Saturday, 23 December 2017 09:59

“ኑሮ እንዴት ነው!” ብሎ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

 “--ኑሮማ እግር ተወርች አስሮናል፡፡ እንደውም በእግረ ሙቅ ነው የጠፈረን፡፡ አይዟችሁ የሚል ነው ያጣነው፡፡ ባለስልጣኑ ሁሉ በመኪና አቧራ እየነዛብን ያልፋል እንጂ ዘወር ብሎ የጓዳችንን ጉድ የሚያይልን ነው ያጣነው፡፡ የምግቡ፣ የህክምናው፡ የምናምኑ ዋጋ ሰማየ ሰማያት ሲደርስ የሚከራከርልን ነው ያጣነው፡፡ እንዲህማ ሲቸገሩ ዝም ብለን አናይም የሚልልን ነው ያጣነው፡፡ ነገሮችን ስርአት የሚያሲዝልን ነው ያጣነው፡፡ እዛ ላይ የተቀመጠው ሁሉ በእኛ ስም አይደል እንዴ ወንበር የያዘው!--”
    
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ጠያቂ፡— ጤና ይስጥልኝ፡፡
ተጠያቂ፡— ጤና ይስጥልኝ፡
ጠያቂ፡— ስለ አንዳንድ ጉዳይ ላናግርዎት ፈልጌ ነበር፡፡
ተጠያቂ፡— ስለ ምንድነው የምታናግረኝ? ቆይ፣ አንተን ማን ልበል?
ጠያቂ፡— ጋዜጠኛ ነኝ…እየዞርን ሰዉን ስለ ኑሮ ሁኔታ እየጠየቅን ነው፡፡
ተጠያቂ፡— ምነው? የተፈጠረ የተለየ ነገር አለ እንዴ!
ጠያቂ፡— ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኑሮ ሁኔታ፣ ከህዝቡ አንደበት መስማት ፈልገን ነው፡፡
ተጠያቂ፡— መጀመሪያ ነገር…የት የበላነውንና የጠጣነውን ነው አንደበት የሚኖረን! (ሳቅ) አንተንም ወንድሜን እንዳላስቀይም፣ በል ጠይቀኝ፡፡
ጠያቂ፡— ስምዎን ማን ልበል?
ተጠያቂ፡— እሱን ተወውና ይልቅ ወደ ጥያቄህ…
ጠያቂ፡— እሺ…ለመሆኑ አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ተጠያቂ፡— እንዴት ይገለጹታል ብሎ ጥያቄ ምንድነው!
ጠያቂ፡— ማለት… በእርሶ እይታ፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው ኑሮ በምን ሁኔታ ይገለጻል?
ተጠያቂ፡— ጉድ እኮ ነው፣ እናንተ! ይገለጻል፣ አይገለጽም ብሎ አማርኛ ምንድንው! ይልቅ በቀን ስንት ጊዜ ትበላለህ ብለህ አትጠይቀኝም!
ጠያቂ፡— እሺ፣ የየቀኑ አመጋገብዎትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ተጠያቂ፡— እንዴት አይነት ጣጣ ነው!…እሺ፣ አኔ ከመመለሴ በፊት አንተን ልጠይቅህ፡፡ ሥራህ ምንድነው?
ጠያቂ፡— ሥራህ ምንድነው ማለት…
ተጠያቂ፡— ሥራህ ምንድነው ማለት ነዋ!
ጠያቂ፡— ጋዜጠኛ ነኝ ብዬዎት የለ እንዴ! ለእርስዎ ቃለ መጠይቅ እያደረግሁ አይደል…
ተጠያቂ፡— እሱን እንኳን ተወው!
ጠያቂ፡— አልገባኝም…
ተጠያቂ፡— አሁ እኔን እየጠየቅህ ሳይሆን እንጀራህን እያበሰልክ ነው…
ጠያቂ፡— መቼም በነጻ አልሠራም፡፡ በደሞዝ ተቀጥሬ ነው…
ተጠያቂ፡— ይህኛው ለደሞዝህ አይደለም…ደሞዙንማ ቢሮህ ቁጭ ብለህም ይሰጡሀል፡፡
ጠያቂ፡— በዚህ እንኳን አልስማማም፡፡
ተጠያቂ፡— ኑሮ አንዴት ነው ብለህ ስትጠይቀኝ፣ እንድመልስልህ የምትፈልገውን ልንገርህ…
ጠያቂ፡— የእርስዎን ሀሳብ ነው መስማት የምፈልገው..
ተጠያቂ፡— አስጨርሰኝ… እንድልልህ የምትፈልገው…“ኑሮማ እግዚአብሔር ይመስገን ሰላም ነው፡፡ በሁሉም በኩል እየተሻሻልን ነው። እድሜ ለፀሃዩ መንግሥታችን! ሁሉም ነገር በሽ ነው፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ የምንሄድበት ፍጥነት፣ ዓለምን እያስደነቀ ነው…እንዲህ እንድልልህ አይደል የምትፈልገው!
ጠያቂ፡— እኔ እንኳን እንደሱ እንዲሉልኝ ፈልጌ አይደለም፡፡
ተጠያቂ፡— ታዲያ ጋዜጠኛ ነኝ ካልክ፣ ኑሮን ራስህ እየዞርክ አታይም እንዴ! ሰዉ አፍ ስር ማይክሮፎን ከመደቀንህ በፊት አንተ ያያኸውን ለምን አትናገርም?
ጠያቂ፡— እንደሱ ሳይሆን ለህዝቡ አስተያየት ቅድሚያ መስጠት ስላለብን ነው፡፡
ተጠያቂ፡— (ሳቅ) እንዲህም ብሎ ቅድሚያ የለም…ቅድሚያውማ ወዴት፣ ወዴት እንደሆነ እናውቀዋለን፡፡
ጠያቂ፡— ሊሉት የፈለጉት አልገባኝም፡፡
ተጠያቂ፡— የሰው አስተያየት ሰበሰብን ትሉና ቢሯችሁ ስትሄዱ፣ ቆራርጣችሁ፣ ቆራርጣችሁ ሰው ያላለውን እንደምታስተላልፉ የማናውቅ መሰለህ!
ጠያቂ፡— ይሄ እንኳን አሉባልታ ነው፡፡
ተጠያቂ፡— እና… ምንም ነገር ሳንቆራርጥ እንዳለ ነው የምናስተላልፈው ነው የምትለኝ?
ጠያቂ፡— እሱም አንዳንድ ከዋናው ሀሳብ ጋር ግንኙነት የሌላቸው…ከፖሊሲ አንጻር…
ተጠያቂ፡— ጎሽ፣ መጣህልኝ፡፡ ከፖሊሲ አንጻር፣ ማለት እናንተ እንዲሆንላችሁ ከምትፈልጉት አንጻር አይደል!…አሁን ጥያቄህን “እንዴት ይገልጹታል፣ እንዴት ይዘጉታል” የምትላቸውን ነገሮች ተውና አሳጥረህ ጠይቀኝ፡፡
ጠያቂ፡— ኑሮ እንዴት ነው?
ተጠያቂ፡— ኑሮማ እግር ተወርች አስሮናል። እንደውም በእግረ ሙቅ ነው የጠፈረን፡፡ አይዟችሁ የሚል ነው ያጣነው፡፡ ባለስልጣኑ ሁሉ በመኪና አቧራ እየነዛብን ያልፋል እንጂ ዘወር ብሎ የጓዳችንን ጉድ የሚያይልን ነው ያጣነው። የምግቡ፣ የህክምናው፡ የምናምኑ ዋጋ ሰማየ ሰማያት ሲደርስ የሚከራከርልን ነው ያጣነው፡፡ እንዲህማ ሲቸገሩ ዝም ብለን አናይም የሚልልን ነው ያጣነው። ነገሮችን ስርአት የሚያሲዝልን ነው ያጣነው።  እዛ ላይ የተቀመጠው ሁሉ በእኛ ስም አይደል እንዴ ወንበር የያዘው!  ነጋዴ እንደፈለገው ዋጋ አየሰቀለ ሲያማርረን፣ ማን አይዟችሁ አለን! ዋናው ችግራችን የመልካም አስተዳደር ነው። ልድገምልህ፣ ዋናው ችግራችን የመልካም አስተዳደር ነው፡፡ እኛ የምንፈለገው ለሰልፍና ለስብሰባ ጊዜ ብቻ ነው እንዴ! መልካም አስተዳደር ጠምቶናል እያልኩህ ነው፡፡ እየቀዳኸው ነው?
ጠያቂ፡— አዎ፣ እየቀዳሁት ነው፡፡
ተጠያቂ፡— አሁን ደግሞ ዜናውን እንዴት እንደምታስተላልፈው ልንገርህ…
ጠያቂ፡— እርስዎ እንደነገሩኝ ነዋ…
ተጠያቂ፡— እሱን እንኳን ሞኝ አማት ካለችህ ለእሷ ንገራት፡፡ አንተ ደግሞ ዜናውን ስታስተላልፍ ምን ትላለህ መሰለህ…“አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ነጋዴዎች ህዝቡን እያማረሩት እንደሆነ ተናገሩ” ነው የምትለው፡፡
ጠያቂ፡— ራስዎ እንደዛ ብለዋል እኮ…
ተጠያቂ፡— ደጋግሜ ዋናው ችግራችን የመልካም አስተዳደር ነው አልኩህ እኮ! ዋናው ቀንዱ እያለ ወደ ጭራው ምን ያስኬዳል! አየህ… የእናንተ ነገር ቀንዱ ካልተስማማችሁ ወደ ጭራው ነው፡፡ ወይ አለቆችህ አዘውህ፣ ወይ በራስህ ተነሳሽነት ደሞዝ እንዲጨመሩልህ፣ እኔ የሰጠሁህን ሸጋ የሆነ ሸማ፣ አንተ ወደ ሰዉ ስታደርስ ቡቱቶ ታደርገዋለህ፡፡
ጠያቂ፡— እኔ እንኳን እንደሱ አይመስለኝም…
ተጠያቂ፡— ስማ… በኳስ ምሳሌ ልስጥህ፡፣ አንተ የየትኛው የእንግሊዝ ቡድን ደጋፊ ነህ?
ጠያቂ፡— የሊቨርፑል…
ተጠያቂ፡— እንበልና ስዋንሲ ሊቨርፑልን በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ፣ አምስት ለዜሮ ያሸንፈዋል፡ ምን ብለህ ታስተላልፋለህ?
ጠያቂ፡— ስዋንሲ ሊቨርፑልን አሸነፈ ብዬ ነዋ!
ተጠያቂ፡— እንደሱ አትልም፡፡ ምክንያቱም ለአንተ አይመችህም፡፡ ሊቨርፑል በስዋንሲ ተሸነፈ ትልና ሰማይ የወረደ ይመስል፣ የስዋንሲን የጨዋታ ብልጫ ሳይሆን የሊቨርፑልን የጨዋታ ድክመት ነው የምታወራው፡፡ …የኳስ ነገር ምን አመጣው በለኝ፡፡
ጠያቂ፡— እሺ፣ የኳስ ነገር ምን አመጣው?
ተጠያቂ፡— ምንም ነገር የምታስተላልፉት እናንተ በሚመቻችሁ ቃና ነው፡፡ በኑሮም ሆነ በሌላ ጉዳይም ዜና የምታስተላልፉት ጥቅማችሁን እንዲያስጠቀምላችሁ አድርጋችሁ ነው፡፡ በነገራችን ላይ…መረጃ አቅርቦት ላይ ጋዜጠኛ ገለልተኛ መሆን አለበት ትሉ የለ እንዴ!
ጠያቂ፡— ገለልተኛ የሚለው ነገር እንኳን አሻሚ ነው…
ተጠያቂ፡— (ጭብጨባ) ብራቮ!  ብራቮ!  አሻሚ ነው አልከኝ! አሁን መለስክልኝ፡፡ ወይ አሻሚ!
ጠያቂ፡— አሻሚ ማለቴ እኮ…
ተጠያቂ፡— ቆይ ልጠይቅህ፣ በሆነ ረብሻ አስር ሰው ከባድ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ በቃ እውነቱ ይህ ነው…እንዴት እንደምታስታላልፈው ልንገርህ፡፡
ጠያቂ፡— ያው ሰው መጎዳቱን ነዋ…
ተጠያቂ፡— ሰው መጎዳቱንማ ትገልጻለህ…ግን ቁጥር መጥራት፣ ጉዳቱ ከባድ መሆኑን መግለጽ ለአንተ ስለማይመችህ… “በተፈጠረው ረብሻ የተወሰኑ ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ” ነው የምትለው። አሁን፣ ላጠቃልልህ፡፡
ጠያቂ፡— አጠቃሉልኝ፡፡
ተጠያቂ፡— ሰሞኑን ግራ እያገባችሁን ያላችሁት፣ በዚህ አይነት አዘጋገባችሁ ነው፡፡ ያሻማል ነው ያልከኝ!
ጠያቂ፡— አንድ የመጨረሻ..
ተጠያቂ፡— እኔ የመጨረሻውን ልናገር… አንተ ቅር እንዳይልህ መጀመሪያ የጠየቅኸኝን ጥያቄ ልመልስልህ፡፡ ኑሮ እንዴት ነው አይደል ያልከኝ… “በሚያስደንቅ ፍጥነት ወደ መካከለኛ ገቢ መገስገሳችን በጣም አስደስቶኛል፡፡” አሁን ደስ አለህ! ደሞዝ ከተጨመርልህ ማኪያቶ ትጋብዘኛለህ። ጉድ እኮ ነው… ሁሉም ነገር እንዲህ ፍጥጥ ብሎ “ኑሮ እንዴት ነው!” ብሎ ነገር!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2444 times