Print this page
Saturday, 23 December 2017 09:34

አበበ ቢቂላና መዝገቡ ከአዳም ረታ ግራጫ ቃጭሎች (ልዩ መገንዘገብ)

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ይህ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ በየጊዜው የሚቀርበው፤ “ታላላቅ ስፖርተኞችን አስደናቂ ብቃታቸውንና የህይወት ዘመን ታሪካቸውን ባስታወስን ቁጥር ለዛሬም ለወደፊትም የመንፈስ ብርታት ይሆነናል” በሚል ነው፡፡

            አበበ ቢቂላና መዝገቡ
             ከአዳም ረታ ግራጫ ቃጭሎች (ልዩ መገንዘገብ)

   እድሜው አስራ አምስት የማይሞላ ልጅ ቅርብ ካሉት ሰዎች የበለጠ የሚያውቃቸው ብዙ ሰዎች አይኖሩም:: የሉም:: ቢኖሩም እንደው ጥቂት ቢሆኑ ነው:: በአይን የማውቃቸውና በትኩረቴ ታክኬያቸው የማልፋቸው ብዙ ነበሩ:: “በጣም” ከሚቀርቡኝ ጥቂት ሰዎች አንደኛዋ እንጀራ እህቴ ነበረች:: ቀድሞ እወዳት ነበር:: ሙስጠፋን ያደረገችውን ነገር ሳይና ስሰማ ግን አስከፋችኝ::
***
ማንን ልውደድ ታዲያ?
ሙስጠፋን አደንቅው ነበር:: የእንቁላል ፍርፍር ጋብዞኝ ደብዳቤውን ለእህቴ ሰጥቶ መልሱን እስካመጣለት ድረስ አደንቅው ነበር:: ምናልባትም እወደውም ነበር:: የሚያለቅስ ሰው እጠላለሁ:: የሚያለቅስ ወንድ ያስጠላኛል:: ውሀ ከሰማይ ወይ ከወንዝ ከምንጭ እንጂ ከአይን መውጣት የለበትም:: ለሙስጠፋ ያለኝ አክብሮት ሲያለቅስ ካየሁት ጀምሮ ጠፋ:: አራዳ እንደሆነ ይገባኛል:: የዚያን ለት ምን እንደነካው ግን አላውቅም:: እህቴ ደ’ሞ እንዲህ ሰው የሚያብድላት አይመስለኝም::
ታዲያ ምንን ነበር የምወደው? ብዙ ሰው ሊገርመው ይችላል:: እኔ የምወደውና የማደንቅው ሰው አበበ ቢቂላ ነበር:: ለምሳሌ አባቴ ጸጉር አስተካካይ ነበር:: እኔ ሳውቀው ጀምሮ ጸጉር ያስተካክላል:: አባቴ ለፍቶ አዳሪ ቢሆንም- በዚህ ቢደነቅም- ለዘመናት ቆርጦ የሚያውቃቸው ያቆራረጥ ጥበቦች ሁለት ዐይነት ነበሩ:: “ሙልጭ” የሚባለውና “ስፖርት” የሚባለው:: ብዙሌሎች የሰፈሬ አባቶችን ይመስላል (ሌሎች ሌላው ቢቀር ሰላልወለዱኝ አይደበድቡኝም እንጂ)
***
ልጅም አልነበርኩ፤ የእንግዴ ልጅም አልነበርኩ:: በቃ በሾርኒ የምታይ ዞፍ:: እንደሰማሁትና እንዳነበብኩት አበበ ቢቂላ ትንሽ መንደር ውስጥ እረኛና ገበሬ ሆኖ ያደገ ነበር:: ክብር ዘበኛ ሆኖ ሲኖር ጥሩ መሮጥ በመቻሉ ተመርጦ ወደ አለም ተላከ:: ወደ አፍሪካም አይደለም:: ወደ አለም ተላከ:: አሸነፈ:: አንድ ግዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ግዜ አሸነፈ::
ከስፖርቶች ሁሉ የማራቶን ሩጫ የሚያስገርም ነው:: ቀላል ተራ ነገር መስሎ ከባድ ነው:: የማራቶን ርቀት ከ40 ኪ.ሜ ይረዝማል ይባላል:: ይህን ለመሮጥና አለምን ለማሸነፍ እንግዲህ አንድ ሰው ታላቅ መሆን አለበት:: ብችልም ባልችልም እንደ አበበ ቢቂላ መሆን እመኛለሁ:: እንዳባቴ ጸጉር ማስተካከል ቀላል ይመስለኛል:: ....እንዲህ ማስተካከል ይከብዳል?
እግዜር ሁለት እጆቹን ወስዶ በመለኮታዊ ጥበቡ (ጥንቸልና እንጀራ እህቴን የፈጠረ አይደል?) ደባልቆ ቢጠፈጥፋቸው አንድ ከግማሽ የሚሆን አበበ ቢቂላ አይወጣቸውም ነበር?
አበበ ቢቂላ ያደረገውን ግን ማንም በአለም ላይ አላደረገውም:: አንድ ግዜ ቢሆን አጋጣሚ ነው ወይም እድል ነው ይባላል:: ... ሁለት ግዜ ነው:: ደስ አይልም?
የምወደው ሰው አበበ ቢቂላን ነበር:: አበበ ቢቂላን በጣም እወደው አደንቀው ነበር:: እኔ ስሜ መዝገቡ ነው:: እና ልጅ ብወልድ አበበ ቢቂላ መዝገቡ እለዋለሁ ብዬ እል ነበር:: ቢከለከል እንኳን እለዋለሁ እል ነበር::
75-76 (የማደንቀው ሰው)
አባቴ አንድ የጃንሆይ ፎቶ ነበረው:: ቤታችን የሚገባ ሰው መጀመሪያ የሚያጋጥመው ስዕል አባቴ እእን አቅፎ የግቢውን የአጋምና የቀጨሞ አጥር ከጀርባው አድርጎ የተነሳው ፎቶግራፍ ሳይሆን የጃንሆይ ጥቁርና ነጭ ጉርድ ፎቶግራፍ ነበር:: የአባቴና የእንጀራ እናቴ ፎቶግራፍ በስተግራ ሞሰበ ወርቅ ተደግፎ ተቀምጧል - ምሳ ወይም እራት ተጋብዞ የሚበላውን ወይም ቡና የሚጠጣውን ጥቁር እንግዳ በአራት ዐይኖቻቸው እንደ ሠላይ ይዘውት::
እኔስ?
እኔ ፎቶግራፍ ሳይሆን የነበረኝ ስም ነው:: “እሱ” የተባለ ...ያውም ስም ያልሞላ:: ይሄም መርቀቅ ሲሆን... “ያ ወመኔ”:: ከምላሳቸው የበለጠ ካሜራ መች ነበራቸውና? እንዳንዴ እኔን መስደቢያ ቃላቶቻቸውን ከራዲዮ የሚቀዱ ይመስለኝ ነበር::
***
መማሪያ ክፍላችን ውስጥ ከእኔ መቀመጫ በስተቀኝ መገርሳ የሚባል ልጅ ነበር:: ስፖርት ይወዳል:: ....የሰበሰባቸው ፎቶግራፎች ደብተር መያዣ ኮሮጆውን ሞልተውታል:: ታዲያ አንድ ዕለት ፎቶ የሚለጥፍበትን ደብተር አውጥቶ ለልጆች ሲያሳይ አንድ አስተማሪያችን ለጉዳይ ጠርተውት ወደ ውጭ ወጣ:: እኔ የምሰራው ስላልነበረኝ ደብተሩን ወደ ዴስኬ ወስጄ ሳገላብጥ ትልቅ ከጋዜጣ የተቀደደ የአበበ ቢቂላን ፎቶግራፍ አገኘሁ:: ደነገጥሁ:: ወርቅ እንዳገኘ ገብጋባ ደነገጥሁ:: እጆቼ ተንቀጠቀጡ:: ለመስረቅ እንደፈለኩ ገባኝ::...
የሰረቅኳዋትን ፎቶግራፍ የክፍሌ የትኛው ግድግዳ ላይ እንደምለጥፋት እያሰላሰልኩ ነበር:: የትም ግድግዳ ላይ ይሁን የትም ግድግዳ ላይ ለዐይኖቼ ቅርብ የሆነ ቦታ ...
ስዕሉ ላይ አበበ ቢቂላ ብቻውን ነው:: የካናቴራው ቁጥር አስራ አንድ ነበር:: ከቅርብ ዕርቀት 185 ቁጥር የለበሰ ፈረንጅ ይከተለዋል:: በባዶ እግሩ ነበር:: አቤ የእኔ እናት በባዶ እግሩ ነበር:: አፉን ከፈት አድርጎአል:: የሚያስብ ይመስላል:: ሐይማኖተኛ ይመስለኛል:: የምንኩስና ልብሱን አውልቀው ለሩጫ የላኩት አበምኔት ይመስላል:: ፊቱ ሠላም በሠላም የሞላ:: የትኛው ሩዋጭ ነው ፊቱ እንዲህ ሠላም የሰፈነበት? የተባረከ ካልሆነ:: ከፎቶው ስር “አቤ በሮም ሲመራ” የሚል ተጸፏል::
እቁነጠነጣለሁ:: ገላዬን ሁሉ በላኝ:: በጸጥታ የተቀመጡት የልብሴ ጉድፎች በላቤ ተቀስቅሰው ከካልሲዬ እስከ ሸሚዜ ክሳድ ድረስ የሚጣፍጥ እከክ ነገር በላኝ:: ትምህርት አልቆ ስንበታተን እጄን ኪሴ ከትቼ ደብተሬን አጣጥፌ ጉያዬ ሸጉጬ ወደ መሀል ከተማ በቀስታ የምራመደው ሰው በሩጫ ወደ ቤቴ.... መኝታ ክፍሌ ገብቼ የአበበን ፎቶ በስንደዶ በስቼ የጭቃ ግድግዳዬን ጎርጉሬ ስሰቅላት በሕይወቴ ትልቅ ለውጥ የመጣ መሰለኝ:: ደስ አለኝ:: በጣም ደስ አለኝ:: ደሞ ወረቀቷን ከታች በኩል ከግድግዳ ጋር ሰላላስያዝኳት በመስኮት የሚገባ ንፋስ በቀስታ እያርገበገባት አበበ ቢቂላን ክፍሌ ውስጥ የሚሮጥ ታስመስለዋለች:: እግሮቹ ቀጫጭን ናቸው:: ያሳዝናሉ:: ምናልባት እንደ እኔ በእንጀራ እናት አድጎ ይሆናል:: የባላገር እንጀራ እናት ልጅዋን ብዙ ብዙ ነገር ታስለፋውና አልደክምላት ሲል በሬ ታሸክመው ይሆናል::
አቤ ግን እንጀራ እናቱንና ዓለምን በሩጫ አሸነፋቸው::
92-93 (የአበበ ቢቂላ ፎቶ )
***
አበበ ስሙ ደስ ይለኝ ነበር:: ረጅም ትከሻው ሰፊ የሆነ ልጅ ነበር:: አፉም ሰፊ ነበር:: ሲስቅ ሌላ ወረዳ ይሰማል:፡ ትምህርት ቤት ውስጥ እሱን የማያውቀው ተማሪ፣ የማያውቀው አስተማሪ አልነበም:: የማይላፋው ተማሪ የለም:: የማያዘው አስተማሪ የለም:: የማይወደው የለም:: እኔ ሌላውን ባላውቅም በስሙ ቀናለሁ:: ስሙ ለሱ መሰጠቱ ግን ያበሽቀኛል:: ብዙ ግዜ ስፖርት ሜዳ የማየው ከሴቶች ጋር ቮሊቦል ሲጫወት ነበር:: ጸሀይን ከመሰሉ የሚንጫጩ፣ የሚበላቀጡ፣ ነጭናጫ፣ ወሬኛ፣ ጮሌ ከሚባሉ ሴቶች ጋር ብዙ ግዜ ቮሊቮል ሲጫወት አየዋለሁ:: ስም ያበላሻል:: ሲሮጥ ግን አይቼው አላውቅም:: ስም ያበላሻል:: አበበ የሚባል ስም ቢኖረኝ በየቀኑ አራት ሰዓት እሮጥ ነበር:: በየቀኑ ላቤ ጠፍ ብሎ እስኪያልቅ እሮጣለሁ:: እግሮቼን ደክሞኝ እስክወድቅ እሮጣለሁ:: እሱ የሚያደርገው ግን ምንድነው?... ከሴቶች ጋር ቮሊቮል መጫወት:: ታዲያ ሴቶች እያቆላመጡ ይጠሩታል:: እበሽቃለሁ:: እያቆላመጡ ይጠሩታል:: አቤ፣ አቢቲ፣ አባዬ፣ አቡ፣ አብ፣ አቢነት፣ አብሽ ሌሎች ብዙ አፈጣጠራቸው የሚያስደንቅ ስሞች:: እበሽቃለሁ:: አበበ ቢቂላን ግን ምናልባት አንዳንዴ “አቤ” ብንለው ነው:: ከሴቶች ጋር ቮሊቮል ስለተጫወተ፣ ጥሩ ልጅ ሰለተባለ ዝነኛ አደርጎ በስምንት በአሥር ሥም ማሞካሸት ከብትነት መሰለኝ::
እኔ ቮሊቮል አልጫወትም ነበር... እንደ ሴት? ማየት አይ ነበር:: ማየት ምንም አይደለም:: ታዲያ እህቴን አንድ ቀን ከአበበ ጋር አየሁዋት:: አብረው ጎን ለጎን ቢሄዱ ጥር:: ግን ያን የማይረባ ቮሊቮል የተጫወተበት እጁን ቂጥዋ ላይ ሲያስቀምጥ አየሁት:: ቂጥዋ ላይ ቢያስቀምጥ ምንም አይደለም እንበል፣ ግን ጣቶቹን በቀስታ ያነቃንቃቸዋል:: እጁን አስቀምጦ ጣቶቹን ቢያነቃንቅ ምንም አይደለም እንበል ግን እህቴ ደስ በሎአት በዳሌዋ ነካ፣ ነካ አድርጋው እየተሽኮረመመች በሳቅ ፍርስ አለች:: ምን ያስቃል? አንድ ሴት እጅዋን ቂጤ ላይ ብታስቀምጥ ተሽኮርምሜ በሳቅ እፈርሳለሁ እንዴ? ወላ ዐይንዋን ነበር የማጠፋው:: አበበ ጀጋው የእህቴን ቂጥ እዚያ ሲነካ ወላ እኔ ራቅ ብዬ እያየሁ እበግናለሁ:: ደ’ሞ ደስ ይላታል:: ደ’ሞ እሱ በሰው ስም ይነግዳል:: አበበ ቢቂላ የቢቂላ ልጅ ሯጭ እንጂ ሸፋዳ አይደለም:: ይሄኛው አበበ የሚሰራው ትልቅ ነገር የኩዋስ ከነመዳሪ ማስተንፈስ ነበር:: ለአስተማሪዎች ቾክ ማምጣት ነበር:: ለዳይሬክተሩ ገበያ መላክ ነበር:: ግን በእህቴ ቂጥ ምን አገባኝ::
ቂጧ መአት ነበር:: ቢነካትም የሚሰማት አይመስለኝም:: ቢሰማት እንኩዋን ዓርብ ነክቷት እንደሆነ ከሁለት ቀኖች በሁዋላ እሁድ ይሆናል:: ከሻማ ጨርቅ የተሰራው የውስጥ ልብስዋ እንኳን መኩዋኩዋቱ አያሳፍራትም:: ምን አገባኝ:: ግን አበበ በሰው ስም ይነግዳል...
ወዳጄ ዘመዴ አጋሬ ወገኔ አበበ ቢቂላ ቢሞት ይሄኛው አበበ በሕይወት ቆሞ የሚያደርገው ነገር ቢኖር በስብ ያበጠ የገብስ እንጀራ በላተኛ ሴቶችን ቂጥ በመጋፊያ እጁ ጨበጥ ለቀቅ ማድረግ ነበር::
101-102 (እህቴና የአበበ እጅ)
***
...በቅርብ ተለውጧል:: አባቴ በቅርብ ተለውጧል:: በራዲዮ የሚሰማው ነገር ልዩ ደስታ የሚሰጠው ይመስለኛል:: ንጉሠ ነገሥቱን እወዳለሁ ሲል የነበረው ሰውዬ ፎቶአቸውን አውርዶ ጓዳ አስቀምጦታል:: ማለቴ የእኔ የአበበ ቢቂላ ፎቶ እስከ ዘላለም የምትሰቀል ናት:: ይመስለኛል::
አበበን ቢሞትም አልረሳውም:: አበበ በሕይወት ቢኖርና አበበ አባቴ ቢሆን የጸጉሬን እርዝመት አይለካውም:: አንዳንዴ ፎቶውም አይቼ፣ፊቱንና አሯሯጡን አይቼ መሞቱ ትዝ ሲለኝ አለቅሳለ ሁ:: የእውነት አለቅሳለሁ:: አባቴ ታዲያ ጸጉሬን እየጎተተ ይለካል:: ጸጉር ትልቅ ቁም ነገር ነው? ኃይለሥላሴ አፍሮ ይቆረጡ የለ ለምን አይጠላቸውም ነበር? ልቡ ግልጥ አልነበረምና የሚወዳቸውን ኃይለሥላሴን እንኳን አልጋ ሥር ደብቋል:: ደሞ “ደርጉ” የሚባል ነገር ስለመጣ ካለሱ የሚያወራው የለም:: ይሄ ደርጉ ምን ዐይነት ነገር እንደሆነ አይገባኝም:: ባይገባኝም ግድ የለኝም:: የማውቀው ነገር ግን ስለማራቶን አለመሆኑን ነበር:: ስለአበበ ቢቂላ ስለማሞ ወልዴ አለመሆኑ ነው:: ሶሻሊዝም እንግሊዘኛ ነው:: የአማርኛው አይያዝልኝም ነበር:: ት/ቤቱ ውስጥ ሁልግዜ የሚወራው ደርጉ ደርጉ ሶሻሊዝም ሶሻሊዝም ነበር:: እንዳሰለቸኝ::
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ገጠር ትዘምታላችሁ ተብለው ያቁነጠንጣቸው ነበር:: እኔ ወላ የትም መሄድ አልፈልግም:: በሕይወት ቢኖር ኖሮና ብችል የአበበ ቢቂላ ጎረቤት ሆኜ ጠዋት ጠዋት ለሩጫ ልምምድ ሲወጣ ባየው እመኛለሁ:: ሩዋጮች አምቦ ውሀ ነው አሉ የሚጠጡት:: ለአበበ ቢቂላ በጀርባዬ ሳጥን ሙሉ ተሸክሜ አመጣለት ነበር::
103 (የዱባለ ጃኬት)

Read 5590 times