Saturday, 23 December 2017 09:33

ዋና አመራሮቹ በእስር ላይ የሚገኙት ኦፌኮ ዛሬ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ ይወያያል ተብሏል

    የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ምክትሉ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 13 ያህል ከፍተኛ አመራሮቹ በእስር ላይ የሚገኙበት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዛሬና ነገ ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ የተገለፀ ሲሆን በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረቶችና የፀጥታ ችግሮች ላይም እንደሚወያይ ተጠቁሟል፡፡
ፓርቲው ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ ጉባኤው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በመወሰኑ አሁን በስራ ላይ ባሉ አመራሮችና ሌሎች አባላት ይካሄዳል ብሏል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በዋናነት በኦሮሚያና በሀገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ችግሮችና ፖለቲካዊ ውጥረቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ፓርቲው አስታውቋል፡፡
“የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በአፅንኦትና በጥልቀት ይገመገማሉ” ያለው የፓርቲው፤ መግለጫ “ ጉባኤው በቀጣይ ለሚከናወኑ ፖለቲካዊ ተግባራት አዳዲስ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል” ብሏል፡፡
ፓርቲው አዲስ የመተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም ማዘጋጀቱንና በጉባኤው ላይ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው መግለጫው፤ አዳዲስ አመራሮች ይመረጡ አይመረጡ የሚለው በጉባኤው እንደሚወሰን አስታውቋል፡፡
በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ይመራ የነበረው የኦሮሞ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) እና በእስር ላይ በሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና ይመራ የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ) ተዋህደው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስን (ኦፌኮ) መመሥረታቸው ይታወሳል፡፡
ኦፌኮ ከተመሰረተ በኋላ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 14 እና ነገ የሚካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡ 

Read 4130 times