Monday, 01 January 2018 00:00

ውይይት ያለ እውነት፣ ክርክር ያለ ሃሳብ - ገበያ ያለ ምርት!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(10 votes)

• ፉክክር ማለት፣… ይሄኛው ዘራፍ እያለ ሲፎክር፣ ያኛው እያቅራራ ይፎክራል። የመገንደስና የመደምሰስ ፉከራዎች!
  • ክርክርስ (ክር-ክር)?… ከወዲህ፣ መከርከር መገዝገዝ እየበረከተ፤… ከወዲያኛውም፣ መከርከርና መተንፈሻ ማሳጣት እየገነነ!
    
    ውድድር ማለት፣… ማዋረድ፣ መዋረድ፣ መወራረድ የሚሆንብን፤… በየእለቱ የሚወደሰው “ውይይት” የተሰኘው ነገር ደግሞ፤… በዋይታ የምንወጋገዝበት፣ የ“ወዮልህ” ዛቻ የምናዥጎድግድበት የመዓት ድግስ የሚሆንብን ለምን ይሆን?
ትልቁና ዋናው ምክንያት ይሄ ነው - የትውልድ ቦታው በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ቢሆን፣ የትውልድ ሃረጉ የትም ቢመዘዝ ቢተረተር፣ ፆታው ምንም ሆነ ምን፣ ያኛውን እምነት ትቶ ያኛውን የሃይማኖት አይነት ቢከተል እንኳ፣… የንግግሩን እውነትና ውሸትነት፣ የሃሳቡን ትክክለኛነትና ስህተትነት… በመንግስት መግለጫ፣ በፓርላማ ውይይት፣ በፓርቲ ግምገማ፣  በኢቢሲ ዝብዘባ፣ በፌስቡክ ዘመቻ፣ በፓርቲዎች ክርክርና ድርድር፣ በሕዝብ ድምፅና በተቃውሞ ሰልፍ… የሚለወጥ፣ የሚሰረዝ፣ የሚወሰን ጉዳይ አይደለም። እንዲሆን ስንመኝ ወይም ደንታ ቢስ ስንሆን ነው ችግር የሚፈጠረው።  
በየትኛውም ቋንቋ ቢናገር እንኳ፣ ሃሰት ተናግሮ እውነት ሊሆንለት፣ ስህተት ተናግሮ ትክክል ሊሆንለት ይችላል? አይችልም። እውነት ተናግሮ፣ ሃሰት ሊሆንበት ይችላል? አይችልም። ትክክለኛ ሃሳብም፣ ስህተት ሊሆንበት አይችልም። ምናለፋችሁ! የቀንና የማታ ኡደት፣ የፀሃይ ብርሃንና የከዋክብት ብርቅርቅታ አይቀይርም። የተጨባጩ ዓለም እውናዊነት… “እውን”ነት አይለወጥም። ለምን? እንድገመው፤ ይሄ በመንግስት መግለጫ፣ በፓርላማ ውይይት፣ በፓርቲ ግምገማ፣  በኢቢሲ ዝብዘባ፣ በፌስቡክ ዘመቻ፣ በፓርቲዎች ክርክርና ድርድር፣ በሕዝብ ድምፅና በተቃውሞ ሰልፍ… የሚለወጥ፣ የሚሰረዝ ጉዳይ አይደለም። የመረጃ እውነተኛነት የሚረጋገጠው፣ ከእውኑ ተፈጥሮና ከእውኑ ክስተት ጋር በማመሳከር ነው - በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣… አይቶ በማስተዋል፣ ማስረጃዎችን በመመልከት፣ በማመሳከርና በማረጋገጥ ነው - እውነትና ውሸትን መለየት የሚቻለው - ሳይንቲፊክ ሜትድ እንዲሉ።
ለነገሩ፣ ጠቃሚና ጎጂ፣ ተገቢና አጥፊ፣ ጥሩና መጥፎ፣ አትራፊና አክሳሪ፣ ስኬትና ውድቀት፣ የከበረ እና የወረደ፣ ብቃትና ድክመት፣ ጥንካሬና አቅመቢስነት፣ የበቃና የከፋ… እነዚህን ሁሉ ለይተን ማወቅ፣ አውቀንም መምረጥና ማስቀረት፤ ማድነቅና መተው፣ የምንችለውም፣… ከሁሉም በፊት እውነትንና ውሸትን፣ ትክክልና ስህተትን፣… በእውኑ ተፈጥሮና በእውን ክስተት ላይ የተመሰረተና የቆመ እንደሆነ እስከተቀበልን ድረስ ነው።
በአገራችን እጅጉን እየገነነ የመጣው ግን፣ የዚህ ተቃራኒ ነው።
በቃ፣… አንድ መረጃ… “እውነት ነው” ተብሎ የሚረጋገጠው፤… ወይም “ውሸት ነው” ተብሎ የሚብጠለጠለው“፤… አንድ ንግግር፣… “ትክክል ነው” ተብሎ ወይም “ስህተት ነው” ተብሎ የሚወሰነው፤… ከእውን መረጃ ጋር በማመሳከር፣ ከማስረጃ ጋር በማስተያየት ነው? በአብዛኛው አይደለም። በጩኸት፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በዘር፣ በቲፎዞ፣ በጭፍን እምነት፣ በስድብ፣ በአፈና፣ በማስፈራሪያ… እውነት በሃሰት እንዲቀየር፣ ሃሰት ወደ እውነት እንዲለወጥ እምንመኝ ይመስላል። ለዚህም ነው፣ አብዛኛው ውይይት፣ ቀስ በቀስ፣ በጭፍን ወደ መቧደን፣ ወደ ስድብና ዘለፋ፣ ወደ ጥላቻና ዛቻ፣ ወደ አፈናና ወደ ብጥብጥ እየተንደረደረ የሚዘቅጠው።
ውይይት ማለት በዋይታ የተሞላ ወይም ወዬልህ አይነት ዛቻ ሆኖ ያርፈዋል። ክርክር ማለት ደግሞ እየከረከሩ መጣል እንደማለት ይሆናል። ክር-ክር፣… ከወዲህ በኩል፣ መከርከር፣ መገዝገዝ እየበረከተ ይመጣል። ከወዲያኛው በኩልም፣ መከርከር፣ መተንፈሻ ማሳጣት እየገነነ ይሄዳል።
አንድ ድርጊትና እቅድ፤… “ጠቃሚ ነው፣ ተገቢ ነው፣ በጎ ነው” ተብሎ ፋይዳው የሚታወቀው፣ ወይም “ጎጂ ነው፣ ጥፋት ነው፣ ነውር ነው” ተብሎ የሚወቀሰው፣ የሚንቋሸሸው፣… በእውነተኛ መረጃ አማካኝነት፣ የሰው ተፈጥሮንና ሕይወትን መሰረት በማድረግ ነው? በአብዛኛው አይደለም።
ለዚህም ነው“ ፉክክር ማለት፣ ፉከራ በፉከራ ሆኖ የሚጠናቀቀው። ያኛውም ዘራፍ እያለ ይፎክራል፣ ይሄኛውም እያቅራራ ይፎክራል። የመገንደስና የመደምሰስ ፉከራዎች አገር ምድሩን ያጥለቀልቁታል።
አንድ ባህርይና ዝንባሌ፣… “ድንቅ ነው፣ ግሩም ነው፣ ክቡር ነው” ተብሎ የሚወደሰው ወይም “መናኛ፣ አስቀያሚ፣ ክፉ” ተብሎ የሚዋረደው… በእውነተኛ መረጃ አማካኝነት፣ የሰው ተፈጥሮንና ሕይወትን መሰረት በማድረግ፣ የእያንዳንዱን ሰው የግል ማንነትና ባህርይ፣ ብቃትና ጥንካሬን በመመዘን፣ እጅጉን ከምናከብረው ቅዱስ የግል ሰብእና ጋር በማነፃፀርና በማወራረድ አይደለም። በጩኸት፣ በፕሮፓጋንዳ፣ በዘር፣ በቲፎዞ፣ በጭፍን እምነት የመቧደን ጉዳይ እንዲሆን እናደርገዋለን። ለዚህም ነው፤ ውድድር ማለት፣… ማዋረድ፣ መዋረድ፣ መወራረድ… የሚሆንብን።
ነገሩን ሁሉ ደላልዘን፣ አመሳቅለን፣ ቁልቁል ደፍተን ስናበቃ፣… የቃላት ትርጉምም እንዲሁ የድብስብ፣ የድንግዝግዝ፣ የተገላቢጦሽ ይሆኑብናል።     

ውይይት ያለ እውነት፣ ክርክር ያለ ሃሳብ - ተጠቃሚነት ያለ ምርት፣ ግብይት ያለ ንብረት ባለቤትነት

ዛሬ ዛሬ፣ የመንግስት መግለጫዎችን፣ የፖለቲከኞች ንግግርን ብትሰሙ፣ በተደጋጋሚ የምታኟቸው ተመሳሳይ አባባሎች… “የሕዝቡ ጥያቄ፣ ፈጣን ምላሽ፣ ውይይት…” የሚሉ ናቸው።
ምን አይነት ሃሳብ የያዘ ጥያቄ? ማንኛውም አይነት ጥያቄ!?
በፍጥነት ምን አይነት ምላሽ? ማንኛውም አይነት ምላሽ?
 ምን አይነት እውነታዎችና መርሆች ላይ የተመሰረ ውይይት? በምን መለኪያ የሚመዘኑ ሃሳቦች የሚቀርቡበት ምን አይነት ክርክር?
እነዚህ ጥያቄዎች በሙሉ፣ ገና ድሮ ተጠይቀው፣ መልስ የተገኘላቸው እናስመስላለን። ከጥያቄዎቹ ለመሸሽ የሚደረግ ራስን የማታለል ልማድ ነው - የማያዛልቅ መጥፊያ ልማድ።   
መገበያየት ስንል፣ የሚጠቅም፣ ፋይዳ ያለው ነገር አቅርቦ በመሸጥ፣… በዚህም አማካኝነት ፋይዳ ያለው ጠቃሚ ነገር ለመግዛት እንደሆነ እንደመዘንጋት ነው። አንዱ ጤፍ ይዞ ቢመጣ፣ ሌላኛው ገለባ፣ አንዱ ከሰል፣ ሌላኛው አመድ፣ አንዱ ከብት፣ ሌላኛው እበት ይዞ ቢመጣ ደንታ ሳይሰጠን፣ ሁሉንም በእኩልነት አይተን፣ ብዝሃነትን በደስታ ተቀብለን መገበያየት! ዋናው ነገር መገበያየት! በቃ፣… ሁሉንም ያሳተፈ ግብይት!
ጠቃሚ እና ፋይዳ ያለው ምርት… የሚባለውን ነገር እንርሳው።… ምርትን መገበያየት ሳይሆን፣… በቃ… “መገበያየት”፣ “ግብይት” ብለውን በቁንፅል! አንደኛው ገበያተኛ፣ ሁለት ኩንታል ጤፍ ይዞ መጥቷል። ሌላኛው፣ ባዶ ከረጢት ይዞ መጥቷል። አዎ የያዙት ነገር ይለያያል። ግን፣ ልዩነታቸው፣ ብዝሃነት ነው። ለያዙት ነገር ትተን፣ ግብይት ላይ ማተኮር! ካልተግባቡ፣ ልዩነታቸውን በውይይትና በድርድር መፍታት አለባቸው። ሁለቱን ኩንታል ጤፍ ልውሰድብህ፤ ምንም ጤፍ አልሰጥም… ችግር፣ ግጭት ይፈጠራል።
ቢሆንም… ይህንን እንደ ችግር እንደ ግጭት መቆጠር የለበትም። ይሄማ መቼም ጊዜ ይኖራል። ዋናው ነገር፣ ችግርና ግጭትን በሰላም፣ በውይይት፣ በድርድር ማስታረቅና መፍታት ነው።

የዘመናችን “ግብይት”! - እንደዘመኑ የውይይት አይነት፣ እንደዘመኑ የመቻቻል ትርጉም?

አንተኛው፣ ያለክፍያ ምንም ጤፍ አልሰጥም ብለህ፣ ንጥቅያ መቃወምህ፣ ዝርፍያን መታገልህ፣ አቤቱታ ማሰማትህ ተገቢ ነው። የሕዝብ ድምፅ፣ የፍትህ ጥያቄ ነው። ነገር ግን፣… ሁልጊዜ፣ እኔ ያልኩት ይሁን አትበል። ሁለት ኩንታል ጤፍ ስለያዝክ፣ ያለ ክፍያ… አንዱን ኩንታል ብትሰጥስ? አንድ ኩንታል ጤፍ ተረፈልህ ማለትኮ ነው፤ ቀላል ትርፍ አይደለም።
አንተኛውም፣… ያለክፍያ ሁለቱንም ኩንታል ጤፍ ጠራርጌ ልውሰድ አትበል። ማንኛውንም ጥያቄ፣… የሕዝብ ጥያቄ እስከሆነ ድረስ፣ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የማቅረብና ምላሽ የማግኘት መብት አለህ። ያለ ክፍያ በነፃ የመገበያየት ጥያቄ፣ የነፃነት ጥያቄ ነው። ነገር ግን፣  ፈጣን ምላሽ ባለማግኘትህ፣ የማቃጠልና የማውደም አማራጭ አትያዝ። ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ይሁን አትበል፤ የሕዝብ የተጠቃሚነት ጥያቄ በሂደት ምላሽ እንዲያገኝ በሰላማዊ መንገድ ትግልህን ቀጥል። ለጊዜው፣ ያለክፍያ አንድ ኩንታል ብቻ ብትወስድበትና ተጠቃሚ ብትሆንስ?
አንተኛውም አንድ ኩንታል ጤፍ ተረፈልህ። አንተኛውም አንድ ኩንታል ጤፍ አገኘህ!
ደሁሉንም ወገኖች ባሳተፈ መንገድ፣ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ መልካም አስተዳደር ይሄውና!  
ቅራኔን በድርድር አቻችሎ፣ መራራቅን በድርድር አቀራርቦ፣ ልዩነትን በውይይት አስማምቶ፣ አለመግባባትን በድርድር ተገበያይቶ፣ በጋራ ተግባቦት፣ በጋራ መስተጋብር፣ በጋራ ማህበራዊነት፣ ልዩነትን እንደውበት ተቀብሎ በህብር…
ይሄ ነገር የት ነው የሚያበቃው? እንዲህ እያነበነብን እስከ መቼ? ማነብነብ ማነብነብበ…
ምናልባት ለአንድ ጊዜ፣ ለአንድ ቀን፣ ለአንድ አመት? የሚያዋጣም ሊመስል ይችላል።
በማግስቱስ? ለከርሞስ? ለዘለቄታውስ?
በማግስቱማ፣ ደህና ምርት ይዞ ለግብይት የሚመጣ ሰው ይጠፋል። ግብይት፣ ድርድር፣ መወያየት፣ መቻቻል ማለት ምን ማለት እንደሆነ አይቷላ። በተቃራኒው ደግሞ፣ “የተጠቃሚነትና የነፃነት ጥያቄ” ይዣለሁ ብሎ እየፎከረ፣ ባዶ ከረጢት አያውለበለበ፣ ያሻውን ምርት ያለክፍያ ለመውሰድ፣ ያሻውን ሸቀጥ በነፃ ለማፈስ… በሆታ የሚጎርፍ ሰው ይበዛል። ገበያው ይተራመሳል። ይቀወጣል።
የሚጠቅምና ፋይዳ ያለው ነገር፣ ምርትና ክፍያ… እነዚህን ቁምነሮች በማድበስበስ፣ ወዲያ በማሽቀንጠር፣… “ግብይት”፣ “መገበያየት” እያሉ በቁንፅል ማነብነብ፣ አያዋጣም።
በአንድ በኩል የዝርፊያ ባንዴራ አለ፤ ከክፍያ ነፃ የመሆን “መብቴ” ይከበር፤ ንብረትህን ልንጠቅ የሚል።
በሌላ በኩል፣ የንብረት ባለቤትነት ባንዴራ አለ፤ የምርት ባለቤትነቴ ይከበር፤ ንብረቴን አልነጠቅም የሚል።
እነዚህን ተቃራኒዎች፣ እንደ እኩል ማየትና እንደ ገበያተኛ መቁጠር የተጀመረ ጊዜ፣… እናም ለማስታረቅ፣ ለማቻቻል፣ ለማቀራረብ፣ ለማደራደር የተሞከረ ጊዜ፣… ፈጠነም ዘገየም… ማን እንደሚያሸንፍ አትጠራጠሩ።
አምራችና ቀማኛ ተደራድረው ተቻችለው እንዲያድሩ ከተመኘን፣… ያው፣ ቀማኛው ደግሞ ሰውዬ ግማሽ ጎተራ እንዲዘርፍ፤ አምራቹ ሰውዬ አመት ሙሉ ሰርቶ ያፈራውን ንብረት ግማሹን በአንድ ጀንበር እንዲያጣ እናደርጋለን። የሰራ እና ያልሰራ ሰው፣ እኩል ሆኑ። የሃብት ክፍፍል፣ የሃብት እኩልነት… የሚል ባንዴራ ተራገበ። ግማሽ ግማሽ ጎተራ ምርት፣ ሁለት ሰዎች! ግን በማግስቱስ? የአቅማቸውን ያህል እየሰሩ ትንሽ ነገር ያመርቱ የነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎች፣… ስራቸውን ትተው አደባባይ እንዲወጡ ጋበዝናቸው ማለት ነው። ለማምረት መሞከር፣ ከንቱ ልፋት ሆነ እንዲታያቸው እያደረግን ነዋ። ያለ ጥረትና ያለ ክፍያ… “ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄ” በማንሳት፣ ባዶ ከረጢት እየራገቡ፣ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠን ይላሉ። የሚያመርቱ ሰዎች ቁጥራቸው እየተመናመነ፣ ወደ ቅሚያ የሚቀላቀሉ የሰዎች ቁጥር ደግሞ በፍጥነት እጥፍ ድርብ እየበረከተ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ማጣፊያው ያጥረናል። ማስቀየሻ የሌለው አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅረን ማጣጣር ይሆናል መጨረሻው።

Read 3579 times