Sunday, 24 December 2017 00:00

በኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ ላይ የተጠራው ውይይት በተቃውሞ ተቋረጠ

Written by 
Rate this item
(16 votes)

· “አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ እየተናጠች ውይይቱን መጥራት ሌላ ችግር መፍጠር ነው ”
            · “ውይይቱ እንዴት በዚህ ወቅት ተዘጋጀ? ምን ፈልጎ ተዘጋጀ?”

   የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ትላንት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተጠራው የውይይት መድረክ፣ በተቃውሞና ባለመግባባት ተቋረጠ፡፡ ውይይቱን ያዘጋጁት የፓርላማው የህግና ፍትህ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴና የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ቋሚ ኮሚቴዎች ሲሆኑ ከመድረክ የተሰየሙት የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎች ወደ ውይይት ሊገቡ ሲሉ፣ “የአካሄድ ጥያቄ” ከተሰብሳቢዎች ተነስቶባቸዋል፡፡
ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ የሆኑት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሚደረገውን ውይይት እንደሚደግፉ፣ ነገር ግን አሁን ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ፣ ይህን ውይይት በተረጋጋ መንገድ ማካሄድ የማያስችል መሆኑን ለመድረኩ ሰብሳቢዎች ተናግረዋል፡፡
አቶ አዲሱ አክለውም፤ ከ600 ሺህ በላይ ህዝብ በግጭት ተፈናቅሎ እርዳታ ጠባቂ በሆነበት፣ ህዝቡ በፀጥታ ችግር ውስጥ ባለበት … ወቅት ውይይቱን በተረጋጋ ሁኔታ ማካሄድ አይቻልም ብለዋል፡፡ ይህ ውይይት መጀመር የነበረበት በህዝቡ እንደሆነም አስታውቀው፣ በዚህ ሁኔታ ውይይቱን ማካሄድ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
ሌላው የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣን በበኩላቸው፤ የአቶ አዲሱን ሃሳብ በማጠናከር፣ ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ውይይቱን ለማካሄድ የሚፈቅድ አይደለም ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በመጀመሪያ ህዝብ እንዲወያይበት ሊደረግ እንደሚገባ በመጥቀስም፣ ህዝብ በየደረጃው ሳይወያይ የሚደረግ ውይይት የይስሙላ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡
በአዳራሹ የተገኙት በአብዛኛው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ውይይቱ ቢካሄድ እንኳ የህዝብ ውይይት ተደርጓል ማለት አይቻልም ብለዋል ባለስልጣኑ፡፡
“በሁለት ቀን የሚዲያ ጥሪ ብቻና ጥቂቶች በተገኙበት ሁኔታ ውይይት ማካሄድ አስቸጋሪ ነው፤ ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን ከግምት አስገብቶ፣ ውይይቱ ከህዝብ ይጀመር” ብለዋል - እኚሁ ባለስልጣን፡፡
የተለያዩ ግጭቶች በየቦታው እየተከሰቱ ባለበት ውይይት ቢካሄድ ውጤታማ መሆን አይቻልም ያሉት እኚሁ ባለስልጣን፤ ከህዝቡ በተጨማሪም በቅድምያ ምሁራን፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች … በጉዳዩ ላይ በስፋት ሊወያዩበት ይገባል እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ተወያይተው ብቻ የህዝብ ውይይት ተደርጓል ማለት፣ የህጉን የወደፊት ተፈፃሚነትም ችግር ውስጥ ይከተዋል ብለዋል፡፡
ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ ወደ አዳራሹ የገቡት አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ አዋጁ ውይይት ሊደረግበት ከታቀደበት ጊዜ መዘግየቱን በመጠቆም፣ ሰፊ የህዝብ ውይይት እንደሚያስፈልገው፤ ነገር ግን ውይይቱ ከየትኛውም አካል ሊጀመር እንደሚችል ገልፀው፣ ውይይቱ መጀመር አለበት ብለዋል፡፡
ተሰብሳቢዎች አቶ አባዱላ ይህን ሲሉ ያጉረመረሙ ሲሆን በመቀጠል የመድረክ መሪው “አቶ አባዱላ ያቀረቡት ማብራሪያ የሚያግባባን ይመስለኛል” በማለታቸው ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
በአካሄዱ ላይም ተጨማሪ ሃሳብ ለመቀበል ተገድደዋል፡፡
በቀጣይ የተናገሩት ተሰብሳቢ በበኩላቸው፤ የአቶ አባዱላን ሀሳብ በመደገፍ፣ ውይይቲ መካሄድ እንዳለበትና በረቂቅ አዋጁ ላይም ተደጋጋሚ ውይይት ሊካሄድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የመድረኩ መሪ “የጠራናችሁ የቋሚ ኮሚቴውን ስራ እንድትደግፉ ነው፤ ቋሚ ኮሚቴው ስራውን እንዳይሰራ ልትወስኑብን አትችሉም፣ ውይይታችን መቀጠል በሚያስችል መልኩ እየተግባባን መሄድ አለብን” የሚል ማሳሰቢያ ቢሰጡም ማጉረምረሙ በመቀጠሉ ስብሰባው ለሻይ እረፍት በሚል ተበትኗል፡፡
መድረኩ ለሻይ እረፍት ሲበተን ግን ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተወካዮች በስብሰባው አዳራሽ እንዲቀሩ ተደርገው፣ አቶ አባዱላ “በውይይቱ እንዲቀጥሉ” ለ20 ደቂቃ ያህል ሲያግቧቧቸው ቆይተዋል፡፡
“አንወያይም ማለት በህዝቡ ዘንድ ሌላ ትርጉም ነው የሚሰጠው፣ እንደ ኦሮሚያ የመንግስት አመራሮች እንዲህ ያለ አቋም መያዝ አይገባንም፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መሄድ አለብን” በማለት ለተወካዮቹ አስረድተዋል - አቶ አባዱላ፡፡
ተወካዮቹ በበኩላቸው፤ “እኛ የህዝብ ውይይት ይቅደም ነው ያልነው ብለዋል፡፡ ሌሎች ተሳታፊዎች ደግሞ “ይህ መድረክ በዚህን ወቅት ለምን እንዲዘጋጅ ተፈለገ? እንዴትስ ተዘጋጀ?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
አቶ አባዱላ በመጨረሻም፤ “መድረኩ አይካሄድም ካላችሁ፣ ያለው አማራጭ ይህን መድረክ በትኖ መተው ነው” በማለት አዳራሹን ለቀው ወጥተዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ ከሻይ እረፍት ከተመለሱ በኋላ የመድረክ መሪዎቹ መድረኩ ከህዝብ ውይይት ቀድሞ የተጠራበትን መንገድ ከመተዳደሪያ ደንብ አንፃር አብራርተው፤ የህዝብ ውይይት እንደሚያስፈልግ የገለፁ ሲሆን ቀኑ አርብ መሆኑንና ሰዓቱም በአካሄድ ውይይት መገባደዱን በመጠቆም፣ የውይይት መድረኩ በሌላ ጊዜ እንዲካሄድ ወስነው ስብሰባው ተበትኗል፡፡
ትላንት ባለመግባባት የተበተነውን ውይይት በተመለከተ አስተያየት የጠየቅናቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ሃገሪቱ በተለያዩ ፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ይህን ጉዳይ አንስቶ በመወያየት በችግር ላይ ችግር መፍጠር አያስፈልግም፤ አጀንዳው በምንም መልኩ አሁን ለውይይት መቅረብ የለበትም” ብለዋል፡፡
ፓርቲያቸው ልዩ ጥቅም ተብሎ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቃወምም አስታውቀዋል - አቶ ሙላቱ፡፡
“አዲስ አበባን በኦሮሚያ ክልል ስር አድርጎ፣ ራሱን የቻለ ከተማ እንዲሆን እንጂ ልዩ ጥቅም በማለት ለትውልድ አጨቃጫቂ ነቀርሳ መትከል አያስፈልግም” ሲሉም አቶ ሙላቱ የፓርቲያቸውን አቋም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 10136 times