Saturday, 23 December 2017 10:20

ለፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሁለተኛ ግልፅ ደብዳቤ

Written by  (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ)
Rate this item
(5 votes)

 ጉዳዩ--- ኦሮምኛን ተጓዳኝ የፌዴራል ቋንቋ ስለማድረግ
              (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ)

   “--ለምሳሌ ባለ 100ው ገፅ በላቲን የተፃፈው መፅሃፍ በ100 ሳንቲም ቢታተም፣ በግዕዙ የተከተበው ግን 40 ሳንቲም ብቻ ይሆናል። ሂሳቡ በሺ ብሮች ቢሰላ፣ በላቲን ቢፃፍ 6000 ብሮች ማዳን ይቻላል ማለት ነው። የዚህን ሁሉ ትርፍና ኪሳራ አይተው እርስዎ ይፍርዱ።---”

ክቡር ፕሬዚደንት ሆይ፡-
ክቡርነትዎ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት፤ ከአማርኛ ቀጥሎ ኦሮምኛ በሚሊዮን ኢትዮጵያውያኖች የሚነገር ትልቅ ቋንቋ ነው። ሆኖም እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። ካናዳ የተባለውን ሃገር እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ሁለት ብሄራዊ ቋንቋዎች አሉት--- እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ። የካናዳ ህዝብ፣ በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሁለቱን ቋንቋዎች ይችላሉ። ቋንቋዎቻቸው እኩል ተከብረው የፌዴራል መሥሪያ በመሆናቸው፣ የካናዳ ህዝቦች በዚህ ረገድ የእኩልነት ስሜት የሚሰማቸውና  የረኩ ናቸው።  በኢትዮጵያም ደረጃ ኦሮምኛም ከአማርኛ ጋር በተጓዳኝነት፣ የፌደራል ቋንቋ ቢሆን ብዙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ስነልቦናዊ ጥቅም ይኖረዋል። ይህን ግንዛቤዎ ውስጥ አኑረው፣ ኦሮምኛ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ ይሆን ዘንድ እርስዎ እና የሃገር አስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ የሚቻላችሁን ታደርጉ ዘንድ አሳስባችኋለሁ።
ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ የተወለዱና የማስተማሪያ ቋንቋቸውን ኦሮምኛ ብቻ ባደረጉ የትምህርት ተቋማት የተማሩ የኦሮሞ ወጣቶች፣ ሥራ ማግኘትን አስመልክቶ ተጎጂዎች ሆነዋል። እነዚህ ወጣቶች በክልላቸው መንግሥት የተነገራቸውን ተቀብለው በኦሮሚፋ ብቻ በመማር የትምህርት ጊዜያቸውን አባከኑ፡፡ በርካታዎቹ በትምህርታቸው በጥሩ ውጤት ከተመረቁ በኋላ ግን በፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ስለማያነቡና ስለማይጽፉ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙት የሥራ ዕድሎች ተወዳዳሪና ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ ሌሎች ዜጎች የሚያገኙትን ዕድል ያለ ጥፋታቸው የኦሮሞ ልጆች አጡ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪዎች ብልሆች ቢሆኑ ኖሮ፣ የሚፈጠረውን ችግር አስቀድመው ገምተው፣ የደቡብ ህዝቦች፣ ተጋሩዎችና ሌሎቹም ወንድሞቻችን እህቶቻችን እንዳደረጉት፣ ልጆቻቸው አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው እንዲማሩ አድርገው፣ የሥራ ዕድላቸውን ባሰፉላቸው ነበር፡፡ ያለፈው ቢያልፍም፣ ለዘለቄታው ግን ለዚህ ሁሉ የተሻለ መፍትሄ የሚሆነው ኦሮምኛ ሁለተኛ የማዕከላዊ መንግሥት ቋንቋ ቢደረግ ነው።        
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ይህስ ደግ ነው፣ ዳሩ ግን ኦሮምኛ በምን ፊደላት ይከተብ፣ የሚል ጥያቄ ሊከተል ይችላል--- በባዕዱ በላቲን ወይስ በሃገር- በቀሉ ኢትዮጵያዊ ፊደል?  በእኔ እና በሌሎችም ምሁራን ምርምር ውጤት መሰረት፣ ከላቲን ይልቅ፣ በተለምዶ ግዕዝ በሚባለው፣ እንደ እውነቱ ግን “ኢትዮጵያዊ ፊደል” መሰኘት በሚገባው ፊደል፣ ኦሮምኛ ቢፃፍ፣ እጅግ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ይህን አባባሌን ዝቅ ብዬ በማስረጃ አንተርሳለሁ።
የሚከተለውን የቁቤ ጽሁፍ ወስደን፣ ከግእዝና ከላቲን ፊደል የትኛው ይበልጥ ውጤታማና ብቁ እንደሆነ እንመለከታለን፡-
Uummanni  Oromoo ilmaan namaa biyya lafaa
ኡመኒ ኦሮሞ  ኢልማን  ነማ ብያ ለፋ
Kanarratti Uumaman kessaa tokkodha Biyyi
ከነረቲ ኡመመን ኬሳ ቶኮዳ ብዪ
Uumamaa fii jireenya issa    Aafrikaa Bahaa
ኡመማ ፊ  ጅሬኘ ኢሳ አፍሪካ በሃ
Gara kaabaatti Yemmuu ta’u Uummmata
ገረ ካባቲ የሙ ተኡ ኡመተ
Akata Sabaatti baay’ina    gudda qabu kan
አከ ሳባቲ የሙ ተኡ ኡመተ
Baha gaanfa Aafrikaatti argamu keessaa
ባሃ ጋንፋ አፍሪካቲ አርገሙ ኬሳ
Isa tokko Seenaan uummata kanaa akkuma
ኢሳ ቶኮ ሴናን ኡመተ ከና አኩማ
Sabaaf sab-lammaota Aafrikaa heddu namnii
ሳባፍ    ሳብ ላሞታ አፍሪካ ሔዱ
Seeraaf sirnaan qulqulleessee barreesse
ሴራፍ    ሰርናን ቁልቁሌሲ በሬሴ
Jiraachun baatullee uummata seenaa
ጂራቹ    ባቱሌ ኡመተ ሲና
Gudddaa fii gaarii qabu     akka ta’e huba
ጉዳ ፊ ጋሪ ቀቡ    አከ ተኤ ሁበ።
Chuun nama     hin dhiba
ቹን ነመ ሕንድቡ።
ከላይ ከቀረበው ናሙና ውስጥ የተወሰኑ ቃላትን እየጠቀስን፣ ኦሮምኛን ለመጻፍ ከላቲኑ እና ከኢትዮጵያው ፊደል የትኛው ብቁና ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ እንደሆነ እንይ፤ Uummanni Oromoo ilmaan namaabiyya lafaa“Uumamaa”  የሚለው ቃል በላቲን ሲጻፍ 7 ሆሄያት ፈጅቷል፡፡ በኢትዮጵያው ግን “ኡመማ” ተብሎ በ3 ፊደላት ይጻፋል፡፡ “oromoo” የሚለው ቃል በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን “ኦሮሞ” ተብሎ በ3 ሆሄያት ይጻፋል፡፡ “ilmaan” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት አሉት፤ በግዕዝ ግን አራት በቂው ነው፡፡ “namaa፣ biyya፣ lafaa፣” የሚሉትም ቃላት፣ በላቲኑ እያንዳንዳቸው 5 ሆሄያት ፈጅተዋል። በግዕዙ ቢሆን ግን “ነማ፣ ቢያ፣ ለፋ” ተብለው እያንዳንዳቸው በ2 ፊደላት ይጻፋሉ፡፡
ኡመኒ    ኦሮሞ ኢልማን ነማ ብያ ለፋ Kanarratt Uumama kessaa tokkodha Biyyi  የሚሉትን ደግሞ ስናይ “Kanarratti” በላቲን ሲጻፍ 10 ሆሄያት ያስፈልጉታል፡፡ በኢትዮጵያው ፊደል በግዕዙ ግን በ 4 ሆሄያት ይጻፋል፡፡  “Uumaman” በላቲን  7 ሆሄያት ያስፈልጉታል፡፡ በግዕዝ ግን 4 ሆሄያት ይበቁታል፡፡  “kessaa” የሚለው በላቲን 6 ሆሄያት ያስፈልጉታል፡፡ በራሳችን ፊደል ግን “ኬሳ” ተብሎ በ2 ፊደላት ይጻፋል።  “Tokkodha” እና “Biyyi” የሚሉትም  በላቲን እንደ ቅደም ተከተላቸው 7 እና 5 ሆሄያት ሲኖሯቸው በግዕዝ ግን 3 እና 2 ሆሄያት ብቻ ነው የሚኖራቸው፡፡ ነገሩ በገጽ ሲታሰብ፣ በላቲን 100 ገጽ የሚፈጅ ጹሁፍ፣ በግዕዝ ግን በ40 ገጽ ሊጻፍ ይችላል፡፡ ብዙ ሺ ኮፒ ሲታተም በላቲን ሲሆን አላግባብ የሚባክነውንና በግዕዙ ሲሆን ግን የሚቆጠበውን ስንትና ስንት ቶን ወረቀት አስቡት። ጊዜንና ገንዘብን በተመለከተም እንዲሁ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለ 100ው ገፅ በላቲን የተፃፈው መፅሃፍ በ100 ሳንቲም ቢታተም፣ በግዕዙ የተከተበው ግን 40 ሳንቲም ብቻ ይሆናል። ሂሳቡ በሺ ብሮች ቢሰላ፣ በላቲን ቢፃፍ 6000 ብሮች ማዳን ይቻላል ማለት ነው። የዚህን ሁሉ ትርፍና ኪሳራ አይተው እርስዎ ይፍርዱ።
ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ቀለማት ቢፃፍ የተሻለ ነው ሲባል፣ አንዳንድ የድሮ ፖለቲከኞችና የቀድሞ ታጋዮች የሚያቀርቧቸው ሰበቦች፣ “አንዳንድ የኦሮምኛ ቃላት በተለምዶ ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደላት ሊፃፉ አይችሉም፣ ለታይፕራይተርም አይመቹም፣” የሚሉ ናቸው። ይህ ግን እውነት አይደለም። ለምሳሌ አይቻሉም ተብለው የነበሩት ፊደላትና ቃላት በኦሮሚያዊትዋ ልጅ፣ በሰንዳፋው ተወላጅ  በዶክተር አበራ ሞላ መላ እነሆ ተችለዋል።
ዸዹዺዻዼዽዾዿ
ዹፌ፣ ዻባ፣ ዻራርቱ፣ ባዻዻ፣ ዼራ፣
ልክ እንደ ላይኛዎቹ ፊደላትና ቃላት፣ የኦሮሞ ቀለማት ሁሉ በኢትዮጵያ ፊደላት ተቀርፀው በተግባር ለመዋል እየጠበቁ ነው። እድሜ ለዶክተር አበራ ሞላ እ.ኤ.አ ከ1987 ጀምሮ በሶፍትዌር ደረጃ ተዘጋጅተው ገበያ ላይ ውለዋል። የአንዱን ቃል ከሌላው መለያ የማጥበቂያ ምልክቶችም ተበጅቶላቸዋል። ዶክተር አበራ ሞላ፤ የግዕዝ ፊደላት ለኦሮምኛና ለሌሎቹም ዋና ዋና ቋንቋዎቻችን መፃፊያ ብቁ እንዲሆኑ ለ35 ዓመታት ያህል ለፍቶባቸዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፊደላት የላቲኑን ሊተኩ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም። አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም ካልተባለ በቀር። የኢትዮጵያ ፊደላት ኦሮምኛን ለመክተብ ብቁ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ጥቅም ያላቸው መሆናቸውን የሚመሰክሩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል። ዊኪፔድያ ውስጥ ገብተው የዶክተር አበራ ሞላን የምርምር ውጤት  ይመልከቱ። አስፈላጊ ከሆነ እኔ እና ዶክተር አበራ ከአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ባዩ ይማም እና ከከሌሎች ቋንቋ ተመራማሪዎች ጋራ ሆነን ሴሚናር ተዘጋጅቶልን፣ ልንነጋገርባቸውና ተጨማሪ ማብራሪያ ልንሰጥባቸው እንችላለን። ፕሮፌሰር ባዩ ይማምም በበኩላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ብለው ሰፊ ጥናት አካሂደዋል።  
የኦሮምኛ ቋንቋ በማደጉና እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት፣ እንደ አማርኛው ሁሉ በላፕቶፕ፣ በግዕዙ ፊደል ተቀርፆ፣ ለወደፊቱ በገበያ ላይ እንደሚውል ከፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋራ ሆነው፣ ላፕቶፑን ያዘጋጁት፣ ወ/ሮ ገነት አየለ አብስረውኛል። እንዲያውም የላፕቶፑ ፋብሪካ፣ በባህርዳር ከተማ እየተተከለ መሆኑንም ሹክ ብለውኛል። ይህ ለኦሮምኛና አማርኛ ቋንቋዎች ደስ የሚል ዜና ነው።
ለእኛ ለአሁኑ ዘመን ሰዎች አዲስ ነገር ይመስለናል እንጂ ለኦሮሞ አባቶቻችን፣በኢትዮጵያ ፊደላት መፃፍ አዲስና እንግዳ ጉዳይ አይደለም። በቅርቡ በደርግ ዘመን እንኳን “በሪሳ” የሚል ጋዜጣ ነበር። ከዛሬ 120 ዓመታት በፊት ቄስ ኦናሲሞስ ነሲብ፣ ሙሉውን ቅዱስ መፅሐፍ፣ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕዩ ዮሃንስ ከትበውበት ነበር። ከዛሬ 200 ዓመት በፊትም እንደፃፉበት የሚያሳይ ሰነድ፣ በቀጣፊው “ጆግራፊ ላጠና ነው” ብሎ መጥቶ፣ ብርቅዬውን “መፅሃፈ ሄኖክ”ን ይዞ በኮበለለው በጀምስ ብሩስ እጅ ተገኝቷል። በመጀመሪያ በኦሮሞው ተወላጅ በታላቁ ፓስተር በኦኔሲሞስ ነሲብ፣ በግዕዝ ፊደላት ከተተረጎመው መፅሐፍ ቅዱስ ለናሙና ያህል ሁለት ገፆች ከዚህ ፅሁፍ ግርጌ አስፍሬአለሁ፡፡
ቀደም ሲል በግዕዝ ፊደላት በኦሮምኛ ስለተፃፉት ሰነዶች ሁሉ ጠቅለል አድርጎ ለመናገር 1ኛ. ከ16ተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተከተበ ቅዱስ ቁርአን በሀረር ይገኛል። 2ኛ. በ1845 ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን በፊት የመፅሐፍ ቅዱስ ወንጌላት በከፊል የተፃፉበት 3ኛ. ከላይ አንደጠቀስኩት፤ ከ120 ዓመታት በፊት በኦሮሞው ሊቅ በቅዱስ ኦኔሲሞስ ነሲብ (አባገመችስ) ሙሉው መፅሐፍ ቅዱስ በአፋን ኦሮሞ የተተረጎመበት 4ኛ. በ1967 ዓ.ም. ከ20 በላይ በሆኑ በተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ የመሬት አዋጅን ፈትፍቶና ቁልጭ አድርጎ የተገለፀበት 5ኛ. የኢትዮጵያ የመሠረተ ትምህርት ከ30 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች፣ በብቃትና በጥራት ይሰጥበት የነበረ 6ኛ. የ”በሪሳ” ታላቅ የአፋን ኦሮሞ ጋዜጣ ለዘመናት በበርካታ ቁጥሮች ሲሰራጭበት የነበረ 7ኛ. የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በበርካታ ባብዛኛው፣ ከ45 ብሔር ብሔረሰቦች በላይ ቋንቋዎች የተገለጡበት 8ኛ. በበርካታ የእስልምና ዝክሮች፣ መንዙማዎች የተፃፋበትና የተዘከሩበት 9ኛ. በርካታ የክርስትያን መዝሙራት በኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች የተገለጡበት 10ኛ. በአፋን ኦሮሞና በሌሎችም ከረጅም ዘመናት በፊት የመዝገበ ቃላት የተደራጀበት ናቸው። እንኳን ዛሬ ዳብሮ በኮምፒዩተር ሳይንስ ተደግፎ አይደለም፣ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ገና ድሮ ተፈትነው፣ ኦሮምኛን ለማስተናገድ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። በዶክተር አበራ ጥረት፣ በዩኒ ኮድ ዩኒቨርሳል ኮድ በመግባታቸው  ጠቀሜታቸው ተገልፆ፣ ዓለምአቀፍ ዕውቅናን አግኝተዋል።
ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በኣሁኑ ጊዜ ግዕዝ በዩኒኮድ ዕውቅና ያገኙትን የቢለን፣ ቤንች፣ ምኢን፣ ሙርሲ፣ ሱሪ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ኣገው፣ ኣውንጂ፣ አማርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ እና ግዕዝ ቋንቋዎች የሚጋሯቸውን ቀለሞችና ሌሎችንም ያስከትባል። ለእዚህም ተግባር የዶ/ር ኣበራ ሞላ ግዕዝኤዲት ገበያ ላይ ይውሏል። ኦሮምኛን ጨምሮ እሱ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች የፈፅመው ተግባር ሁሉ በሚከተለው የዊኪፒዲያ ሊንክ ማግኘት ይቻላል።  https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A3%E1%89%A0%E1%88%AB_%E1%88%9E%E1%88%8B# ግዕዝና_ኦሮሚፋ
የእንግሊዝኛ ወይም የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው ስለማይፃፉ፣ ስፔሊንጉን ለማወቅ የእድሜ ልክ ትግል ይገጥማል። በኢትዮጵያ ቀለማት ግን ሰው እንደሚናገረው ስለሚፅፍ፣ የስፔሊንግ  ስህተት ሊሠራ አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ወይም እንግሊዝኛ ፊደላት ይልቅ እሱን መምረጥ ይገባናል። እኛም እንደተጋሩ ወገኖቻችን ብልጥ መሆን ይገባናል። እነሱ በኢትዮጵያ ፊደላት እንጂ መቼ  በላቲን ይፅፋሉ? ኤርትራውያንስ መቼ የግእዝን ቀለማት አሽቀንጥረው ጣሉአቸው? ከኢትዮጵያ ተገነጠሉ እንጂ መቼ ከፊደላችን ተገነጠሉ? እንደውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በመገንዘባቸው ግን ፊደሎቻችን ላይ ሙጭጭ ብለው ይዘዋቸው ሄዱ። የኢትዮጵያ ፊደላት የሰሜን ሰዎችና የአማራ ብቻ አይምሰለን። ባለፉት 4000 ዓመታት ከሁላችንም አባት ከኢትዮጵ ጀምሮ በነገሥታት ልጅ ልጆቹ እየተቀረፀና እየተሻሻለ፣ ሲወርድ ሲዋረድ እዚህ የደረሰ ነው። ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አጋዝያን፣ መደበኛ ፊደላቱን ኢትዮጵያ ውስጥ አግኝተው፣ ለራሳቸው እንዲመቻቸው አድርገው ሞርደዋቸዋል። አማሮች ዘመዶቻችንም ለእነሱ አፍ የሚስማሙ የተወሰኑ ፊደላትን ቀርፀው እውስጣቸው አካተዋል። ስለዚህ ፊደላቱ የኦሮሞም ናቸው። በእርግጥም ናቸው እንጂ ባይሆኑም እንኳ  ከማናውቃቸው ከባእዳኑ ከአውሮፓውያኖቹ ፊደላት ይልቅ የተፈጠርንበትና የኖርንባት የኢትዮጵያ ፊደላት ለኛ ይቀርቡናል።  
ከቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ!  በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ፍቅር መንደድዎን፣ ባህርዳር በነበሩ ጊዜ አሳይተውን ነበር። ኢትዮጵያዊነት፤ የኢትዮጵያን ፊደላትንም ይጨምራል። ስለዚህ ይህን ጉዳይ አተኩረው ያስቡበት። ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት መጫፈ ቁሉን ጨምሮ ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ፊደላት እጅግ ብዙ ፅፎበታል። በዚህ አጋጣሚ አንድ ጥያቄ እንዳቀርብ ይፍቀዱልኝና ባለፉት 26 ዓመታት በቁቤ ወይም በላቲን ፊደላት ምን ያህል የረባ መፃህፍት ተከትበዋል? ከኦሮሞ ሰፊው ህዝብ ውስጥስ ምን ያህሉ ነው በቁቤ የሚፅፍና የሚያነብ? ነው ወይንስ እንደው ለወጉ ነው ቁቤ ቁቤ የምንለው? እዚህ ላይ ብርሃን የሚረጭ ጥናት ቢኖር እንዴት ሸጋ ነበር። ለማንኛውም ቁጥራቸው በዛም አነሰም ቁቤ የሚችሉ ሰዎች፣ በግለሰብ ደረጃ አሁንም በቁቤ እንዳይገለገሉ የሚያግዳቸው የለም። እርስበርሳቸውም ሆነ ለየብቻቸው በቁቤ መጠቀማቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። በሃገር ደረጃ ግን ከላቲን ይልቅ ግዕዝ በጣም በርካታ ጥቅም ስላለው ነው ኦሮምኛ ሁለተኛ የፌዴራል ቋንቋ ሆኖ፣ በግዕዝ ፊደላት ይፃፍ ብዬ የምመክረው። ኢትዮጵያዊው ፊደል በሀገር ደረጃ ፀድቆ ከተተገበረ፣ ከመዋዕለ ህፃናትና ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሊደርስ ይችላል። በእድሜው የገፋውን አዛውንት ሳያስጨንቁ በህፃናቱ ቢጀመር ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጪው ትውልድ ይዳረሳል። ይህን ጉዳይ ለመተግበር ደሞ ለእርስዎና ለሃገር አስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እሺታ እና ትብብር ያሻችኋል። ይህ በቶሎ የሚፈፀም ነገር ስላልሆነ፣ ለጊዜው ቅዱሱ ሃሳቡ ይንሸራሽር።  
ደብዳቤዬን ለመደምደም፣ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ ቁጥር በጣም በርካታ ስለሆነ፣ ካናዳ ውስጥ እንግሊዝኛንና ፈረንሳይኛን የሥራ ቋንቋዎች አድርገው እንደሚሠሩባቸው ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ከአማርኛ ጎን ለጎን ኦሮምኛ፣በኢትዮጵያውያኑ ፊደላት እየተከተበ፣ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ሊተጋበት ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ፣ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተመዘነ፣ አዋጭነቱ በሳይንሳዊ መንገድ እየተረጋገጠ፤ አማርኛን እንደ ሁለተኛ ቋንቋቸው በተቀበሉ እንደ ደቡብ ክልል ባሉ ሕዝቦች ላይ ጭነት አለመሆኑም እየተጣራ፣ በጥንቃቄ ሊመከርበት ግድ ይላል፡፡ ኦሮሞ ያልሆኑ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ሌሎችም አያሌ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዓት ኦሮምኛን መማር ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን በባዕዱ ፊደል በላቲን ተማሩ ከምንላቸው ይልቅ ሁሉም በሚያውቁት በኢትዮጵያ ፊደላት እንዲማሩ ብናመቻችላቸው በቀላሉ ሊቀስሙት ይችላሉ።  በግድ በላቲኑ ተማሩ ካልናቸው ግን፣ “ጊዜና ገንዘብ ከሚያባክነው ከላቲኑ ፊደል ይልቅ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነውና በምናውቀው ባገራችን ፊደል እንጽፋለን” ቢሉ፣ ይህ አቋማቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ክቡር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ሆይ! እርስዎ አንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪካውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና  እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝቦች፤ ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን  አይገባም። በእዚህ እና እላይ በተዘረዘሩት የአመክንዮ ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ ይህን የተቀደሰ ጉዳይ ትጉበት። ከዚያም ውጤቱ ለህዝባችን ልብ የሚያኮራና ለኑሮም የሚበጅ ይሆናል።
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ፓስተር ኦኔሲሞስ ነሲብ፣ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጎመው የኦሮምኛ ቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ የወሰድኳቸውን ሁለት ገፆች ከዚህ በታች አስፍሬለዎታለሁ። የዛሬ 120 ዓመት እንኳን፣ ቅዱስ መፅሐፍን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ-ኮምፒዩተር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን ግዕዝ በሚባለው ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለ ችግር መክተብ እንችላለን።  ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ብቻ ነው!!

Read 3581 times