለ ህዝብ ማውራት ፖለቲካ ከሆነ፣ ህዝቡ አጥብቆ ስለሚፈልገው ዛሬ ግን ስላጣው ስኳር ማውራትም ፖለቲካ ነው፡፡ ለነገሩ ፖለቲካ ያልሆነ ምን አለ? አንዳንዴ ህይወት ራስዋ ፖለቲካ ትሆናለች፡፡
ኒውተን “for every action, there is reaction” ማለቱ ትክክል ነው፡፡ እንኳን ሰው ይቅርና ግድግዳም ራሱ በቡጢ ስንመታው ዝም ብሎ አይመታም። የሆነ ዓይነት ምላሽ አለው፡፡ እጃችንን ሊያመን ይችላል፡፡ እጃችን ሊላላጥ ይችላል፡፡ እጃችን ሊዝል ይችላል፡፡… ስለዚህ ማንኛውም ሰው ሲረግጡትና ሲጨቁኑት ለተወሰነች ጊዜ ታግሶ ያሳልፍ ይሆናል እንጂ እርግጫውና ጭቆናው ሲበዛበት ማመፁ አይቀርም፡፡ (ድብን አድርጎ ያምፅ!!) አሻፈረኝ ብሎ ከወደቀበት ወይም ከተንበረከከበት ይነሳል፡፡ (ብድግ!) ይነሳና ምላሽ ይሰጣል፡፡ እሱም ወይ መልሶ ይራገጣል ወይ ጨቋኙን ፈንግሎ ይጥላል፡፡ (ዘጭ!) ቢያንስ ቢያንስ የረጋን እግር ወዲያ መወርወሩ የሚቀር አይደለም፡፡ (ውርውር!)
“ስኳር ስኳር አለኝ ብቀምሰው ከንፈሩን” ብላ አዚማ ነበር፤ አቀንቃኝዋ፡፡ አሁን ግን ይሄ ዘፈን ወይም የዚህ ዘፈን ግጥም መቀየር ሊኖርበት ነው። ስኳር ጠፍታ የስኳር ጣዕም ተረስቶናልና አስቴር ዘፈንዋን ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ እንዴት? እንዲህ፡- “...ጨው ጨው አለኝ ብቀምሰው ከንፈሩን” (ሃ-ሃሃ… ይሄም ጨው ከገበያ እስክትጠፋ ድረስ ነው። እሷም “ወጉ ደርሷት” የጠፋች ቀን ደግሞ ሌላ ትዘፍናለች።) መዝፈን ያለባትን ግጥም ምንነት፣ ያኔ ጠቆም እናደርጋለን፡፡ ለማንኛውም ስለ ስኳር መጥፋት ማውራት ብቻ ሳይሆን “ፅድቁ ቀርቶብን በወጉ በኮነነን” እያልን ጨውም እንዳይጠፋ ደጀ ሰላሙን መሳለም ግዴታችን ሳይሆን  አልቀረም፡፡
እስቲ ደግሞ ሰዎች  እየጠቀስንና የወቅቱን ሁኔታ እያዛነቅን ወደ መቦትለኩ እንለፍ፡፡
ስኳር የራስዋ ታሪክ አላት፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ማለቴ ነው፡፡ ስኳር ብዙዎችን አሳስራለች፡፡ በደርግ ጊዜ በህብረት ሱቅ  ተወስና ከዛ ተቸብችባለች። በኢህአዴግ ጊዜ በሸማቾች ማህበር በኩል ተከፋፍላለች፡፡ ቡናና ሻይ ስር ስትውል፣ ከዳቦ ላይ ጠብ ስትደረግ ወዘተ  እጅ ታስቆረጥማለች፡፡
የቀድሞው የብአዴን አመራርና ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት  አቶ ታምራት ላይኔ፤ በዚችው ስኳር ሰበብ ወህኒ መውረዳቸው ይታወቃል። (ወረዱ እየተንገዳገዱ… ሄዱ እየተወላገዱ…ዱ…ዱ…ዱ…) በወቅቱ ስለ ታምራት ሃጢያት የተናዘዙትና ስለ ወንጀላቸው የተናገሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ተው ተው አልነው፤ መከርን አስመከርነው፤ እሱ ግን ስኳሯን ለምዶ…ስለጣፈጠችው እምቢኝ አለ…”
አቶ ታምራት የታሰሩት ስኳር ሸጠው አሻሽጠው፣ ንግዷንም አጧጡፈው ነው ይባላል። በርግጥ ምክንያቱ ሙስና ሳይሆን ፖለቲካዊ እንደነበርም የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ አቶ ታምራት በስኳር ምክንያት ለ14 ዓመት ለመቀፍደድ በቅተዋል፡፡
ስኳር ታሪካዊ ናት፡፡ ስኳር ዝነኛ ናት፡፡ ስኳር…
ይህች ስኳር አሁን ከገበያ ጠፍታለች (ጥፍት እንደ ዳይኖሰር!!) በእኛ እድሜ እንኳን ከ2 ብር ከ50 ጀምሮ እንዳልተሸጠች፣ ዛሬ በኪሎ 60 እና 70 ብር ገብታለች፡፡ (ሰው ሻይንም በጨው መጠጣት ጀምሯል አሉ! ሃሃሃሃሃሃሃ) አጃኢብ ነው!... አታዳንቁም?!! መንግስት ምን እየሰራ ነው?!....አትጠይቁም?!!
በነገራችን ላይ በዓይነቱ ለየት ያለ አንድ መጽሐፍ ልፅፍ እያሰብኩ ነው፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ “ስኳርና የኢትዮጵያ እርምጃ” የሚል ይሆናል። እንዴት ነው አልተመቻችሁም?! ካልደላችሁ መቀየር እችላለሁ፡፡ በቃ ርዕሱን “የስኳር መጥፋትና የመንግስት እርምጃ” እለዋለሁ፡፡  ሌላው ግልፅ ነው፤ ትንሽ ሊሰወርባችሁና ግራ ሊያጋባችሁ የሚችለው ‹እርምጃ› የሚለው ቃል ነው፡፡
‹እርምጃ› መንግስት ከሚለው ቃል ቀጥሎ ሲመጣ ትርጉሙ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚያቅታችሁ አይመስለኝም፡፡ የመንግስት ‹እርምጃ› ያው ‹እርምጃ› ነው፡፡ እናንተ ሰዎች እኮ እንደ ዋዛ ልታስጠቁሩኝ ነው፡፡ እባካችሁ ስሜን አታበላሹ!... ‹እንኳን ስምህ ክብርህም ተበላሽቷል። እንኳን ስም ሀገርም ተንኮታኩቷል› ያላችሁኝ መሰለኝ፡፡ እርግጥ ነው፤ አልተሳሳታችሁም!.... ሀገር ተንኮታኩቷል!!...
እዚህ ጋ ደግሞ እንደገና ሌላ የፈጠራ ሀሳብ መጣልኝ፡፡… እንዴት ነው?.... ተደራጅተው ኮብል ስቶን እንደሚያነጥፉት ተደራጅተን ስኳር ማምረት ብንጀምርስ?! (እዛ ማን አድርሶን እላችሁ?!!... ጥሩ ብላችኋል!!!... ሃሃሃሃሃ) ለማንኛውም ፈጣሪ ስኳሪቱን ወደ ገበያና ወደ ጓዳችን እንዲመልስልን እንፀልይ!!!... ያለን ብቸኛ መሳሪያ ፀሎት ነው!!... አይመስላችሁም ወዳጆቼ?!

Read 3489 times