Tuesday, 02 January 2018 09:40

ኢዴፓ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሳቢያ ሊፈርስ ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  “አዲስ ፓርቲ አቋቁመን ትግላችንን እንቀጥላለን” - አቶ ልደቱ አያሌው

     የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ በእነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እንዲመራ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መወሰኑን ተከትሎ፣ በፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ተመርጠናል ያሉት አዲሱ የእነ አቶ አዳነ ታደሰ የአመራር ቡድን፣ከኢዴፓ  ወጥተው፣ አዲስ ፓርቲ እንደሚያቋቁሙ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ፣በብሄራዊ ም/ቤት አባላት መመረጣቸውን ሲገልጹ ለቆዩት ለእነ አቶ አዳነ ታደሰ ቡድን በሰጠው ምላሽ፤ ተመርጠንበታል ያሉትን የህግ አካሄድ መፈተሹንና ያቀረቡት ሰነዶች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት በዲሲፕሊን እርምጃ ፓርቲው ከአመራርነት ያነሳቸው የቀድሞዎቹ የእነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ቡድን በአመራርነታቸው እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡
ቦርዱ ለእነ አቶ አዳነ ታደሰ በፃፈው ደብዳቤ፤ ተመርጠንበታል ያሉትን የህግ አካሄድ ከተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000 አንፃር መመርመሩን ይገልጻል፡፡ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ፣ አንቀፅ 22.8፤”ፕሬዚዳንቱ በብሄራዊ ምክር ቤቱና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ መሰረት የሚወጡ ደብዳቤዎችንና ሰነዶችን እንዲሁም ሌሎች አስተዳደር ነክ ደብዳቤዎችን ይፈርማል” በሚል የሚደነግግ መሆኑን የሚጠቅሰው ደብዳቤው፤የቀረቡት ሰነዶች ግን ቦርዱ በሚያውቃቸው የፓርቲው ፕሬዚዳንት የተፈረሙ አለመሆናቸውን ጠቁሞ፣ ሰነዶቹ  አግባብነት እንደሌላቸው  አስታውቋል፡፡
የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 20.1.1፤ “የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሲወስን ወይም ከምክር ቤቱ አባሎች 1/3ኛዎቹ ሲጠይቁ፣ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል” እንደሚል፣ የመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 20.2.2 ደግሞ፤ “የብሄራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሚወስነው ቦታና ጊዜ ይካሄዳል” በማለት መደንገጉን በመጥቀስም፣እነዚህ ሂደቶች አለመሟላታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል - ቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፡፡ በዚህም ምክንያት እነ አቶ አዳነ ታደሰ ያቀረቡት ሰነድ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡
በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 9.4.17 መሰረት፤ ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጠራ ብሄራዊ ም/ቤቱ በከፍተኛ ድምፅ እንደመረጣቸውና እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደን ከስልጣን እንደሻረ የገለፁት አቶ አዳነ ታደሰ፤ ምርጫ ቦርድ ደንባችንን በአግባቡ ሳያጤን  ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡  
“የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ፓርቲያችንን የሚያፈርስ ነው” ያሉት አቶ አዳነ፤ “አሁንም ቦርዱ ጉዳዩን እንዲያጤነው እንጠይቃለን፤ ተገቢ ምላሽ ካልተሰጠን ግን ፓርቲው ይበተናል” ብለዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳዩን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ “ስርአቱ በሃገሪቱ ከተፈጠሩ ቀውሶች የማይማር መሆኑን የመድብለ ፓርቲ ስርአት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በሚጎዳ መልኩ ፓርቲያችንን በማፍረስ አሳይቶናል” ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ችግር በሃቅ ለመፍታት ፈፅሞ እንደማይችል በምርጫ ቦርዱ ውሳኔ አረጋግጠናል ያሉት አቶ ልደቱ፤ በሚቀጥለው ምርጫ ከዚህ ቀደም ሲያደርገው በነበረበት መንገድ ለመቀጠል እንደፈለገ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
“ኢዴፓን የፈጠርነው እኛ ነን፤ አስተሳሰቡን የፈጠርነው እኛ ነን፤ ስሙን ስለተነጠቅን አስተሳሰባችንን አንነጠቅም፤ እንደገና አዲስ ፓርቲ አቋቁመን ትግላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል - አቶ ልደቱ፡፡

Read 4656 times