Print this page
Monday, 18 December 2017 13:21

“የታጠፉት ገፆች”

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(6 votes)

 …. ለእሱ እውነት ያለው አየር ላይ ነው፡፡ አየሩን እንጂ በቴሌቪዥን የሚቀርበውን አየር ትንበያ ፈፅሞ አያምንም፡፡… ሰዎች በአንደበታቸው የሚናገሩት መቶ ፐርሰንት ውሸት እንደሆነ ያውቃል፡፡ በአንደበታቸው ሲጎርሩ ፊታቸውን በጥሞና ያጠናል፡፡ አይን አይናቸውን። እንደ አይን ሀኪም፡፡…ተረማምደው ደረስን ከሚሉበት የበለጠ አረማመዳቸውን ያነባል፡፡ እውነት እንዳላቸው ይገባዋል፡፡ እውነታቸው ግን የሚናገሩት ላይ አይደለም ያለው፡፡ ወይንም ለሰው ብለው ከቤታቸው ተለማምደው ይዘው አደባባይ ላይ በሚወጡት አኳሃናቸው ላይ አይደለም፡፡
እውነታቸው ያለው ራሳቸውን ለጥቂትም ቅፅበት በሚረሱበት ጊዜ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ድብን ያለ እንቅልፍ ጥሏቸውም መተወን የሚቀጥሉ አሉ፡፡ በጉራ የሚያንኮራፉ፡፡ እሱ ሰዎችን ማንበብ ይችላል። ያነበበውን ግን አይነግራቸውም፡፡ ከነገራቸው፤ ይደነግጣሉ፡፡ ግራ ይጋባሉ፡፡ ይቆጣሉ፡፡ ስለዚህ አይነግራቸውም፡፡ እያነበባቸው ይመሰጣል፡፡ እንደ መፅሐፍ፡፡
መፅሐፍትንም የሚያነበው እንደ ሰዎች ነው፡፡ በመስመሩ መሀል፡፡ ፀሐፊው መናገር ከፈለገው ጀርባ ያለው ንግግሩን፡፡ አንባቢን ለመስበክ ሲጥር፣ ጥረቱ ከምን እንደመነጨ ይገባዋል፡፡… መፅሐፉን በጣም መሸጥ የፈለገ…መፈለጉን አይገልፅም፡፡ እሱ ግን እንዳይገለፅ በጥንቃቄ የተደበቀውን ያነባል፡፡
ሰዎች የማያምንበትን የፃፈ ፀሐፊን፣ በሙሉ እምነት ተመስጠው ሲያነቡ አንዳንዴ ያጋጥሙታል። ሌላ ጊዜ ደግሞ መፅሐፍ በመፃፉ በራሱ ለመገረም ድርሰት ያበረከተን ሰው ስራ፣ በራሳቸው የማንበብ አቅም ለመደመም መፅሐፍ ሲያገላብጡ ያገኛል፡፡ ሁለት ተዋናዮች ሲናበቡ፡፡ እሱ ሁለቱንም በቀረቡበት ዋጋ አይቀበላቸውም፤ ይመነዝራቸዋል፡፡ በቃ ይሄ “ሆቢው” ነው፡፡ የሰውን እውነተኛ ማንነት ማንበብ፡፡
አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ሰዎቹም አያስፈልጉትም። ሰዎቹ የተጠቀሙበትን እቃ በማስተዋል እውነተኛ ገፃቸው ይነበብለታል፡፡ መኪናቸውን፣ ቤታቸውን…አንዳንድ ጊዜ የቤት ሰራተኞቻቸውን አይቶ ቀጣሪዎቹን ያነባል፡፡… ደግሞ “ንባቤ በጣም ትክክለኛ ነው” ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ግምቱን ተጨባጭ መረጃ ነው የሚያደርገው፡፡ ግን ተጨባጭ መረጃ ማለት ጋዜጣ ወይም የዘንድሮው የሬዲዮ ዜና ከሆነ…ምናልባት አንድ ፊቱን ግምቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡
* * *
እና ብዙ አስመሳዮች ይገጥሙታል፡፡ ወይን ጠጅ እዘው፣ ሻማ አስለኩሰው በአደባባይ የግጥም መፅሐፍ የሚያነቡ አይነቶች፡፡… የሚያነቡት የግጥም መፅሐፍ ምን እንደሆነ አሻግሮ ይመለከትና… እየተወኑ ያለው ዘውግ ይገባዋል፡፡ ጎመን የግጥም መፅሐፍን እንደ ጮማ በወይን ለማወራረድ ሲታገሉ እሱ ተሻግሮ ተቀምጦ ያስተውላቸዋል፡፡… ተውኔቱን የሚያካሂዱት ተመልካችን ለመሳብ ቢሆንም እሱ ግን ተራ ተመልካች አይደለም። የተተወነውን ሁሉ አያምንም፡፡ “ሮማንቲክ” ትዕይንት ለመፍጠር ሲጥሩ… “ቧልታይ” ይሆናሉ፡፡ መሆናቸውን ግን አያውቁትም፡፡ ሻማው ቀልጦ እስኪያልቅ ችክ ብለው ከማይረባው መፅሐፍ ጋር መታገላቸውን ይቀጥላሉ፡፡..
መምሰል እና መሆን አንድ እና ያው ሆነው አያገኝም፡፡ “ዓለም ትያትር ናት” ተዋናዮቹ ግን በደንብ መተወን አይችሉም፡፡ ማስመሰላቸውን ወደ መሆን ደረጃ ማስጠጋት ያቅታቸዋል፡፡ የራሳቸውን መኪና ሲነዱ ሰርቀው ነው የሚመስሉት፡፡ ይንቀዠቀዣሉ፡፡… ፊታቸው እንኳን በውስጡ እድሜ ልካቸውን የኖሩበት አይመስልም፡፡…መጀመሪያ፤ ፊታቸውን እንዳይቆጣ በሰላምታ ማለስለስ ያስፈልጋል፡፡… ሰላምታ በቀን አስር ጊዜ ካልተሰጣቸው ፊት ሰርቀው መልበሳቸው የተነቃባቸው ይመስላቸዋል፡፡ የተነቃ ሲመስላቸው ተንኮለኛ ይሆናሉ፡፡
…እሱ ራሱን መመልከት ነው እንጂ የማይችልበት…እነሱን ጠርጥሮ ማየት ተክኖበታል፡፡ ብዙዎቹ ከስልካቸው ጋር ነው የሚጫወቱት፡፡ ወይም ከስልካቸው ጋር ነው ሲጨንቃቸው የሚያወሩት፡፡… ከስልክ ጋር የሚጫወቱት ጥልቀት አይገኝባቸውም፡፡ እሱ መፅሐፍ የሚያነቡትን ማንበብ ያስደስተዋል፡፡ ተመስጧቸውን በማጥናት የሚተውኑት ተውኔትን ጥልቀት መለካት ይችላል፡፡… በመሰረቱ ነገር አለሙ በሙሉ ተውኔት ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን በቀላሉ አያስነቁም….፡፡ አተዋወናቸው ከልብ የመነጨ ይመስላል፡፡ እስኪያስነቁ ድረስ እሱ ያስተውላቸዋል፡፡
* * *
…እችኛዋ ሰሞኑን እዚህ ካፌ ያገኛት ናት፡፡…. ምንም ጥያቄ አልነበረውም፤ገና ዓይኑን እንዳሳረፈባት የተለየች መሆኑዋን አወቀ፡፡ ልዩ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ደስ አለችው፡፡… የካፌው በረንዳ ላይ ሆና ነው ቡና  የምታዘው፡፡ በወረቀት የተለበዱ መፅሐፍት ጠረጴዛዋ ላይ ከክርኗ ሳይርቁ ይቀመጣሉ፡፡ መፅሐፍቱን በሰው ፊት አታነባቸውም፡፡ ግን እሱ እንደምታነባቸው አውቋል፡፡… የሚያነብ ሰው እና የሚነበብ መፅሐፍ ያውቃል፡፡… ብዙ ጊዜ መፅሐፍ የሚሸፍን ሰው፣ የንባብ አሻራውን መደበቅ የሚፈልግ ነው፡፡… እቺ እንዲህ ናት። መነፅር አድርጋለች፡፡ የአይን ነው፡፡ የፋሽን አይደለም። ጭንቅላቷ ከዳሌዋ ጎላ ይላል፡፡ ጎላ ማለቱን በፍሪዝ ፀጉሯ ውስጥ ደብቃዋለች፡፡ ቀለበት አላደረገችም…ግን ባል ያደከማት ወይንም ያዳከመች መሆኗ ሰውነቷ እንደ ድመት ዘና ብሎ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥበት መንገድ ይገልፀዋል፡፡… ወይ አንዱን አባራ ሌላ ከማጥመዷ በፊት እረፍት እየወሰደች ነው፡፡… ተነስታ ከመሄዷ በፊት አንድ ሲጋራ ታጨሳለች፡፡… የተመልካችን ትኩረት ለመሳብ ወይ የራሷን ብስጭት ለመግለፅ አይደለም፡፡ በቃ ማጨስ ስለፈለገች ነው፡፡ አንገቷ ላይ እንደ ሻሽ የመሰለ ባለ ብዙ ጠቃጠቆ ሻርፕ ታደርጋለች፡፡ “ለማንም ጉዳዬ አይደለም” የሚል ተውኔትን ለማንፀባረቅ ፈፅሞ አትሞክርም፡፡ እሱ ግን ለማንም ጉዳዩዋ እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆኗል፡፡
በዛ ሰዓት ያንኑ ካፌ እሱም ማዘውተር ጀመረ፡፡ ስለወደዳት ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም ተውኔቷ አዲስ ስለሆነበት…ብቻ ነገም ደግማ እስክትመጣ ቀደም ብሎ ደርሶ ይጠብቃታል፡፡… ምናልባት መኖሪያ ሰፈሯ እዛው አካባቢ ይሆናል ብሎ እየጠረጠረ ይጠብቃታል፡፡ ሰዓት አታዛንፍም፡፡ ሶስት ሰዓት ላይ እዛ በረንዳ ላይ ናት፡፡ መፅሐፍ ከክርኗ አጠገብ ይቀመጣል፡፡ ቡናውን ቀስ ብላ ትጠጣለች፡፡
….ቀስ እያለ አጠገቧ ያለው ወንበር ላይ መቀመጥ ጀመረ፡፡ እጆቿን ያስተውላል፡፡ እጅ ብዙ ነገር ይናገራል። በእንክብካቤ ነው ያደገችው፡፡ ምንም አይነት ስራ ሰርታ አታውቅም፡፡ ኮምፒውተር ላይ በጣም ፈጣን የሚመስሉ ረጃጅም ጣቶች ነው ያሏት፡፡… ሊያናግራት ሞክሮ ያውቃል፡፡ አጭር መልስ ሰጥታው ያለ ሰዓቷ ለመሄድ ተነሳች፡፡ ከዛ በኋላ ጎኗ ላለመቀመጥ ማለ፡፡ ፈራት፡፡
በመስመር መሀል ሊያነባት አልቻለም፡፡ ተሰቃየ። የሆነ ማስተር ፒስ ነገር ሆነችበት፡፡ ጠረኗ እንደ ልጅነት ትዝታ እየመጣ ማታ ይረብሸዋል፡፡… የካፌውን አስተናጋጆች ስለ ማንነቷ ጠይቆ አጥጋቢ መልስ አላገኘም፡፡… አድራሻዋን ማወቅ አልፈለገም፡፡ አድራሻ ምንም አያደርግለትም፡፡ የምታነበውን መፅሐፍ ብትሰጠው በደንብ ያውቃት ነበር፡፡ እሷን ከማንበብ የምታነበውን መፅሐፍ ማንበብ ይቀላል፡፡
…ከብዙ ክትትል በኋላ አንድ ቀን በጋዜጣ- ያልተለበደ መፅሐፍ ይዛ መጣች፡፡ የአማርኛ መጽሐፍ። ትንሽ ሳትቸኩል አትቀርም የዛን ቀን፡፡ የቡናዋን ከፍላ ሲጋራዋን በጥድፊያ አጭሳ ተነሳች፡፡…ወጣች፤ አልተመለሰችም፡፡ ጠረጴዛው ላይ የተወችውን መፅሐፍ፣ እሱ ተሸጉጦ ከሚያስተውልበት ተንደርድሮ አነሳው፡፡… እንደ ሌባ በጉያው ሸጉጦት፣ ከዛ አካባቢ ተሰወረ፡፡
ሌላ ስፍራ ሄዶ ይገላልጠው ጀመር፡፡ መፅሐፉ የበዕውቀቱ ስዩም “ስብሰብ ግጥሞች” ናቸው፡፡… መፅሐፉ ላይ ያለውን ግጥም ሳይሆን የመፅሐፍ ባለቤቲቷን አሻራ ለማንበብ ገፆቹን በጥንቃቄ ያገላብጥ ጀመር፡፡
በመግቢያው ገፅ ላይ “T” የሚል አንድ ፊደል ሰፍሯል፡፡…የእሷ ስም መሆን አለበት ብሎ አሰበ፡፡…ወይ “ፅጌ”… “ፀደኒያ”… ፀሐይ እንኳን አትሆንም፡፡ በቃ “ፀ” ብዬ ልያዛት አለ፡፡
እያንዳንዱን ገፅ በጥሞና መመርመር ጀመረ። አንዳንዶቹ ግጥሞች ያሉበት ገፅ ጆሮው ታጥፏል፡፡ ለምሳሌ ገፅ አስራ ስምንት፣ “ሞኝ ፍቅር” የሚለው፡፡
“ለሱ
ሰው ብቻ አይደለችም
ጠፈር ናት ባካሏ
መሬት ናት በነፍሷ
ዕድሜ ልኩን ቢሮጥ
አያመልጥም ከሷ፡፡”
ይላል ግጥሙ፡፡ ፌመኒስት ናት ብሎ አሰበ፡፡  ወይንም ጥሏት የሄደው ወንድ ተመልሶ መጥቶ መለመኑ አይቀርም ብላ አስባ ይሆናል…እያለ ገፆቹን ማጥናት ቀጠለ፡፡ ሌላ የታጠፈ ገፅ አገኘ- “ይድረስ ለአድርባይ ጓዴ” ይላል የግጥሙ አርዕስት፡፡
“እየለየ ጊዜ ቦታ እየመረጠ
እስስታማ መልክህ ገፅኽ ተለወጠ
አህያ እንዳልነበርክ በሰርዶዎች መሀል
አህዮች ሲበዙ ዛሬ ጅብ ሆነሀል”
ይኼም ያው ጥሏት የሄደው ሰውዬ የበደላትን የሚገልፅ ግጥም መሰለው፡፡ የሆነ አህያ ሰው ጋር ነው ፍቅር ይዟት የነበረው፡፡ ግን ፍቅሩ ወጥቶላታል፡፡ ለዛ ነው “አድርባይ ጓዴ” ብላ የጠራችው፡፡…የታጠፉት ገፆች የተወሰኑ ናቸው፡፡.. እየመረጠ፣ በከፍተኛ ጥሞና ማንበቡን ቀጠለ፡፡ የግጥም መፅሐፉን ከዚህ በፊት አንብቦታል፡፡ አሁን ግን እያነበበ ያለው እሷን ነው፡፡ “ፀ”ን፡፡ የእሷን ደብዳቤ ነው በግጥሞቹ ውስጥ ተፅፈው ያገኛቸው፡፡
ቀጥሎ “የባይተዋር ገድል” የሚለው መልዕክቷን አነበበው፡፡ ገፁን በደንብ አድርጋ ነው ያጠፈችው፡፡ ምን ያህል ባይተዋር ሆና እንደተሰቃየች ወለል ብሎ ታየው። እንደዛ በረንዳ ላይ ተቀምጣ እያያት የሰበሰው ምስል ሁሉ በዚህ ግጥም ውስጥ መልሶ መጣበት፡፡ የግጥሙ የመጨረሻው ስንኞች በጥቁር ቀለም ተሰምሮባቸዋል፡፡
“…በሌሊት ወፍ ምትክ፣ ክንፍ ያወጣ ሌሊት፣ ጎጆህን ሲዞረው
መረሳት የሚሉት፣ የኑሮ ገባር ወንዝ፣ አልጋህን ሲገምሰው
 “መንሳፈፉስ ይቅር፣ መስጠም ያቅተዋል ሰው” ሲያሰኝህ እድልህ
 ያኔ ይጀመራል፣ የባይተዋር ገድልህ”
…የእሷን ድምፅ አንዴ ብቻ ነው የጠየቃትን አልባሌ ጥያቄ ስትመልስለት ያዳመጠው፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ፡፡ ያችኑ ትዝታውን ተጠቅሞ ግጥሙን ሲያነብ፣በህሊናው የእሷ ድምፅ ነበር በለቅሶ ዜማ የሚንሾካሾክበት፡፡… ህመሟ ቁልጭ ብሎ ታየው፡፡ እንባው እንደ ሳግ ጉሮሮው ላይ መጥቶ ተጠራቀመበት፡፡… ሳያስበው አንድ ነገር ተገለፀለት፤ እቺን ልጅ ከገባችበት ሀዘን ለማውጣት ከነገ ጀምሮ እንደሚጥር፡፡ “ይኼ ተውኔት አይደለም” አለ ለራሱ፡፡ ይኼ እውነተኛ የሰው ነብስ ሀዘን ነው፡፡ እደርስላታለሁ…፡፡ ብሎ በሀይል ማለ፡፡
የመጨረሻው የታጠፈ ገፅ ላይ ያለውን ግጥም፣ እንባ ብዥ ባደረገው አይኑ፣ ጉሮሮው ላይ ያለውን ሳግ ለመዋጥ እየታገለ አነበበው፡፡ “ምንቸት እና ጋን” ይላል አርዕስቱ፡፡
“ይኑሩ እንጂ ባ’ገር
በቀዬ በሰፈር
ኩሬ ሙሉ ውኃ፣ ምድጃ ሙሉ ሻይ
ዳውላ ሙሉ አፈር
የምንቸቶች ስፍር መች በጋን ይለካል
ጋኖች እንኳን ቢያልቁ ሌላ አፈር ይቦካል፡፡”
በገፁ ላይ ጠብ ያለውን እንባ ሲጠርግ፣ የድል አድራጊነት መንፈስ እየዋጠው ነበር፡፡ ያ አህያ ባሏ ጥሏት ቢሄድ…ሌላ አፈር ይቦካል፡፡ እኔ እሱን እተካዋለሁ፡፡ እንደኔ የሚረዳት የለም፡፡ እንደኔ እሷን ማንበብ የሚችል የለም፡፡…ድንገት እርግጠኛ ሆነ- እቺ ሴት “ፐ”… “ፀ” የእሱ እጣ ፋንታ መሆንዋን አመነ፡፡
ቀኑ እንዴት እንዳለፈ አያውቀውም፡፡ ግጥሞቹን ከገጣሚው በላይ ተረዳቸው፡፡ የሚረዳቸው ደግሞ በእሷ አንፃር እያደረገ ሲተረጉማቸው ነው፡፡ ገፃቸው የታጠፉትን ብቻ ሳይሆን ያልታጠፉትንም… ልክ እንደ እሷ ደብዳቤ እያሰባጠረ አነበባቸው፡፡
በተከታዩ ቀን ካፌው ገና ሳይከፈት ቀድሞ ተገኘ። እሷ በሰዓቷ መጣች፡፡ ግን ብቻዋን አልነበረችም። ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ጠና ያለ ሰውዬ ጋር ነው የመጣችው፡፡ አጎቷ ለመሆን እድሜው ትንሽ ያጥራል፤ ግን እኩያዋ ለመሆንም ይበዛል፡፡ ጥጥ እራስ ነገር ነው፡፡
እሱ… አዘጋጅቶ የመጣው ዲስኩር ጠፋበት። ሽማግሌው ሰውዬ ከየት መጥቶ ህልሙ መሀል እንደገባበት አላወቀም፡፡… በስንት መከራ ኪሱ ውስጥ የሸጎጣትን የግጥም መፅሐፍ በቀስታ አውጥቶ ወደ “T” አቅጣጫ ሰደደው፡፡…የእጅ አዘረጋጉ ሊኮረኩራት እንደከጀለ አይነት ከተሸማቀቀች በኋላ… መፅሐፉን ስታየው…ስትለየው ድንገት ፈገግ አለች፡፡
“ትላንት እዚህ ጥዬው ሄጄ ነው?” ብላ ጠየቀችው፤ ግልፅ በሆነ የዋህ አንደበት፡፡
“አዎ” አላት እሱ፡፡
“…መፅሐፌን ብትጥይው ኖሮ አልለቅሽም ነበር” አለ አጎትየው፡፡ እና ጠጋ ብሎ “አሁን ሳሚኝና መፅሐፌን ስጭኝ…” አላት፡፡
ሳመችው፡፡ አጎትየው ፍቅረኛዋ ሆነ፤ ሲሳም፡፡
“የግጥሙን መፅሐፍ እሱ ነው የሚወደው…እንኳን አልጠፋ…አይለቀኝም ነበር፡፡” አለች፤ ወደ እሱ ዞር ብላ እንደ ማስረዳት፡፡ ከዛ ወደ አጎቷ ተመለሰች፡፡
እሱ ምንም ሳይናገር ከጎናቸው ተነስቶ ሌላ ቦታ ቀየረ። መሄዱን ልብ አላሉም፡፡ … የሆነ ጥግ ተወሽቆ ሁለቱ ሲዳሩ፣ እሱ ብቻ ማየት የሚችለውን ጥናት ማድረግ ቀጠለ፡፡ በመስመር መሀል ማንበቡን፡፡ መስመሮቹ ግን ብዥ ብለው ያበጡ ሰንበሮች ይሆኑበታል፡፡…ቢሆኑም ማንበቡን አያቋርጥም፡፡

Read 3863 times