Sunday, 24 December 2017 00:00

እንጠንቀቅ! ይህች አገር… መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት!

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(7 votes)

 በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አማካኝነት እየጦዘ የሚገኝ የስልጣን ሽኩቻ! በኢኮኖሚ ችግር ላይ ታክሎበት!
               
   በአዲስ አድማስ ጋዜጣ እትሞች፤ ባለፉት አስር ዓመታት ከቀረቡ ዘገባዎች መካከል ጥቂቶቹን ቀንጨብ እያደረግን እንመልከት - የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አሳፋሪ መዘዞችን ለማሳየትና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በጊዜ እንዲስተካከሉ የሚያሳስቡ ፅሁፎች ናቸው፡፡

አደገኛ የስልጣን ሽኩቻ!... ጣጠኛ ነው!
(ነሐሴ 5 ቀን 2004 ዓም)
የስልጣን ሽኩቻ፣ የመሪዎች መተካካት አልያም “የስልጣን ሽግግር” ተብሎ ቢሰየም እንኳ ለውጥ የለውም - በቃ የስልጣን ሽኩቻ) ጣጠኛ ነው - ሌሎች ችግሮችን ጎትቶ ያመጣል ወይም ያባብሳቸዋል። ለምሳሌ የሙስና ወረርሽኝ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። አለመረጋጋትም ይኖራል።…
መጥፎነቱ ደግሞ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ መንግስት ብዙ ነገር ውስጥ እጆቹን ስላስገባ የሙስና መንገዶችና እድሎች እንደ ጉድ ተበራክተዋል። (እናም፣…) መንግስት “ሲንገራገጭ”፤ ሁሉም ነገር “ይንገጫገጫል” ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ታስታውሱ እንደሆነ፤ በ93 ዓ.ም የኢህአዴግ ትኩረት በመሪዎቹ የስልጣን ሽኩክቻ ላይ ነበር። በ97 ዓ.ም ደግሞ ከምርጫ ቀውስ ጋር ተያይዞ፣ የኢህአዴግ ትኩረት በፓርቲዎች የስልጣን ሽኩቻ ላይ ነበር ያነጣጠረው። ከእነዚህ “የስልጣን ሽግግር” ችግሮች ጋር ነው፤ የሙስናና የግጭቶች ወረርሽኝ ሲባባስ ያየነው - ተጨማሪ ጣጣ።
አሁንስ? አሁንም የኢህአዴግ ትኩረት “የስልጣን ሽግግር” (የስልጣን ሽኩቻ… የመሪዎች መተካካት) ላይ ሲያነጣጥርና ሲጠመድ፤ በየአቅጣጫው ሌሎች ችግሮች መባባሳቸውና መፈልፈላቸው ይቀራል? “የስልጣን ሽግግር” ለኢህአዴግ ፈታኝና ከባድ ስራ ነው። (አደገኛ የስልጣን ሽኩቻ ነው ቢባል ይሻላል። እናም ያሰጋል፤ ያስፈራል፤ ያቃውሳል። የስልጣን ሽኩቻ የሚጥማቸው፣ ቀውስና ትርምስ የሚያስጎመጃቸውም አሉ። )

(የኢህአዴግ የስልጣን ሽኩቻ! እና የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ!)
በአንድ በኩል፤ … አገሪቱ ምን ይውጣታል ብለው የሚሰጉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአገሪቱ ኋላቀር ባህል ሳይለወጥ የመንግስት መሪዎች ወይም ገዢ ፓርቲዎች ስለተቀየሩ ብቻ አንዳች ተአምር ይፈጠራል ብለው የሚጠብቁ አሉ። በአንድ በኩል ስልጣንና ጥቅም እናጣለን ብለው የሚብሰለሰሉ የስልጣን ጥመኞችና ጥገኞች ይኖራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣንና ጥቅም ለመቀራመት የሚያቆበቁቡ ስልጣን ናፋቂዎችና ተስፈኞች ይኖራሉ።
በአንድ በኩል፤ በብሄረሰብ እና በሃይማኖት የመቧደን ጭፍንነት እንዳይባባስና እንዳይፈነዳ የሚሰጉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በጭፍን የመቧደንና ሱስ ግጭት የመፍጠር አባዜ የሚያቅበዘብዛቸው አሉ - በ1993 ዓ.ም የኢህአዴግ መሪዎች ተከፋፍለው ፀብ ውስጥ የገቡ ጊዜ በየአቅጣጫው የተፈጠሩትን ግጭቶች ማስታወስ ይቻላል።
በአንድ በኩል አለመረጋጋት እንዳይከሰት፣ ስራ እንዳይስተጓጎል፣ ኑሮ እንዳይመሳቀል የሚጨነቁ አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ለመቦጨቅ የሚቁነጠነጡ የሙስና ረሃብተኞች አሉ። በ97ቱ የምርጫ ቀውስ ማግስት የተከሰተው የመሬት ወረራና የሙስና ወረርሽኝን መጥቀስ ይቻላል።
በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ሽግግር በፈተና የተሞላ ነው። (የስልጣን ሽግግር፣ በኢትዮጵያ፣ አደገኛ የስልጣን ሽኩቻ ነው!)

በመንግስት የስልጣን ሽኩቻ… አገር ምድሩ ይናወጥ?  
ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት የኢህአዴግ መሪዎች ዋና ትኩረት በዚሁ የስልጣን ሽግግር ዙሪያ ላይ የሚያነጣጥር ከሆነ፤ በሌሎች አቅጣጫዎች ሌሎች ችግሮች የሚፈጠሩበት ወይም የሚባባሱበት እድል ይፈጠራል። በምርጫ 97 ቀውስ እንዲሁም በ93ቱ የመሪዎች ሽኩቻ ወቅት ከተፈጠሩትና ከተባባሱት ችግሮች ጋር የሚመሳሰል ጣጣ ማለቴ ነው፤ ለምሳሌ የሙስና ወረርሽኝ። ለዚያውምኮ ያኔ ብዙ የሙስና እድሎች አልነበሩም። ዛሬ ግን የሙስና እድሎች በብዙ እጥፍ ጨምረዋል፤ ሰፍተዋል።
መንግስት የቱን ያህል በቢዝነስ ስራ ውስጥ እንደገባ ተመልከቱ - በየአመቱ ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅስ ሆኗል። የስኳር ኮርፖሬሽንን፣ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ የባህር ትራንስፖርት እስከ መሃል ከተማ፣ በየክልሉ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች... ብዙ ቢሊዮን ብሮች ወዲህ ወዲያ የሚሉበት የቢሮክራሲ መረብ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የሃብት ብክነትና የሙስና አይነት ለቁጥር ያስቸግራል። ይህም ብቻ አይደለም።
መንግስት የግል ቢዝነሶች ላይ የቱን ያህል አላስፈላጊ ጣልቃ ገብ ቁጥጥሮችን እንዳበራከተ አስተውሉ። በተለይ ባለፉት አምስት አመታት አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥሮች እንደአሸን ፈልተዋል። ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ፣ የዋጋ ቁጥጥር፣ የጡረታ ታክስ፣ የጋዜጣ የማስታወቂያ ቁጥጥር፣ የታክሲ ስምሪት ቁጥጥር፣ የባንክ ቦንድ ግዢ ቁጥጥር... በየአቅጣጫው የመንግስት ገናናነት እየገዘፈ ሲሄድ፤ የባለስልጣናትና የቢሮክራቶች የሙስና እድሎችም በዚያው መጠን ይሰፋሉ፤ ይስፋፋሉ። የተመቸ ጊዜ ያገኙ ሲመስላቸው ደግሞ የሙስና እድሎች የሙስና ወረርሺኝ ይሆናሉ።
ግን መፍትሄ አላቸው። አላስፈላጊዎቹን ቁጥጥሮች አንድ በአንድ ለመሰረዝ ከባድ አይደለም። መንግስት ቢዝነስ ውስጥ የመግባት ዘመቻውን እንዲገታ ማድረግም ቀላል ነው። ቀስ በቀስም፤ በመንግስት የተቋቋሙትን ቢዝነሶች በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል ማዛወር ይቻላል። የመንግስት ገናናነት ሲቀንስ፤ ቢዝነስ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪነቱ ሲከስም፤ ከዜጎች እየወሰደ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ገደብ ሲበጅለት...፤ ለዘለቄታውም ጥሩ ይሆናል - የሙስና እድሎች ከመጥበባቸውም በላይ፤ የመንግስትን ስልጣን መያዝ ያን ያህልም አጓጊና አስጎምጂ መሆኑ ይቀንሳል። እናም ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አመቺ ይሆናል።
የተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተናዎች
መስከረም 5 ቀን 2005
ቢዝነስ መዳከሙ፣ ስራ አጥነት መግነኑ - የወጣቶችና የተመራቂዎች
ኢትዮጵያ እንደ ወትሮው ዛሬም እጅግ ድሃ አገር ነች። (በእርግጥ)… በዜጎች ኑሮ ላይ የመጣው ለውጥ አነስተኛ ቢሆንም፤ …የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል። እንዲያም ሆኖ፤ ዛሬም ጭምር፣ ኢትዮጵያ በአለማችን ከአስሩ የመጨረሻ ድሃ አገራት መካከል አንዷ ነች።
በገጠር፤ አመቱን መዝለቅ የማይችሉ የሴፍቲኔት ተረጂ ችግረኞች እንዲሁም ደራሽ እርዳታ የሚጠብቁ የረሃብ ተጠቂ ዜጎች ቁጥራቸው፤ ከ11 ሚ. በላይ ነው። በከተማም፤ የብዙ ዜጎች ኑሮ ከድህነት ወለል በታች እንደተቀበረ ነው። በተለይ ባለፉት… አመታት የተከሰቱት ከፍተኛ የዋጋ ንረት ቀውሶች የከተሜዎችን ኑሮ አናግተዋል። ከድህነቱ ጋር፤ የወጣቶችና የተመራቂዎች ስራ አጥነትም ከባድ ፈተና ነው። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ መዳከምም፤ እጅግ ያሳስባል። መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል።

የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ…. ዘረኝነት
ረሃቡ፣ ድህነቱና ስራ አጥነቱ፤ በ”መንግስት ኢንቨስትመንት” እንደማይፈታ፣ የአገራችንና የሌሎች በርካታ አገራት የቅርብና የሩቅ ታሪኮች በግልፅ ይመሰክራሉ። እንዲያውም ኢኮኖሚው ውስጥ መንግስት ገናና እየሆነ በመጣ ቁጥር፤ በዚያው መጠን የሃብት ብክነትና ሙስና ነው የሚስፋፋው።
በተለይ በኢትዮጵያ መዘዙ የከፋ ነው። ኢትዮጵያ ከቻይናና ከደቡብ ኮሪያ በእጅጉ ትለያለች። እነሱ እንደኛ ብዙም ከብሄረሰብና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጣጣዎች የሉባቸውም።
እንደ ኢትዮጵያ፣ በብሄር ብሄረሰብና በሃይማኖት የመቧደን ስር የሰደደ ኋላቀር ባህል ባለበት አገር ግን፤ ስራ አጥነትና ሙስና የመሳሰሉ የኑሮና የኢኮኖሚ ችግሮች በሙሉ በሰበብ አስባቡ ከብሄር ተወላጅነትና ከሃይማኖት ተከታይነት ጋር እየተያያዙ መዘዝ ያመጣሉ፤ ለዘረኝነትና ለቡድንተኝነት ቀውስ የሚያጋልጡ አደጋዎች ይሆናሉ። ስለዚህ፤ የወደ ፊት የመንግስት ስራ፣ የነፃ ገበያ ስርዓትን ማስፋፋትና አስተማማኝ መሰረት ላይ መገንባት ሊሆን ይገባል።

የማንነት ቀውስ…
(ኅዳር 26 ቀን 2002 ዓ.ም)
አሁን በአገራችን ከሁሉም በላይ አሳሳቢውና ዋነኛው የማንነት ቀውስ ምልክት፤ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ነው።
በአገራችን ዋነኛው የማንነት ቀውስ ምልክት - የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ!
ልጆቹን እንግሊዝኛ እያስጠና፤ ስለብሄረሰብ ቋንቋ የሚደሰኩር ፖለቲከኛ!
ከተማን እየቀወጡ፤ ገጠሬና ገበሬ ለመምሰል የሚታገሉ ዘፋኞችና ዳንሰኞች!
የሳጠራ ሬስቶራንት፤ ለመኝታ የሳር ጎጆ የሚሰራ ባለቪላ ባለፎቅ ኢንቨስተር!
ኋላቀር ኑሮን እያደነቀ፤ በኮምፒዩተር አፅፎ በሲዲ የሚያሳትም ደራሲ!
የአሜሪካን ስልጣኔ አትመኙ በማለት ተነዛንዞ የሚሄድ የዳያስፖራ ምሁር!
ጥንታዊ ዜማዎችን “የኛ ሙዚቃ” ብሎ የሚያቀርብ የዘመናችን ቲቪ!
ቴክኖሎጂን እየተቃወመ፤ ኑሮ እንዲመቸው የሚመኝ የአካባቢ ጥበቃ ሰባኪ!

የማንነት ቀውስ፤… ላይ ላዩ ብዙ መልክ ቢኖረውም፤ በየጊዜውም አንደኛው ወይም ሌላኛው መልክ ጎልቶ ቢታይም፤ ሁሌም መሰረታዊ ባህሪው ተመሳሳይ ነው። በተለያዩ ሰበቦችና ስህተቶች የተነሳ፤ “ሃሳብ ወዲህ፤ ተግባር ወዲያ”፤ “ትምህርት ወደ ላይ፤ ስራ ወደ ታች”፤ “ወሬ በምስራቅ፤ ኑሮ በምእራብ” ሲበታተን፤ ማንነት ይቃወሳል፤ ይዘበራረቃል። አሁን በአገራችን ከሁሉም በላይ አሳሳቢውና ዋነኛው የማንነት ቀውስ ምልክት፤ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ነው - በብሄረሰብ መቧደንና መደራጀትን ጨምሮ። ኋላቀርነትንና ድህነትን የማምለክ ስህተቶችም፤ የማንነት ቀውስን የሚመሰክሩ እንደሆኑ ለማሳየት እሞክራለሁ።

“የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ” - ማንነትን አይሰጥም፤ ያቃውሳል እንጂ!

የዚህኛው ብሄር ወይም የዚያኛው ብሄረሰብ ተወላጅ መሆን፤ አእምሮ ውስጥ እውቀትን አይጨምርም ወይም አይቀንስም፤ በተግባርም ምርትን አያበረክትም ወይም አያሳንስም። መንፈስ ወይም ባህርይ ደግሞ፤ የአእምሮና የአካል፤ የእውቀትና የተግባር ውህደት ስለሆነ፤ የብሄረሰብ ተወላጅነት ወሳኝ አይደለም፤ ቀና ወይም ጠማማ፤ ታታሪ ወይም ሰነፍ አያደርግም። በሌላ አነጋገር፤ ማንነት የግል ነው። የግለሰቦች ማንነት ላይ ተመሳሳይነት ሲኖር፤ “ይህች፤ ይህች የጋራቸው ነች” እንላለን እንጂ፤ በተቃራኒው ከቡድን ወደ ግለሰብ አይወራረስም - ማንነት። የብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት፤ በሰዎች ማንነት ላይ ድርሻ የለውም። ድርሻ እንዳለው፤ ከዚያም አልፎ ወሳኝ እንደሆነ ስናስመስል ነው፤ የማንነት ቀውስ ፈጥጦ የሚታየው።
አንደኛ፤ አእምሮን እንመልከት። እውቀት በተወላጅነት አይለካም አይደለም? የብሄረሰብ ተወላጅነት፤ እውቀት ማስገኘትም ሆነ ማሳጣት እንደማይችለው ሁሉ፤ የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የሶማሌ፤ የትግሬ እውቀት ብሎ ነገርም የለም። ከግሪክም ሆነ ከአሜሪካ፤ ከጃፓንም ሆነ ከጋና፤ ከብራዚልም ሆነ ከኢትዮጵያ፤ ከየትኛውም አካባቢ የመጣ፤ በማንኛውም ሰው የተፃፈ መፅሃፍ፤ በቁሙ አልያም በትርጉም በማንበብ እውቀት እናገኛለን። ሰዎችንም የምናደንቀውና የምንወቅሰው፤ የምንወዳጀውና የምንርቀው፤ ለእውቀት መስፋፋት በሚኖራቸው አስተዋፅኦ ይሆናል - በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት መሆን አይገባውም።
ሁለተኛ፤ አካልን እንመልከት። የእያንዳንዳችን ምርት በብሄረሰብ ተወላጅነት አይወሰንም አይደለም? የምናመርተውና የምንነግደው፤ እቃ የምንገዛውና የምንሸጠው፤ በአጠቃላይ ከምግብና ከልብስ ጀምሮ እስከ ሞባይልና አውሮፕላን፤ በየእለቱ ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የምናሟላው እንዴት ነው? የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ ተወላጅ ፋብሪካ፤ ሱቅ፤ መኪና እያልን ነው? አይደለም። በማንም ይሰራ፤ ከየትም ይምጣ፤ የትም ይሂድ፤ የእቃውን ጥራትና ዋጋ አመዛዝነን፤ ጥቅሙን አስልተን ነው የምናመርተው፤ የምንገበያየው፤ የምንገለገልበት። ሰዎችን ተግባር የምንመዝነውም በዚሁ መለኪያ እንጂ በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት መሆን የለበትም።
እንዲህ በአእምሮ እውቀትን እያሰፋ፤ በአካል ምርትን እያሳደገ፤ ሁለቱን አጣጥሞ ህይወቱን የሚመራ ሰው፤ እውቀት ምርትን እንዲያበረክት፤ ምርትም በተራው ለተጨማሪ እውቀት በር እንዲከፍት የሚያደርግ ባህርይ ወይም መንፈስ ይጎናፀፋል - አስተዋይነት፤ ቀናነት፤ ብሩህነት፤ ታታሪነት፤ ጠንካራነት የመሳሰሉ፤ አእምሮንና አካልን በህብር የሚያዋህዱ ባህርያትን።
አእምሮና አካል፤ ከዚያ መንፈስ... በቃ በእነዚህ የተገነባ ነው የእያንዳንዱ ሰው ማንነት። በአእምሮ በኩል ትምህርትና ፍልስፍና፤ በአካል በኩል ደግሞ ምርምርና ጥናት፤ በጋራ የብሩህነትና የተነሳሽነት መንፈስን ይፈጥራሉ። ግንዛቤዎች እንዲሁም፤ “ያኛው ነገር ጠቃሚ፤ ይሄኛው ነገር ጎጂ” የሚሉ ሃሳቦች በአእምሮ ውስጥ፤ በአካል ደግሞ ነገሮችን መፈተሽ፤ መሞከር፤ መቅመስ... ሁለቱ በጋራ፤ መልካም ነገሮችን የመፈለግ፤ የማፍቀር፤ የመመኘት ስሜቶችን ይገነባሉ። ራዕይ፤ አላማ፤ መርህ በአእምሮ ውስጥ፤ በአካል ከሚከናወኑት ስልጠና፤ ልምምድ፤ ጥረት ጋር ህብር ሲፈጥሩ፤ ችሎታ፤ ልምድ፤ ክህሎት የመሳሰሉ ልክ እንደ “ሁለተኛ ተፈጥሮ” የምንቆጥራቸው አውቶማቲክ ባህሪያት እውን ይሆናሉ።
በዚህም አያቆምም። አእምሮ ተጨባጭ እቅዶችን ይነድፋል፤ ውሳኔዎችን ያሳልፋል። ይህም በተግባርና በስራ ሲተረጎም... እንዲህ ሁለቱ ሲጣጣሙ፤ የታታሪነት፤ የፅናት፤ የትጋት መልካም ባህሪዎችን ያስገኛሉ። በመጨረሻም፤ “ምን አከናወንኩ?” ብሎ በአእምሮ አገናዝቦና አስልቶ መመዘን ይኖራል። በአካል ደግሞ፤ ውጤቱ ይታያል፤ ምርት፤ ሃብት፤ ብልፅግና። የሁለቱ መጣጣም በጋራ፤ በራስ የመተማመን፤ የእርካታ፤ የኩራት፤ የደስታ መንፈስን ያቀዳጃል። እንዲህ ከአእምሮ፤ ከአካልና የሁለቱ ውህደት ከሆነው መንፈስ ውጭ፤ ማንነት ብሎ ነገር የለም።
ራሳችንንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን የምንመዝነው፤ ከአእምሮአዊና ከአካላዊ ገፅታዎች፤ እንዲሁም ሁለቱ በጥምረት ከሚያሰርፁት መንፈስ ጋር በማገናዘብ ነው - ወደ ሶስት የግንኙት አይነቶች የሚያመሩ ሶስት ጥያቄዎችን በማንሳት።
አንደኛ፤ “ይሄ ሰውዬ፤ እውቀቱ፤ ሃሳቡ፤ መርሁ፤ አላማው፤ እቅዱ እንዴት ነው?” ብለን እንጠይቃለን። በዚህ መመዘኛ ነው አዕምሮአዊ ግንኙነት መፍጠር የሚኖርብን - የመማማርና ሃሳብ የመለዋወጥ፤ በሳይንስ ዘርፍና በቢዝነስ መስክ ሃሳብ እያመነጩ የመወያየት፤ የማህበርና የፓርቲ መርሆችን የማርቀቅ ግንኙነት። ሁለተኛው ጥያቄ፤ “ያኛው ሰውዬ፤ ጥናትና ምርምሩ፤ ልምምዱና ጥረቱ፤ ስራውና ተግባሩ ምን ይመስላል?” የሚል ነው። በዚህ መመዘኛም፤ ከሰዎች ጋር በስራ ቅጥርና በኮንትራት፤ በግብይትና በአክስዮን፤ በማህበርና በፓርቲ አደረጃጀት በመሳሰሉ መንገዶች የምርትና የተግባር ትብብር መመስረት ይቻላል - አካላዊ።
ሶስተኛው ጥያቄ በአእምሮአዊና በአካላዊ ፈርጆች ጥምረት የሚፈጠሩ የብሩህ መንፈስ ባህርያትን የሚመለከት ነው - “ሰውዬው፤ አስተዋይነቱ፤ ቀናነቱ፤ ለመልካም ነገሮች ያለው ፍቅር፤ ችሎታው፤ ታታሪነቱ፤ ፅናቱ ምን ያህል ነው?” የሚል። በዚህኛው መመዘኛም፤ መንፈሳዊ ግንኙነቶችን መመስረት ይቻላል - ፍቅርና ወዳጅነት፤ አድናቆትና አክብሮት የመሳሰሉ።
በእነዚህ ሶስት ጥያቄዎች ነው፤ የየራሳችንም ሆነ የሌሎችን ሰዎች ማንነት መመዘን እንዲሁም ግንኙነቶቻችንን መምራት የሚገባን።
የሰው አእምሮአዊ፤ አካላዊና መንፈሳዊ ገፅታዎች የተነጣጠሉ ነገሮች ባለመሆናቸው፤ ሶስቱን ጥያቄዎች በአንድነት ብናጠቃልላቸውስ? በአጭሩ “ከሰው ተፈጥሮ ጋር በተስማማ መንገድ፤ የቱን ያህል አእምሮንና አካልን ያጣጣመ ስብእና ገንብቷል?” በሚል ጥያቄ ልንተካቸው እንችላለን። ታዲያ የማንነት መመዘኛ ይሄ ሆኖ ሳለ፤ የብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ምን አመጣው? ምንስ ያስከትላል? የአእምሮና የአካል፤ የሃሳብና የተግባር አለመጣጣምን፤ እናም የመንፈስ፤ የስሜትና የባህርይ መዘበራረቅን ያስከትላል። ማለትም የማንነት ቀውስ። ለምን?
በፖለቲካ ሃሳቦች ዙሪያ ስለ ፓርቲ መርህና ፖሊሲ መወያየት (አእምሮአዊ ግንኙነት መፍጠር) የሚቻለው፤ እውቀት፤ ሃሳብና መርህ ከያዙ ሰዎች ጋር ነው። በአካልና በተግባር ግን፤ የሰዎችን እውቀትና ሃሳብ ሳይመዝኑ፤ እንዲሁ በጅምላ በብሄረሰብ ተወላጅነት ወደ መቧደንና ወደ መደራጀት ያመራል - የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ። የአእምሮና የአካል፤ የሃሳብና የተግባር ግጭት ይሄው ነው። የአንድ ብሄር ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች በሙሉ፤ በእውቀትና በተግባር፤ በሃሳብና በጥረት ይለያያሉ። ይህን በተጨባጭና በተግባር እያዩ፤ የመርህና የአላማ ተመሳሳይነት በብሄረሰብ ተወላጅነት የሚመጣ አስመስሎ ማሰብ ምንን ይመሰክራል? የአእምሮና የአካል ጦርነት። በተጣጣመ መንገድ የጠራና የፀና ስብእና መፍጠር ሲገባ አእምሮንና አካልን እያናከሱ፤ ሃሳብና ተግባርን በተለያየ አቅጣጫ መበተን፤ ቀስ በቀስ የ”ማንነት”ን አድራሻ ያሳጣል። ከብሩህ መንፈስና ከቅንነት ይልቅ፤ እልህና መመቀኛኘት፤ ከወዳጅነትና ከአድናቆት ይልቅ፤ መሻኮትና መጠላለፍ፤ በፓርቲዎች ውስጥ በርክቶ መታየቱስ ይገርማል?
ከሁሉም በላይ ግን፤ የብሄረሰብ ተወላጅነት የማንነት መሰረታዊ ምንጭ እንዳልሆነ እየታወቀ፤ የራስን ማንነት በዚያ ላይ ለመመስረት መሞከር ነው፤ ትልቁ የማንነት ቀውስ። እንኳን የብሄረሰብ ተወላጅነትና ቋንቋ ቀርቶ፤ ቤተሰብም የማንነት መሰረት አይደለማ።
እንጠንቀቅ! ይህች አገር የብልፅግና ተስፋና የመናጋት አደጋ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች
(ግንቦት 2006 ዓ.ም) Saturday, 10 May 2014 12:11
ስለ ፖለቲካ ወይም ስለ ኢኮኖሚ ወሬ በተነሳ ቁጥር፤ አፍታም ሳይቆይ በጭፍን የዘረኝነት ስሜት ውስጥ መዘፈቅና መንቦራጨቅ ይጀምራል። ኢትዮጵያን የሚመለከቱ የኢንተርኔት ወሬዎችንም መመልከት ትችላላችሁ።
እናስተውል! ስልጡን ጎዳና ከያዘች የሚያስቆመን አይኖርም፤ ከተናጋችም መመለሻ የለንም
ተቃውሞውና ረብሻው የብሄር ብሄረሰብ ቅኝት መያዙም፣ የዘመናችንን አደጋ ያመለክታል
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱ ጎላ ጎላ ያሉ ችግሮችንና ውዝግቦችን ተመልከቱ። አንዳንዶቹ፣ ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር የተያያዙ ቀውሶች ናቸው። ገሚሶቹ ደግሞ፤ ከጎሰኝነት ወይም ብሔረተኝነት ጋር የተቆራኙ። የብዙዎቹ መነሻ ግን ጭራና ቀንዱ የማይታወቅ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ነው። የሦስቱን ቀውሶች ግንኙነታቸውን ለማየት፤ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስን በማንሳት ልጀምር።
“ድሆችን ለመደገፍና ሰፊውን ህዝብ ለመጥቀም ወይም አገርን ለማልማት” በሚሉ ሰበቦች መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ እየገነነ ሲመጣ፣ ሃብትን ከማባከን ያለፈ ውጤት አይኖረውም። በዚያውም ሙስናን ያስፋፋል።
መንግስታት ስራዬ ብለው የዜጎችን ሃብት በእልፍ መንገድ ማባከንን ከተያያዙት፤ እዳ መቆለሉ፣ ሙስና መስፋፋቱ፣ ኢንቨስትመንት መንቀራፈፉ፣ የሰራ እድል መጥፋቱ፣ ኑሮ መክበዱ የማይቀር ነው። የቅይጥ ኢኮኖሚ የቀውስ አዙሪት!
የሊቢያና የግብፅ፣ የሶሪያና የኢራቅ፣ የሴንትራል አፍሪካና የናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካና የኮንጎ ግጭቶችና ትርምሶች... በሙሉ ከቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የተሳሰሩ ቢሆኑም ውለው አድረው የጎሰኝነት ወይም የብሔረተኝነት ቀውስ እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁት በአጋጣሚ አይደለም። በአጭሩ፤ ሶስቱ ቀውሶች፤ (የቅይጥ ኢኮኖሚ አዙሪት፣ የጎሰኝነት (የብሔረተኝነት) አባዜ እና የሃይማኖት አክራሪነት)፤ አለምን ከዳር ዳር ያዳረሱ የ21ኛው ክፍለዘመን መለያ ቀውሶች ናቸው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ቀውሶች ውጭ አይደለችም። ከሌሎቹ አገሮች አትለይም።
ቀውሶቹን ለመከላከል ወይም ለመግታት እያንዳንዱ አገር ውስጥ በሚከናወን ዝግጅትና ጥረት ነው ልዩነት የሚመጣው። የኛ አገር ሁኔታ እጅጉን አሳሳቢ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። ዝግጅትና ጥረት ሊከናወን ይቅርና፤ አደገኛዎቹን ቀውሶች በቅጡ መገንዘብም ለብዙዎች አቀበት ሆኖባቸዋል። የቀውሶቹን ምንነትና አደገኛነታቸውን የተገነዘብን ጊዜ ግን፤ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ለማወቅ አይከብደንም።
ትልቁ ሃላፊነት የመንግስትና የገዢው ፓርቲ ነው - ሦስቱ የሰው መሰረታዊ ፍላጎቶችን (የነፃነት፣ የብልፅግናና የእኔነት ከብር ፍላጎቶችን) የሚያሰናክሉ የአፈና፣ የቁጥጥርና የውርደት ድርጊቶች እንዳይባባሱ መጠንቀቅ፤ ቀስ በቀስም እየቀነሱ እንዲሄዱ በትጋት መጣር ይገባቸዋል። ለራሳቸው ሕልውናም ይበጃል።
ዜጎች፣ ምሁራን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም ሃላፊነት አለባቸው። በቅድሚያ ግልፅ መፍትሄ በማበጀት እንጂ፤ በአንዳች ተዓምር መልካም ለውጥ እንደማይመጣ በመገንዘብ፤ ቀውሶችን ከማባባስ መቆጠብና መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በብሄር ብሄረሰብ ተወላጅነት ወይም በሃይማኖት ተከታይነት ምክንያት የሚወረስ የጋራ አእምሮና አካል የለም። እናም፣ በጅምላ “ትግሬ ተገለለ፤ አማራ ተሰደበ፤ ኦሮሞ ተፈናቀለ ... ምናምን” በማለት ጭፍንነትን ከማራገብ እንራቅ! ኢህአዴግን ለመቃወምና ለመተቸት እልፍ ትክክለኛ ምክንያቶች ይኖራሉ። ኢህአዴግን ለመቃወም ሲባል፣ አክራሪነትንና አሸባሪነትን ወይም ጎሰኝነትንና ብሔረተኝነትን መደገፍ ይቅርና በዝምታ ማለፍም ነውር እንዲሆን እናድርግ።
መንግስትና ገዢው ፓርቲ፤ እንዲሁም ዜጎችና ምሁራን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች የየራሳቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ከተሳናቸው፤ ወይም ፈቃደኛ ካልሆኑ፤ ይባስ ብለው በጭፍን የእልህ ስሜት የሚቀጥሉ ከሆነስ? አትጠራጠሩ፤ ያኔ በዘር የተቧደኑ የጎሰኝነት (የብሔረተኝነት) መዓተኞችና የሃይማኖት አክራሪ ሽብርተኞች እግር ስር እንወድቅና መመለሻ ወደሌለው የጥፋት ቀውስ እናመራለን።

Read 3962 times