Tuesday, 02 January 2018 09:35

ከሳኡዲ በኃይል የተባረሩት ኢትዮጵያውያን፣ ኢ-ሰብአዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ተናገሩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላቸውም በሚል በኃይል ከሳኡዲ አረቢያ የተባረሩ ኢትዮጵያውያን፤ በሳውዲ ፖሊስ ኢ-ሰብአዊ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው አስታወቁ፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው፣ ከሳኡዲ በኃይል የተባረሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሀገሪቱ መንግስት ያስቀመጠው የምህረት ጊዜ ማብቃቱን ተከትሎ ከያሉበት በፖሊስ እየታደኑ፣ እጅግ ወደ ቆሸሹና ለሰው ልጅ ወደማይመቹ እስር ቤቶች መጋዛቸውን፣ መደብደባቸውንና ንብረታቸው በሙሉ መዘረፉን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከስደት ተመላሾች የሳኡዲ ፖሊስ አባላት ድብደባና ዘረፋ ከመፈፀም ባለፈ ከእስር ቤት ሊያመልጡ የሞከሩ ሰዎች ላይም ተኩስ ሲከፍቱ መመልከታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች የምህረት ጊዜውን ተጠቅመው እንዲወጡ ሲያሳስብ የቆየ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በተደረገው ዘመቻም ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችን በአዋጁ ወቅት ማስወጣት መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የምህረት አዋጁ መጠናቀቁን ተከትሎ ሳኡዲ በወሰደችው ህገ ወጥ ያለቻቸውን ዜጎች የማሰርና የማባረር እርምጃ ከ14 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በኃይል ከሀገሪቱ መባረራቸውን የዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡
የሳኡዲ ባለስልጣናት በበኩላቸው፤ ከ11 ወራት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በኋላ እየተወሰደ ባለው እርምጃ ሩብ ሚሊዮን አካባቢ ህገ ወጦችን ማሰር መቻሉንና ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ በኃይል ወደየሀገራቸው መላካቸውን አስታውቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ፎክስ ኒውስ በሰራው ሰፊ ዘገባ፣ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳኡዲ ከገቡ የውጭ ሃገር ዜጎች የመናውያን 72 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያውያን 26 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ጠቁሟል፡፡
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በጉዳዩ ላይ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ፣ መንግስት ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገር ቤት መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሳኡዲ መንግስት ጋር በመነጋገር እየሰራ መሆኑን መጠቆማቸው አይዘነጋም፡፡

Read 2700 times