Monday, 18 December 2017 13:57

የፌደሬሽኑ አመራሮች ምርጫ በድጋሚ ሊራዘም ነው

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• ለፕሬዝዳንትነት 5 እጩዎች፤ ለስራ አስፈፃሚነት 16 እጩዎች ቀርበዋል
• በስፖርቱ አመራር ላይ የሰፈነው አለመተማመን ጫና ቢፈጥርብንም፤ ስራችንን በአግባቡ እየሰራን ነው- የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ
• የቀድሞዎቹ ስራ አስፈፃሚዎች አቶ ልዑልሰገድ በጋሻውና ኢንጅነር ቾል ቤል ተወዳዳሪነታቸው ያልፀደቀላቸው እጩዎች ናቸው        


     ታህሳስ 16 ላይ በሰመራ ከተማ አፋር ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት እና የሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ በድጋሚ ሊራዘም ነው፡፡ ምርጫው ተገቢውን ህግና ደንብን ተከትሎ እንዲካሄድ በፊፋ ሃላፊነት የተሰጠው የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ በትናንትናው እለት በሰጠው  መግለጫ እንዳመለከተው ምርጫው በድጋሚ እንዲራዘም የተወሰነው አስቀድሞ ይካሄዳል የተባለበት ቀን ከፈረንጆች እና ከኢትዮጵያ የገና በዓል አከባበር የሚጋጭ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኮንን  በሰመራ የሚካሄደው ጉባዔ ታህሳስ 16 ላይ እንደማይካሄድ  ማረጋገጫ ሰጥተው ኮሚቴው በተቀያሪው ቀን ላይ ተወያይቶ በመወሰን ያስታውቃል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያካሂደውን የአመራሮች ምርጫ ያራዘመው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን   አስቀድሞ ጥቅምት 30 ሊካሄድ በነበረበት ወቅት ፌዴሬሽኑ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎቹን አላሟላም በማለት የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን (ፊፋ) እንዲራዘም ሲያደርግ ለፌደሬሽኑ ፅፎት በነበረው ደብዳቤ የምርጫው ሂደት ከፊፋ የመልካም አስተዳደር ህግጋት ጋር እንደማይጣጣም፤  ሂደቱ የተወዳዳሪዎች ተገቢነትን ለማጣራት በቂ ጊዜ አለመስጠቱን መጥቀሱ የሚታወስ ነው፡፡
ህዳር 14 ላይ የተቋቋመው የምርጫ አስመራጭ ኮሚቴው ባለፉት 3 ሳምንታት ስላከናወናቸው የቆያቸውን ዝርዝር ስራዎች አስመልክቶ በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል በትናንትናው ዕለት መግለጫ ሲሰጥ፤ ከሚዲያ አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች ዋንኛው ሃላፊነታችሁን በግልፅነት፤ ያለመከፋፈል እየሰራችሁ ነው ወይ የሚል ቢሆንም የኮሚቴው አባላት የስፖርቱ አመራር ላይ የሰፈነው አለመተማመን ጫና ቢፈጥርብንም ስራችንን በአግባቡ እየሰራን ነው በሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን መኮንን ባቀረቡት ሪፖርት በምርጫው ሂደት ከደንብና መመርያ አኳያ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ሁሉም የኮሚቴው አባላት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ፤ የፊፋ እና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር በጥልቀት እንዲያጠኑ መደረጉን፤ እጩ ተወዳዳሪዎችን ድምፅ የሚሰጡ የጉባኤው አባላት እንዲያቀርቡመጋበዙን፤ ከዚያም በኋላ የእጩዎች  ተገቢነት ማረጋገጣቸውን፤ የሚነሱ ቅሬታዎችን ማስተናገዳቸውን፤ ለሚመለከታቸው አካላት ፀድቆላቸው መወዳደደር  ስለሚችሉ እጩዎች  ማስታወቃቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የምርጫውን ሂደት ቴክኒካል ስራዎች እና ቁሳቁሶች በማዘጋጀት ኮሚቴው መስራቱንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለፕሬዝዳንትነት የቀረቡ 5 እጩዎችና ለስራ አስፈፃሚነት የሚወዳደሩ 16 እጩዎችን ያፀደቀው ኅዳር 25 ላይ ባደረገው ስብሰባ ነበር፡፡  በምርጫ አስፈፃሚው ትናንት በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው ክልሎች በላኳቸው ደብዳቤዎች መሰረት አንዳንድ እጩ ተወዳዳሪዎች ከውድድር ውጭ የተደረጉ ሲሆን ተተኪ እጩዎችን የመለየት ተግባራት ተከናውነው የፀደቁት በሙሉ ድምፅ ነው፡፡ ለፕሬዝዳንትነት የቀረቡ 5 እጩዎችና ለስራ አስፈፃሚነት የሚወዳደሩ 16 እጩዎች ሙሉ ስም ዝርዝራቸውም ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው።


            ለፕሬዝዳንትነት የቀረቡ እጩዎች

ተ.ቁ ስም የተወከሉበት ክልል/ከተማ መስተዳደር
1 አቶ ጁነዲን ባሻ ቲሊሞ ከድሬድዋ ከተማ መስተዳደር እ.ፌ
2 አቶ ተካ አስፋው ተሰማ ከአማራ ብ/ክ/መንግስት እ.ፌ
3 አቶ ኢሳያስ ጂራ ቦሾ ከኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት እ.ፌ
4 ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ጋዮ ከደቡብ ብ/ብ/ህ/ክ መንግስት እ.ፌ
5 አቶ ዳግሞ መላሼን ዋኞክ ከጋምቤላ ብ/ክ/መንግሰት እ.ፌ
ለስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴ አባልነት የቀረቡ እጩዎች
ተ.ቁ ስም የተወከሉበት ክልል/ከተማ መስተዳደር
1 አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ አርጋው ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እ.ፌ
2 አቶ ሰውነት ቢሻው ውቤ ከአማራ ብ/ክ/መንግስት እ.ፌ
3 አቶ አበበ ገላጋይ ዘለቀ ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እ.ፌ
4 አቶ ከማል ሁሴን መሀመድ ከኦሮሚያ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
5 ዶ/ር ሀይሌ ኢቲቻ ቡልቲ ከኦሮሚያ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
6 አቶ ኢብራሂም መሀመድ ኢብራሂም ከሀረሪ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
7 አቶ አብድረዛቅ ሀሰን መሀመድ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
8 ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ባበከር ከቤንሻንጉል ጉምዝ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
9 አቶ አሊሚራህ መሀመድ አሊ ከአፋር ብ/ክ/መንግስት እ.ፌ
10 ኮ/ል አወል አብድራሂም ኢራሂም ከትግራይ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
11 ዶ/ር ሲራክ ሀብተማርያም ከለለው ከአማራ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
12 አቶ ወልደገብርኤል መዝገቡ ተስፋዬ ከትግራይ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
13 አቶ አስራት ሀይሌ ገብሬ ከአዲ አበባ ከተማ መስተዳደር እ.ፌ
14 አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ሆርሳ ከደቡብ ብ/ብ/ህ/ክ መንግስት እ.ፌ
15 ዶ/ር ቻን ጋትኮት ዮም ከጋምቤላ ብ/ክ መንግስት እ.ፌ
16 ኢ/ር ሀይለእየሱስ ፍስሀ አለማየሁ ከአዲስ አበበ ከተማ መስተዳደር እ.ፌ

Read 2125 times