Saturday, 23 December 2017 10:31

የፈለቀ አበበ የማበብ ምስጢር!

Written by  (ሶ. አ)
Rate this item
(2 votes)

“የማያነብ ሰው በአግባቡ መኖር የሚችል አይመስለኝም”
           
   ከያኒ ፈለቀ አበበ “የከተማው ዘላን” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የመለሳቸውን የአጫጭር ልብ ወለዶች ስብስብ በቅርቡ ለንባብ አብቅቷል፡፡ በመፅሐፉ የተካተቱት አስራ ስድስት አጫጭር ልብ ወለዶች ሲሆኑ የኤድጋር አለን ፖ አንድ ግጥምና የራሱ የፈለቀ አንድ ተጨማሪ ግጥም፣ በመፅሐፉ መጨረሻ ገፆች እንደ ምርቃት ቀርበውልናል፡፡
ፈለቀ የተረጎማቸው የዓለም ታላላቅ ደራሲያን፡- ቺኑዋ አቼቤ፣ ማርክ ትዌይን፣ ካህሊል ጂብራን፣ ጆን ኦሀራ፣ ሉይዝ ቫሌንዙዬላ፣ ስቴፈን ሊኮክ፣ አንቷን ቼኾቭ፣ ሊዮ ቶልስቶይ፣ ኤች ኤች ሙንይሳኪ፣ ራሲፑራም ናራያን፣ ኤስፒ ኤፍ፣ ኦ.ሄንሪ እና ኤድጋር አለን ፖ ናቸው፡፡
እነዚህ ደራሲያን በአንድ መድበል መምጣታቸው፣ እያንዳንዱ ደራሲ የራሱ የሆነ ብቃትና ዘዬ (Style) ስላለው፣ በተቀራራቢና አንድ ጊዜ ውስጥ የተለያየ ጣዕም እንድናጣጥም ይረዳናል፡፡ የጥበብ ኮክቴል ወይም “ማህበራዊ” በሉት! ደራሲያኑ በአንድ መፅሐፍ መካተታቸው፣ ትልቅ ፋይዳ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ፀሀፍቱን የማያውቁ አንባቢያን እንዲያውቋቸው ዕድል የሚፈጥርላቸው ሲሆን ለጥልቅ አንባቢያን ደግሞ ተመሳስሎና ተቃርኖዎቻቸውን፣ የአተራረክ ዘዴዎቻቸውንና የጭብጥ አመራረጣቸውን እንዲያውቁ ያግዛቸዋል፡፡ ጀማሪ ፀሐፍትንም በመነሸጥ ፅሑፍ ወደ ማምረት እንዲገቡ ያነሳሳቸዋል።
አርቲስቱ ከዚህ በፊትም ሁለት መፅሐፍትን የተረጎመልን ሲሆን ከአስራ ሦስት ዓመት በፊት “ብርሃንና ጥላ” የተሰኘ የግጥም መድበል እንዳበረከተልን ይታወሳል፡፡
የማያነብ በበረከተበት፤ መልክን ብቻ ይዞ ወደ መድረክ ወይም ወደ ስክሪን መውጣት በበዛበት ዘመን፣ ተዋናይ ፈለቀ እንዴት ይህን ሁሉ አበረከተልን ወይም ሊያበረክትልን ቻለ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ ተዋናዩ እንዴት ጥበብን እንዲህ አብዝቶ አፈለቀ?! መልሱ አጭርና ግልፅ ነው፤ ከያኒው ያነባል፡፡ ያነባል ስል የሬዲዮ ላይ ትርክት ነው? ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ አርቲስቶች፤ በሬዲዮ ማራኪ ድምፃቸውን ተገን አድርገው፣ ልብ- ወለዶችን ይተርኩልን ይሆናል እንጂ በብዛትና በጥልቀት የሚያነቡ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው፤ ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፤ በዚህ ማራኪና አንበርካኪ ድምፁ፤ “ዲቪ ሎተሪ” የተሰኘውን መፅሐፍ ከዓመታት በፊት ተርኮልናል፡፡ አንዳንድ የሬዲዮ ድራማዎችንና ጭውውቶችንም ተጫውቷል፡፡ ስለዚህ ፈለቀ ቁመናውንና የመድረክ ሰብዕናው ብቻ ሳይሆን ድምፁንም በአግባቡ ተጠቅሟል ማለት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ገና ብዙ እንደሚሰራ ተስፋ ማድረግ የበለጠ የተሻለ ነው፡፡ የወጣትነት የዕድሜ ክልልን ገና አላለፈምና፡፡
ፈለቀ ሲተውን አስማተኛ ነው፡፡ ብቃቱ አፍዝ አደንግዝ ነው፤ አፍ ያስከፍተናል፤ አዕምሯአችን በድማሜ ወደ ከፍታ ይመጥቃል፤ ልባችን በአድናቆት እንደ ከበሮ ይደልቃል፡፡ የፈለቀ ብቃት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ የሙያ ባልደረቦቹ እንደሚመሰክሩት፤ ተውኔት ወይም የፊልም ስክሪፕት ሲሰጠው፣ ሊተውን የሚመጣው የቤት ስራውን ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ መሆኑ ብዙዎች እንዲያደንቁት ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ ሌላው የሚጠቀስለት መልካም ነገሩ፣ ባለሙያዎችን (professionals) አጥብቆ የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ፊልም ሲሰራ ለ3 ወር ተዋውሎ ከሆነ፣ ከዛች ቀን ዝንፍ እንዲል አይፈልግም፡፡ አይፈቅድምም፡፡ ምክንያቱም ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ይፈልጋል፡፡
በእርግጥ ደካማ ጎኑን የሚጠቅሱ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ ሰው ነውና አንድ ደካማ ጎን እንደማያጣ እሙን ነው፡፡ ለኔ ግን ጠንካራ ጎኑና ብርታቱ ነው፣ ጎልቶ የሚታየኝ፡፡ ዘርፈ ብዙ ባለሞያ ከመሆኑም በተጨማሪ ሰናይ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ በርታ ተበራታ ልንለው ይገባል፡፡ ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆንኩ ባላውቅም፣ ለእኔ የሚታየኝ እውነት ይሄ ነው፡፡
ለማንኛውም የከያኒ ፈለቀ አበበ የማበብ ምስጢር፣ ጥልቅ አንባቢ መሆኑ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ባለሞያነቱና ከስኬቶቹ ጀርባ ያለው ጠንካራ ጎን ይሄ ነው፡፡ የሚያነብ ሰው ይፍጠንም ይዘግይ፤ አንድ ቀን የመፃፍ ተስፋ ይኖረዋል፡፡ የማያነብ ሰው ግን እንኳን ሊፅፍ በአግባቡ መኖርም (ይቅርታ ይደረግልኝና) የሚችል አይመስለኝም፡፡ ፈሌ በእርግጥም ያነባል። ሸጋ ሸጋ ነገሮችንም ይፅፋል፡፡ ንባቡ ደግሞ በሀገር ውስጥ ስራዎች ብቻ የተቀነበበ አይደለም፤ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ መተርጎም የቻለውም ንባቡ በዛን ያህል ርቀት እንዲጓዝ ስለፈቀደለት ነው፡፡
ፈለቀ በዚህ የትርጉም መፅሐፉ አንዳንድ ታሪኮችን ኢትዮጵያዊ ቀለም ለመቀባት ሞክሯል። አንዳንድ የአራዳ ቋንቋ ሊባሉ የሚችሉ ቃላትን ተጠቅሟል፡፡ ይሄ ደግሞ ገፀ-ባህሪያቱ ቅርባችን (የምናውቃቸው) እንደሆኑ ያህል እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ ታሪኮቹ እኛን እኛን እንዲሸቱ መትጋቱ “እሰየው!” የሚያሰኝ ነው፡፡ አንድ የደነቀኝን ነገር ላካፍላችሁ፡- እኔ የካህሊል ጂብራን የልብ አድናቂ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ጂብራን እይታው ጥልቅ የሆነ ደራሲና ፈላስፋ ነው፡፡ በመፅሐፎቹ ውስጥ ለአንባቢያን ፍልስፍናዊ እሳቤዎቹን ከማሻገሩም በላይ የሚገርም የቋንቋ ክህሎት ባለቤት ነው፡፡ ገለፃዎቹ የሚያፈዙና ለጥበብ አፍቃሪ የሚያስፈነጥዙ ዓይነት ናቸው፡፡ ፈለቀ አበበ፤ የጂብራንን “ትናንት እና ዛሬ” የተሰኘ አጭር ልብ-ወለድ ወደ አማርኛ ሲመልስ፣ ተቀራራቢና ማራኪ በሆነ አማርኛ ነው። እውነት ለመናገር፣ ካህሊል ጂብራን፣ በእንግሊዝኛ የተራቀቀውን ያህል ፈለቀ በአማርኛ ተራቅቋል። “ውሸት!” የሚል ካለ፣ ልብ-ወለዱን አንብቦ ይፍረደኝ፡፡  
እንግዲህ በመጨረሻ ፈለቀ አበበ ምንድን ነው? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ መጠየቅም አግባብ ነው፡፡
ፈለቀ ተዋናይ ነው፡፡
ፈለቀ ተርጓሚ ነው
ፈለቀ ገጣሚ ነው
ፈለቀ አዘጋጅ ነው
ፈለቀ ፀሐፊ ነው
ፈለቀ….
ፈለቀ …
ሰናይ የእረፍት ጊዜ ይሁንላቸው!

Read 2236 times