Saturday, 23 December 2017 10:35

የሆድ ነገር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(10 votes)

 ወለጫ ወደ ገበያ መሄጃው ጎዳና ዳር ጠረጴዛ ላይ ቅንጥብጣቢ ስጋ ደርድሮ፣ ቢላውን እያፏጨ፣ በዜማ እያዋዛ ይሸጣል፡፡ አንዳንድ የባላገር ሴቶች ጎራ እያሉ ይሸምታሉ፡፡ ወዲያ ጎን ደግሞ ዳስ ነገር ጥሎ፣ ስጋ የሚጠብስ አጋሩ፤ በመጥበሻ ስጋውን ያንሻስችሰዋል፡፡
ሌላው ሰው ጥንድ ጥንድ ሆኖ፣ አሊያም ለየብቻ፣ እህትና ወንድም፣ ባልና ሚስት ሆነው ወደ ላይ ወደ ታች ይላሉ፡፡
የገና ሰሞን ትንሿ ከተማ በእጅጉ ትሞቃለች። የቡና ጊዜው ሳንቲም ገና ከእጃቸው ያልሸሸ ገበሬዎች፤ ጠጅ ቤቱን፣ ጠላ ቤቱን፣ ሥጋ ቤቱን ያሟሙቁታል፡፡  ለጠጅ ነጋዴው፣ ለልብስ ሰፊው፣ ለባለጋሪው - ለሁሉም ህይወት ሳቂታ ናት፡፡ ክረምት መጥቶ ግንባርዋን ቋጥራ፣ በዝናብና በድህነት እስክትደበድበው ሁሉም ንቁ ነው፡፡
እኔም በኪሴ ትንሽ ገንዘብ ስለነበረኝ፣ ሥጋ ልበላ አሰብኩና ወለጫ ጋ የምቆም መስዬ- ዘው አልኩ፡፡ የሚጠበሰው ስጋ ይንቸሰቸሳል፡፡ “የስንት … የስንት ነው ያለው?” ስል ጠየቅሁት፡፡ ጉጉት መላ ሰውነቴን ይዞታል። ባንድ በኩል ሥጋ መብላቱ ቢያምረኝም በሌላ በኩል ደግሞ ቤተሰቦቼ ካዩኝ የሚመጣብኝን ፍዳ ፈርቻለሁ። በቀጥታ እናቴ ወይም አባቴ ባያዩኝ እንኳ ከጎረቤት ሰዎች አንዳቸው ካዩኝ አለቀልኝ፡፡ እርሱ ብቻ አይደለም። ከሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች አንዳቸው ካዩኝ አሳሬን ያበሉኛል፡፡ በተለይ ያ እርጉም ዳኛቸው፡፡
በልቤ እግዜር እንዲያድነኝ እየለመንኩ፣ በትን    ሽዋ የንኬል ሳህን የቀረበልኝን ጥብስ መጠበቅ ጀመርኩ፡፡ ሥጋ ጠባሹ ጥቁር ፊቱ በዘይት የተነከረ መስሎ፣ ንፍጡን በጃኬቱ ጫፍ እየጠረገ፣ በረጅሙ ቢላዋ ያነኩረዋል፡፡
“ፍላስ” ቢላዋውን ይዞ ወጣ፡፡ ድንገት ክፉ ሀሳብ መጣብኝና መለስኩት፡፡ እንደገና አመነታሁ፡፡ አንድ ሙዳ ስጋ ለውሻችን ለችሎ ማደር ልመነትፍለት ተመኘሁ። ግን ልምዱ ስለሌለኝ ነው መሰል ተርበተበትኩ፡፡ በመጨረሻ ግን አልተውኩትም፣ አንስቼ ኪሴ ውስጥ ከተትኩት፡፡ ፋላስ ተመልሶ መጣና “አንተ” አለኝ፡፡
“አቤት”
ዝም ብሎ አየኝ፡፡ ሰውነቴ ተንዘፈዘፈ፡፡ “ቅድም አይቼሃለሁ” ሲለኝ፣ ከኪሴ ስጋውን ለማውጣት እጄን ሰደድኩት፡፡ እሱ ግን ስጋውን ማንኮር ቀጠለ።
“የጋሽ ዓለሙ ልጅ አይደለህ!?”
“አዎ”
በቃ ሊናገርብኝ ነው!
“የኬላ አድባር ታሳድግህ! ዕደግ!”
ግራ ተጋባሁ፡፡
“በቀደም’ለት ያደረከውን አባትህ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ ብሩክ ልጅ ነህ!”
እንባዬ ተናነቀኝ፡፡ ህሊናዬ ከሰሰኝ፡፡
“አንድ ደሀ ደጃችሁ ላይ ወድቆ ብርድ ሲደበድበው፣ ጃኬትህን አውልቀህ ሰጥተሃል አሉ። … ወደድኩህ!”
ደስታ ቢሰማኝም ለውሻችን ብዬ የወሰድኩት ሙዳ ስጋ ግን ፍም ሆኖ አቃጠለኝ፡፡
የወለጫ ድምፅ ይሰማኛል፡፡
“ጮማ ሥጋ! .. ዕድለኛ አያምልጠው” በአማርኛ ሲለው፣ በሲዳሞኛ ያስተዋውቃል፤ ያሻሽጣል። ፊላስ ስጋውን ይጠብሳል፡፡ እኔ የተጠበሰውን ስጋ፣ ዓይኖቼን ጎልጉዬ እጠብቃለሁ፡፡ በጨረፍታ በመንገድ የሚያልፉት ጓደኞቼ ይታዩኛል፡፡ ሰለሞን… ታፈሰ… ቡርቃ …
ሁሉም የክፍላችን ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ቢያዩኝም ግድ የለኝም- የገጠር ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ገብተው ሊበሉ ይችላሉ፡፡ ብቻ የሰፈሬ ልጆችና የክፍሌ ልጆች ሆነው የከተማ ልጆች አያግኙኝ፡፡
ጥብሱ  እንደቀረበልኝ ፉላስ ድንገት በሌላ ሰው ተተክቶ ሄደ፡፡ ወለጫ ግን ቅንጥብጣቢ ሥጋውን ይሸጣል፡፡ አሁን የመጣውን ሥጋ ጠባሽ አላውቀውም። እንደ ፉላስ ጥቁር አይደለም፤ ቀላ ይላል፡፡
“እንዴት ነው ምግባችን?!” አለኝ፡፡
“ጥሩ ነው!”
“ይጣፍጣል አይደል?... ሌላም ጊዜ ደንበኛ ሁን!”
ችላ ብዬው መጉረሴን ቀጠልኩኝ፡፡ ቅድም የተፀፀትኩበትና ለውሻችን ብዬ በኪሴ የያዝኩት ሙዳ ሥጋ አሁን ሳስበው ደስ አለኝ፡፡ ቤት እንደገባሁ… ጥግ ይዤ፣ አንድ ሁለት ቦታ ጎምጄ ስሰጠው፣ እንዴት እንደሚፈነድቅና የሲሲጥታ ዜማውን እንደሚለቀው አሰብኩ፡፡ ጭራውን እየወዘወዘ… መሰንቆውን ይመታልኛል፡፡ ጊታሩን ያርገበግብልኛል፡፡
ለማንኛውም በልቼ ካበቃሁ በኋላም አወጣጤ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ አባቴ እንዲያገኘኝ አልፈልግም፡፡ ምናልባትም የትምህርት ቤት መምህራን እዚህ ቢያዩኝ ሀፍረት የሚጫነኝ ይመስለኛል።
“እጅ መታጠቢያ እዚያች ጋ አለችልህ!” ሲለኝ፣ ወደ ውጭ ወጥቼ መታጠቡን አልፈለኩም፡፡ እጄን በወረቀት ጠራርጌ ሌላ ቦታ ብታጠብ ይመረጣል። መታጠቢያው ወጭ ወራጁ የሚመለከተው ቦታ ላይ የተንጠለጠለ ቢጫ ጀሪካን ነው፡፡
“ታጠብ… ምች ይመታሃል!”
“ግድ የለም - እታጠበዋለሁ” ብዬ ሂሳብ ለመክፈል እጄን ወደ ኪሴ ሰደድኩ፡፡ ተያየን፡፡
ከአንዱ ኪስ ወደ ሌላኛው ኪሴ እጄን ቀያየርኩ። ከሰውነቴ ላብ ሲዘንብ ይሰማኛል፡፡ ጃኬት ኪስ ሸሚዝ ኪስ፣ ሱሪ ኪስ…፣ ገንዘብ የለም፡፡ ግራና ቀኝ አይቼ፣ መሮጥ አስመኘኝ፡፡ ግን ሥጋ ጠባሹ አፍጥጦብኛል፡፡
“በል አትቀልድ! የዚህ ዓይነት ጮሌነት እኛ ጋ አይሰራም!፡፡”
“ጮሌነት አይደለም፣ ጃኬቴ ውስጥ ጥዬ መጥቼ ነው፡፡” ብዬ ልለምነው ሞከርኩ፡፡ ዓይኖቹን የበለጠ አፈጠጠብኝ፡፡
“እያንዳንዷን ኪስህን ፈትሽና እኔ በተራዬ እፈትሸሃለሁ” ሲለኝ የባሰ ፍርሃት ወረረኝ። ለውሻችን የያዝኩትን ሥጋ ሊያገኝብኝ ነው፡፡ አሁን እንዳያዩኝ የምፈራቸውን የሰፈሬንና የክፍሌን ልጆች ረሳኋቸው። አይኔ መንገድ መንገዱን ሲያይ፣ ድንገት ያንን እርጉም ጓደኛዬን አየሁት፡፡ ልጠራው አልፈለግሁም፡፡ እርሱ አለፍ እንዳለ ሊዲያ ብቅ አለች፡፡ አላስቻለኝም ጠራኋት። ቀይ ፊቷ ሚጥሚጣ መስሏል፡፡
“ገንዘብ ጠፋብኝ!” አልኳት፡፡
“ስንት ብር?”
“ሃያ ብር”
“ለትምህርት ቤት የተሰጠኝ ነው፤ ትመልስልኛለህ”
“እሺ” ብዬ ልቀበላት ስል ድንገት እናቷ “አንቺ ሊዲያ!” ብለው እንደ ብራቅ ጮሁ፡፡
“ምናባሽ ታደርጊያለሽ?” ደንግጣ ጥላኝ ሮጠች፡፡
ፈርዶብኛል- እንባዬ መጣ፡፡ ሥጋ ጠባሹ ኪሶቼን መፈተሽ ያዘ፡፡
“አንተ ሌባ!” ሲለኝ
አንድ ልጅ የተጠቀለለ ብር እጄ ላይ አደረገልኝ “ሊዲያ ናት የላከችልህ!” አለኝ፡፡
ነፍሴ ተመለሰች፡፡ ብሩን ወርውሬለት ስሮጥ ጥንቸልም አይቀድመኝ!

Read 3783 times