Saturday, 23 December 2017 10:41

‹‹…ኤችአይቪ ኤይድስ - 2030/…››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ‹‹…እኔ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ የተገኘው የዛሬ ሀያ ሶስት አመት ነው፡፡ ዛሬ   እድሜዬ 45 አመት ደርሶአል፡፡ በጊዜው ሳይውል ሳያድር ተመርምሬ ችግሩን በማወቄ እነሆ እስከዛሬ ድረስ ካለምንም ችግር እራሴን በአግባቡ እየመራሁ እገኛለሁ፡፡ ጤንነቴም ተጉዋድሎ አያውቅም፡፡ አበባ እንደመሰልኩ እኖራለሁ፡፡ ሕመም ገጠመም አልገጠመም በተወሰነ ጊዜ ምርመራ እያደረጉ እራስን መጠበቅ ጠቃሚ ነው፡፡…››
(የኤችአይቪ ቫይረስ በደምዋ ውስጥ የሚገኝ ሴት እማኝነት)
ኤይድስ HIV (human immunodeficiency virus) ከሚባል የቫይረስ አይነት የሚከሰት ገዳይ የሆነ በሽታ ነው፡፡ ኤይድስ በአለም አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያ መኖሩ የታወቀው እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1981/ዓም ነው፡፡ ለዚህ የማይድን በሽታ ኤይድስ የሚል ስያሜ የተሰጠውም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁላይ 27/1982/ዓ/ም ነው፡፡
በየአመቱ በውጭው አቆጣጠር ዲሴምበር 1/ አለም አቀፍ የኤችአይቪ ቀን በሚል እንደ ውጭው አቆጣጠር ከ1988/ዓ/ም ጀምሮ ሲከበር ቆይቶአል፡፡ ዲሴምበር 1/ አሁንም ኤችአይቪን በተመለከተ  የተለያዩ ነጥቦች በአለም ዙሪያ የሚንጸባረቁበት ቀን ሆኖአል፡፡ ይህ አለምአቀፍ ቀን ኤችአይቪን በሚመለከት ትምህርቶችን በመስጠት ግንዛቤ በማስጨበጥ እና ስርጭቱን ለመግታት የተለያዩ እንቅስቃሲዎች የሚደረግበት ነው፡፡  
በ2016/በአለም አቀፍ ደረጃ በደማቸው የኤችአይቪ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር በአማካይ 36.7/ሚሊዮን ሲሆን 1.8/ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ናቸው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ወደ 2/ሚሊዮን የሚደርሱት ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለሕልፈት የሚዳረጉ ሲሆን ከነዚህም 10 በመቶ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው፡፡
ኤይድስ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ እድሜያቸው ከ10-29/ አመት የሆናቸውን ሰዎች በመግደል ዋነኛው ምክንያት ሲሆን በአለምአቀፍ ደረጃ ደግሞ በወጣቶች ገዳይነቱ በ2ኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በቀጣይነት እንዲተገበር ለታቀደው ልማት አንዱና ዋነኛው እቅድ በማናቸውም እድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ጤናማ ሕይወትን መምራት እና ደህንነትን ማረጋገጥ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህም ውስጥ ኤችአይቪ ኤይድስ እስከ 2030/ ስርጭቱን እስከወዲያኛው እንዲያከትም አለም አቀፍ ስምምነት ተደርጎአል፡፡
ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ምንም ጥረት ካልተደረገ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ15-45/ በመቶ በሚደርስ ደረጃ ከእናት ወደ ልጅ በሚተላለፍባቸው መንገዶች ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል። በ2016 በተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደተገኘው መረጃ ከሆነ መተላለፉን ለመከላከል በአለም አቀፍ ደረጃ በተወሰዱ እርምጃዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚኖር 76 ከመቶ የሚሆኑ እርጉዝ እናቶች ፀረኤችይቪ መድሀኒትን በትክክል እንዲጠቀሙ ተደርጎአል፡፡ በዚህም ጥረት ከኤችአይቪ ነጻ የሆነ ትውልድ እንዲመጣ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ባጠቃላይም በአለም አቀፉ ኤችአይቪ ቀንም ሆነ በሌሎች ጊዜያቶች በአለም አቀፍ ደረጃ አገራት እንዲሁም የሚመለከታቸው ድርጅቶች እና ህብረተሰብ ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡትና ጥንቃቄ ሊያደርጉበት የሚገባ ሲሆን የህክምናው አገልግሎትም ከጊዜ ወደጊዜ እንዲሻሻል የተቻለው ጥረት እንዲደረግ አለምአቀፍ ስምምነት አለ፡፡
ምንጭ ፡-WHO…2017/
ኤችአይቪ በአሁኑ ወቅት አነጋጋሪ እየሆነ ነው። በመሆኑም አለም አቀፉን የኤችአይቪ ኤይድስ ቀን ምክንያት በማድረግ የጋንዲ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ለሆስፒታሉ ሰራተኞችና በወቅቱ ለነበሩ ታካሚዎች ስለኤችአይቪ ገለጻ የማድረጊያ ፕሮግራም አከናውኖአል። ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት የሆስፒታሉን ስራአስኪያጅ ሲ/ር ሕይወት ገ/ሚካኤልን አነጋግረን ለንባብ ብለናል፡፡
ሲ/ር ሕይወት እንደሚሉት ኤችአይቪን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት የመዘናጋት ነገር አለ፡፡ ለምሳሌም በአዲስ አበባ አሁን ያለው ስርጭት መጠን ቀደም ሲል ከነበረው ጨምሮ ይታያል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚቆጠረው ውስጥ አንዳንድ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች የፀረኤችአይቪ ኤይድስ መድሀኒት በሚወስዱበት ጊዜ የጤናቸው ሁኔታ ስለሚሻሻል ጨርሰው የተፈወሱ እየመሰላቸው መድሀኒቱን ስለሚያቋርጡ ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የባህርይ ለውጥ ማምጣት የሚባለውን ወደጎን በመተው እና 5ቱን መ…ዎች… ማለትም …መጠንቀቅ… መታቀብ… መመርመር…መድሀኒት መጠቀም… ኮንዶም መጠቀም የሚሉትን በትክክል ተግባር ላይ አለማዋል ይታይባቸዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ሲነገራቸው ወደ ሕክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ በተለያዩ ልማዳዊና የእምነት ቦታዎች በመሄድ በቃ ከሕመሙ ፈውስ አግኝተናል ብለው ስለሚያስቡ ቫይረሱ እየጎዳቸው ይገኛል፡፡ ከጤና ባለሙያውም ይሁን ከመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም ከተለያዩ ከሚመለከታቸው አካላትም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የመስጠትና ሰዎች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያደርግ ስራ ከመስራት ቆጠብ የተባለበት ሁኔታ ስለአለ አጠቃላይ ሁኔታውን መዘናጋት ልንለው እንችላለን ብለዋል፡፡
ሲ/ር ሕይወት አስከትለውም የጋንዲ ሆስፒታል የእናቶችና የጨቅላ ህጻናቶች መታከሚያ እንደመሆኑ አንዲትም እናት የእርግዝና ክትትል በምታደርግበት ጊዜ የኤችአይቪ ምርመራ የማታደርግ የለችም፡፡ ይህም ሁለት ጥቅም ያለው ነው፡፡
ክትትል ለማድረግ ከሆስፒታል የመጣችው እናት ዛሬ ከቫይረሱ ነጻ ብትሆን እንኩዋን ነገ በቫይረሱ አትያዝም ማለት ስላልሆነ በቀጣይ ሕይወትዋ እንዴት እንደምትኖር አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚሰጥበት ነው፡፡  
የእርግዝና ክትትል የምታደርገው እናት ቫይረሱ በደምዋ ውስጥ ቢገኝባት ባለቤቷን ጭምር በመጋበዝ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅ እንዴት መውለድ እንደሚቻል እና ባልና ሚስቱም በቀጣይ ምን አይነት የህክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው የምክር አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡
ስለዚህም የደም ምርመራ ማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግና መድሀኒት ለማስጀመር በጣም ወሳኝ ስለሆነ ለሁሉም እርጉዝ ሴቶች የምክር አገልግሎትና የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘባቸው እናቶች የተወለዱ ሕጻናት በሙሉ ቫይረሱ በደማቸው አልተገኘም፡፡ ይህ ወደፊት ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ትውልድን በማግኘቱ ረገድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ አይካድም፡፡
PEPFAR ETHIOPIA/ በ2017 እንዳወጣው መረጃ በኢትዮጵያ 15 ሺህ በደማቸው ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስ የሚገኝባቸው እርጉዝ ሴቶች ፀረኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ ናቸው፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በአለም አቀፍ ደረጃ ኤችአይቪን ስለመከላከል ያወጣው ቁልፍ መልእክት፡-
ከኤችአይቪ ኤይድስ ጋር በተያያዘ የማንም ሰው ጉዳይ ቸል ሊባል አይገባውም፡፡
ኤች አይቪ የሳንባ በሽታ እና ሄፒታይተስ ለተባሉት ሕመሞች ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የተቀናጀ ነው፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝባቸው ሰዎች የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ ጥራት ያለው መሆን አለበት፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ሰዎች በሚችሉት መንገድ ደህንነታቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡
ኤችአይቪን በሚመለከት ያለው ምላሽ በጎ እና ጠንካራ የጤና አጠባበቅ ዘዴ እንዲኖር ማድረግ ያስችላል፡፡
ሲ/ር ሕይወት በስተመጨረሻውም እንደተነገሩት ህብረተሰቡን ከኤችይቪ ኤድስ ጋር በተያያዘ ከሚደርስ ጉዳት ለመጠበቅ የጤና ተቋማት እንዲሁም መገናኛ ብዙሀን እና ተመሳሳይ መድረኮች የምክር አገልግሎትና ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም የህክምና ተቋማት ወይንም የሚመለከታቸው አካላት ለታዳጊዎች እና ለወጣቶች በነጻነት የሚጠቀሙበት የምክር አገልግሎ መስጫ ክሊኒኮች ቢያመቻቹ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የጋንዲ ሆስፒታል  በዚህ አመት አንዱ እቅዱ Adolescence clinic በመክፈት ለታዳጊውና ለወጣቱ በማንኛውም ሰአትና ቀን የምክር አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ብለዋል፡፡

Read 2734 times