Saturday, 23 December 2017 09:21

በኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሉንም ወገኖች ያሣተፈ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ጉዳቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ህብረቱ ጠይቋል

   በሃገሪቱ ለሚታዩ ግጭቶች መፍትሄ ለማግኘት ሁሉንም ሃይሎች አሣታፊ ያደረገ የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ያሣሠበው የአውሮፓ ህብረት፤ በግጭቶች የሚደርሡ ጉዳቶች በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩ ለመንግስት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መግለጫ ያወጣው የአውሮፓ ህብረት፤ በሃገሪቱ የተፈጠረው ግጭትና ቀውስ አሣሣቢ መሆኑን አስታውቆ የፀጥታ ሃይሎች በሃላፊነት ስሜት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል፡፡
ህብረቱ በዩኒቨርሲቲዎች እና በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የብሄር ተኮር ግጭቶች እየጨመሩ መምጣታቸው አሳሳቢ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
እነዚህን ለሃገሪቱ አሣሣቢ የሆኑ ግጭቶች ለመፍታት በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የግጭት አፈታት ዘዴዎችንና ድንጋጌዎችን በአፋጣኝ በመተግበር ሁሉንም የፖለቲካ ተቀናቃኝ ሃይሎች ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች ከሁሉም ዜጎች ጎን በመቆም የሚደርሡ ጉዳዮች እንዲቀንሡ መጣር አለባቸው ብሏል-ህብረቱ፡፡
በቅርቡ በግጭቶች ህይወታቸውን ላጡትም የተሠማውን ጥልቅ ሃዘን ህብረቱ በመግለጫው አስፍሯል፡፡
መፍትሄ ሣያገኝ ለአንድ አመት በዘለቀው የሶማሌ ኦሮሚያ ክልል አዋሣኝ ግጭት ከሠሞኑ አንድ ሣምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 78 ንፁሃን ዜጎች በአሠቃቂ ሁኔታ መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ ከነበረው ብሄር ተኮር ግጭት ጋር ተያይዞም የ4 ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ በደረሠው ጉዳት የተሠማውን ሃዘን ገልፆ፣ አጥፊዎችን ለህግ አቀርባለሁ ብሏል፡፡

Read 4328 times