Tuesday, 02 January 2018 09:41

የአረና ም/ሊቀመንበር፤ በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 • ህወሓት የበላይ ለመሆን አዲስ ሀሳብና አቅም የለውም
       • የህዝቡ ችግር የእርስ በእርስ ግንኙነት ሳይሆን የዲሞክራሲ ነው
       • ከኢትዮጵያ አንድነት ይልቅ ልዩነት ከሚገባው በላይ ተሰብኳል

    የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ ም/ሊቀ መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬን፣ በወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች፣ በብሔር
ተኮር ግጭቶች እንዲሁም በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

    በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ብሔር ተኮር ግጭቶችን አረና እንዴት ይመለከተዋል?
ሲጀመር አሁን በሀገሪቱ ያሉ ቀውሶች የብሄር ችግር ናቸው ብለን አናምንም፡፡ ጉዳዩን እንደ ብሄር ግጭት አንረዳውም፡፡ በኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ፉክክር ውጤት ነው፡፡ የብሄር ግጭት ቢሆን ኖሮ፣ በርካታ ህዝብ ነበር ለጉዳት የሚዳረገው፡፡ አሁን የምናየው የተወሰኑ ዒላማ የሚደረጉ አካላትን የማጥቃት ዝንባሌ ነው፡፡ እርግጥ ነው የብሄር ግጭት ፍንጮች አሉ። መንገዱም ወደዚያ ሊያደርስ የሚችል ነው። እስካሁን ግን በዩኒቨርሲቲዎች የተነሳው ግጭትም ሆነ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ የተከሰተው ግጭት የብሄር አይደለም፡፡ በዩኒቨርሲቲ የታየው ግጭት በተማሪዎች መሃል የገቡ የደህንነት ሰዎች የፈጠሩት ነው የሚል ጥርጣሬ አለን፡፡ በተመሳሳይ በድንበሩም ያለው ከዚሁ ግምት የማያልፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩን በጥሞና ካስተዋልነው፣ ጉዳት ያደረሱ ሰዎች፣ ሲጋለጡና ለህግ ሲቀርቡ አናይም፡፡ ለህግ እናቀርባለን የሚል ወሬ ብቻ እንጂ ተግባራዊ እርምጃ የለም፡፡ ህዝቡ ግን በየትም መንገድ ዛሬም በባህሉ፣ በሥነ ልቦናው አንድ ነው፡፡
ግጭቶቹ ሆን ተብለው የሚፈጠሩ ናቸው ከተባሉ፣ ዓላማቸው ምን  ሊሆን ይችላል?
አንደኛ በዚህ በብሄር ግጭት ውስጥ ተደብቆ፣ በስልጣን መቆየት የሚፈልግ አካል አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንን ግጭት ተጠቅሞ በቀጥታ ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡ ይሄንን በተግባር እያየን ነው፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ድንበር ያለው፣ የህዝብ ለህዝብ ግጭት ሳይሆን የታጣቂዎች ነው፡፡ እነዚህን ታጣቂዎች ማን ነው በህግ የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው? ብዙ ህዝብ እንዲገደልና እንዲፈናቀል የተደረገው በተራ ዜጎች አይደለም፤ በታጣቂዎች ነው፡፡ ሀገሪቱን የሚገዙት የመንግስት አካላት ናቸው፤ የዚህ ሁሉ ባለቤትና ተጠያቂዎች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በተመለከተ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ይሄም ቢሆን መንግስት ችግሩን ለመደበቅ የሚያደርገው ሩጫ ነው፡፡ የህዝቡ ችግር የእርስ በእርስ ግንኙነት ሳይሆን የዲሞክራሲ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ወይም የአማራ አሊያም የትግራይና ሌሎችም ህዝቦች፣ ያለባቸው ችግር ከሌላው ወንድም ህዝቦች ጋር አብሮ የመኖር አይደለም፤ ዋናው የዲሞክራሲና የነፃነት ችግር ነው፡፡ የህዝቡ ችግር የኢኮኖሚና ፍትሃዊ አስተዳደር እንጂ ህዝብ ለህዝብ አልተጣላም፡፡ ህዝብ ለህዝብ ባልተጣላበት ሁኔታ እርቅ ትርጉሙ ምን እንደሆነ እነሱም የሚረዱት አይመስለኝም፡፡ ይሄን ስል ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፤ ግን ህዝቡ ካነሳው መሰረታዊ ጥያቄ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ዋናውን ችግር ለመሸሽና ለመደበቅ የሚደረግ ሩጫ ነው፡፡ እንደኔ ይሄን ታክቲክ መንግስት ቢተወውና ወደ ዋናው የህዝብን ጥያቄ መመለስ ቢገባ የተሻለ ነው፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ፋይዳ የለውም ማለት ነው?
የኛ አቋም፣ ለዜጎች ነፃ እንቅስቃሴ መፈጠር አለበት የሚል ነው፡፡ ማንም ያለ ድንበር መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ነፃ የሆኑ የዲሞክራሲ ተቋማትን በመፍጠር፣ ሃገርን ማስተዳደር ቢቻል ይሄ ሁሉ ግርግር አያስፈልግም ነበር፡፡ ለህዝቡ የሚጠቅመው ነፃ እንቅስቃሴ እንጂ እንደ ጎረቤት ሃገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አይደለም፡፡ የብሔር ግጭትን መጠቀሚያ ማድረጉ ቆሞ፣ የህዝቡ በነፃነት መንቀሳቀስ መቅደም አለበት።
የፌደራሊዝም ሥርዓቱ ብሄር ተኮር በመሆኑ፣ አሁን ለሚታዩ ክፍፍሎችና ግጭቶች መንስኤ ሆኗል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የፓርቲያችሁ አቋም ምንድን ነው?
እውነቱን ለመናገር፣ በህገ-መንግስቱ ሊመሠረት ስለሚገባው ፌደራሊዝም የሚያትተው አንቀፅ ላይ፣ በቋንቋ ብቻ አይደለም የሚለው፡፡ ስነ ልቦና፣ ባህል፣ ኩታ-ገጠምነት፣ የህዝብ ፍቃደኝነት  የሚል አለው። ስለዚህ መልክአምድራዊንም ያጠቃልላል ማለት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የሚያስቀምጠው በሠፊው ነው፡፡ የህዝብ ፍቃደኝነት የሚለው ለምሣሌ፣ ህዝበ ውሳኔ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን እንቀበላለን፤ ነገር ግን በህገ መንግስቱ የተቀመጠው አልተተገበረም የሚል የፀና እምነት አለን፡፡  
ለምሣሌ የወልቃይት ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ጉዳይ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው የህዝብ ፍቃደኝነት መሠረት፣ መፈታት የሚችል ችግር ነው፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ የህወሓት እና የብአዴን ግጭት ውጤት እንጂ የወልቃይት ህዝብ ችግር አልነበረም፡፡ ህወሓት ጉዳዩን ለፖለቲካ ሲጠቀምበት በሚገባ አይተናል። ብአዴንም በተመሳሳይ ጉዳዩን ለፖለቲካ አላማ ሲጠቀምበት አስተውለናል፡፡ ግን ህዝበ ውሳኔም ለማካሄድ አሁንም መቅደም ያለበት የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በሌለበት የሚካሄድ ህዝበ ውሳኔ ዋጋ የለውም፡፡
ባለፉት ዓመታት በፌደራሊዝም ሥርአቱ ላይ የታዩ ህጸጾች ምንድን ናቸው?
በእርግጥ ባለፉት ዓመታት በዚህ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ከኢትዮጵያ አንድነት ይልቅ ልዩነት ከሚገባው በላይ ተሰብኳል፡፡ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት በላይ ከርሯል፡፡ እንደ እኔ አረዳድ፣ ማንነት የሚባለው ነገር በብሄር ብቻ የሚወከል አይደለም፡፡ አንዳንዴ የዘር ነው ይባላል፡፡ ግን እኛ መሃል የተለየ ዘር የለም፡፡ ዘር ማለት በቀለም፣ በቆዳ አይነት የሚመጣን ልዩነት ያማከለ ነው። እኛ ጋ ያለው ልዩነት የቋንቋ ነው እንጂ አንድን ሰው መልኩን አይቶ፣ ምን ቋንቋ እንደሚናገር እንኳ መለየት አይቻልም፡፡ አሁን ያለን የቋንቋ ልዩነት ነው፡፡ ይሄ ልዩነት ከሚገባው በላይ መጉላቱ በጣም ነው የሚያሳዝነው፡፡ የዘር ልዩነት ሳይኖረን፣ በቋንቋ መለያየታችን ያሳዝናል፡፡
“ሀገሪቱን በበላይነት የሚመራው ህወሓት ነው” የሚሉ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ እርስዎ  በዚህ ጉዳይ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አንዳንዴ ነገሮችን የምንረዳበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ ሁልጊዜ የምጠይቀው በዚህች ሀገር የትኛው ነው የመንግስት ቁልፍ የሥልጣን ቦታ የሚለውን ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በላይ ቁልፍ የሥልጣን ቦታ የለም፡፡ አቶ መለስ በነበሩ ሰዓት ህወሓት ይሄን ቦታ በመያዙ፣ በእርግጥም የበላይ ነበር ማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጦሩም፣ ደህንነቱም ሁሉም ነገር የሚታዘዘው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ይሄ የስልጣን ቦታ  በሌላ ከተተካም በኋላ ግን “ህወሓት የበላይ ነው” የሚለው አስተሳሰብ ቀጥሏል፡፡ በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቦታውም ከህወሓት ወጥቶ ወደ ሌላ ሲዘዋወር፣ ቦታው አሁንም የህወሓት ነው የሚለው አመለካከት አልቀነሰም፡፡ እነዚህ ቁልፍ ቦታዎች በሌላ አካል ተይዘውም፣ “የህወሓትና የትግራይ የበላይነት አለ” የሚል አመለካከት  መቀጠሉ አስገራሚ ነው፡፡
 እኔ አሁን ጉዳዩን የምመለከትበት አግባብም ከወትሮው የተለየ ነው፡፡ ለምን ከተባለ፣ ”ትግሬ ምንም ቦታ ላይ መቀመጥ የለበትም” የሚል አስተሳሰብ ነው እየነገሰ ያለው፡፡ እንደ ተቃውሞ ማነሳሻም  እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ይሄ አደገኛ ጉዳይ ነው፡፡ እንደኔ ምልከታ፣ በአሁኑ ወቅት የህወሓት የበላይነት የለም፡፡ ምክንያቱም የህወሓት ሰዎች አሁን  ምንም አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ችሎታ ያላቸው አይደሉም፡፡ ከአቶ መለስ ጋር ለመወዳደር የሚችል ሰው የላቸውም፡፡ ስለዚህ በሌላው የሀገሪቱ ዜጋ ላይ ተፅዕኖ የማድረግ አቅም ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለንም፡፡
አንዱ የሚነሳው ክርክር ህወሓቶች፣ የደህንነት ኃይሉን ተቆጣጥረውታል የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ የደህንነት ኃላፊው ህወሓት ሊሆን ይችላል፤ ግን ከሱ በታች ያሉትን አናውቃቸውም፡፡ የመከላከያ ኢታማዦር ሹም የትግራይ ሰው ነው፤ ግን ከዚያ በታች ያለው ማን እንደሆነ አናውቅም፡፡ አንድ አካል ወይም ሰው የበላይ መሆን የሚችለው፣ የበላይ ሊሆን የሚችል ሃሳብ ይዞ ሲመጣ ነው እንጂ እንዲሁ የበላይ እሆናለሁ ብሎ ስለተነሳ አይደለም። በአሁን ወቅት ደግሞ ህወሓት የበላይ ለመሆን አዲስ ሀሳብና አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ የበላይ ነው የሚለው አያሳምንም፡፡ በአሁኑ ወቅት ጠንካራ ሃሳብ ይዞ ማሳመን የቻለ ድርጅት ከመካከላቸው የለም። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ መናናቅ የተፈጠረውና ሃገሪቱን መምራት ያቃታቸውም ለዚህ ነው፡፡  
ህወሓት አዲስ የአመራር ለውጥ ማድረጉስ ---?
አመራሩ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣት ካልቻለ፣ መለወጥ የየትኛውም መንግስት አሰራር ነው፡፡ ህወሓትም የአመራር ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ መጠየቅ  ያለበት፣ “የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈታ የሚችለው የአመራር ለውጥ ነው ወይንስ የአስተሳሰብ ለውጥ?” የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ህዝብ ነፃነትና ዲሞክራሲ ይፈልጋል ለሚለው ያስቀመጡት ምንም አዲስ አቅጣጫ የለም፡፡ ይሄ ባልተቀመጠበት ሁኔታ  እንዴት ነው ውጤት የሚመጣው? ሰዎቹ በዋናነት ያደረጉት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብን በሚገባ አላስፈፀሙም ያሏቸውን አንስተው፣ ሊያስፈፅሙ ይችላሉ ያሏቸውን ነው የሾሙት፡፡ ስለዚህ የርዕዮተ ዓለም ፍተሻ አላደረጉም፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደግሞ በ1ለ5 ዜጎችን ጨምድዶ ለመያዝ የሚተጋ ርዕዮተ አለም ነው፡፡ ይሄ ባልተለወጠበት ሁኔታ ምን አዲስ ነገር እንዲመጣ ነው የሚጠበቀው?  ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን አንድ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ይሄን ዓይነት አመለካከት ግን  ምንጩ ምን ይመስልዎታል?
አንድ ጉዳይ አስቀድሜ ላንሳ፡፡ በቅርቡ አቶ አባዱላ ገመዳ ሲናገሩ፣ በሃገር ውስጥም በውጪም ያለው የኦሮሞ ህዝብ ከምንግዜውም በላይ አንድ ሆኗል ብለዋል፡፡ ይሄ በጣም ነው የገረመኝ። ሁሉም ኦሮሞ ኦህዴድ ሆነ ማለት ነው? ኦሮሞ ሁሉ በአስተሳሰብ አንድ ሆነ ማለታቸው ነው? ይሄ አስተሳሰብ ደግሞ በአቶ መለስም በጀነራል ሳሞራ የኑስም ተብሏል፡፡ የትግራይ ህዝብ አንድ ሆኗል። የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ነው ተብሏል፡፡ ይሄ ማለት የተለያየ አስተሳሰብ የለም ማለት ነው? እንደ’ኔ ምልከታ፣ ይሄ አስተሳሰብ ነው ሀገሪቷን እየበጠበጠ ያለው፡፡       
እንደ እኔ፣ ህዝብን በቋንቋው ጠርቶ፣ አንድ ነው ማለት የአስተሳሰብ ጭፍለቃን ነው የሚፈጥረው። “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ነው” ሲሉ፣ ህወሓቶች ህዝቡን መደበቂያ እያደረጉት ነው። እነዚህ ባለስልጣኖች ይሄን እያሉ፣ ዘመድ አዝማዳቸውን በሙስና የጠቀሙ እንደሆነ አስቀድመው በፈጠሩት ምስል መሰረት፣ ድሃው የትግራይ ህዝብ ሁሉ እንደተጠቀመ ተደርጎ በሌላው ይታሰባል ማለት ነው፡፡ ህወሓት ጉዳዩን ለመደበቂያነት ሲጠቀምበት በተቃራኒ የተሰለፉት ደግሞ ለማነሳሻነት ይጠቀሙበታል፡፡ ይሄ በእውነት በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን፣ አንድ የሚያደርጉንን ነው ማበረታታት ያለብን እንጂ ልዩነታችንን ጨምረን ጨማምረን እያጎላን ከሄድን አደገኛ ነው፡፡
“አረና” በአገሪቱ ለሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስ  መፍትሄው ምንድን ነው ይላል?
በቅንነት መነጋገር ነው መፍትሄው፡፡ አሁን እንደሚደረገው፣ ቢሮ እንኳ የሌላቸው ግለሰቦችን በፓርቲ ስም እየሰበሰቡ ማነጋገር ሳይሆን የህዝብ መሰረት ያላቸውን ፓርቲዎች ማነጋገር ይገባል። በውጪም በሀገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን በሰፊው የሚነጋገሩበት፣ ማንንም ያላገለለ መድረክ መዘጋጀት አለበት፡፡ በእልህ ሀገሪቱን የሌላ ኃይል መጠቀሚያ ላለማድረግ ከወዲሁ መጠንቀቅ አለብን፡፡

Read 918 times