Monday, 18 December 2017 13:15

የተመራቂው ወግ

Written by  መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

(የአጭር አጭር ልብ ወለድ)
            
   ሰፈሪቱ በሰው ተጎርሳለች፡፡ ምኗም አይታይ፤ ሰው ብቻ! እቅፍ አበባ የታቀፉ ሰዎች! የተመራቂዎች ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ! … ግቢው ውርወሩን ተነፍጓል፤ስለሚሸኛቸው ተማሪዎች የተከዘ ይመስላል፡፡ መመረቂያ አዳራሹ ጠቁሯል። በጥቁር ጋዋን፣ በጥቁር ኮፍያ፡፡ … ስሙ ተጠራ፤ የግቢው አንደኛ ‹ሰቃይ!›
ጭብጨባ፣ ፉጨት! የተሰማውን ይገልፅ ዘንድ ‹ማይክ› ተሰጠው፡፡
“እንኳን ደስ አላችሁ እ …” የጭብጨባው ስለት ድምፁን ቆረጠው፡፡
ከቆመበት ቀጠለ፡፡
“…. ንዳልላችሁ፤ ደስ እንዳላችሁ ደስ ባለው አዕምሮዬ ማሰብ ቸገረኝ፡፡” ቤቱ በፀጥታ አዘቅጥ ተዋጠ፡፡
“… ፊታችሁ ላይ የማየው የእውነት ሳቅ ነው ወገኖቼ?! አልመሰለኝም፡፡ የእውነት ሳቅ አይደለም። ነጭ እንባ ነው ጥርሳችሁ ላይ የሚታየኝ፡፡ ዐይናችሁን የሞላው ደስታ አይደለም፡፡ የሟሟ ተስፋ ነው፤ ከዐይነ ውሀችሁ የሚነበበኝ! የስኬት ቅባት አይደለም ፊታችሁን ያወዛው፤ የፍርሀት ላብ ነው! የእውነት ፍርሃት! ስለዚህ እንኳን ደስ አላችሁ አልልም፡፡”
ቤቱ ድምፅ ፈጠረ … ሹክሹክታ! … ግርምታ!
“ወንድምና እህቶቼ ሆይ፤ እኔም ደስ አላለኝም። ይህን ዋንጫ ማግኘቴ ለኔ ምኔም አይደል፡፡ አንድ እውነት ልንገራችሁ፤ መማር ከምንም ተነስቶ ወደ ራስ መድረስ ነው፡፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስገባ ከራሴ ውስጥ መውጣት ጀመርኩ፡፡ ይህን ጅምር ከግብ አድርሼ ስፈፅም፤ ይኸው ዩኒቨርሲቲያችን ሸለመኝ። … ዓለም ወለፈንድ አይደለች?! የመማርን መልካምነት ሌኒን ሰብኳል፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ራስ መጓዝ ይበልጣል እላለሁ፡፡ ደስተኛ አይደለሁም ብያለሁ፡፡ ደስተኛ አይደላችሁምም ብያለሁ፡፡ ደስተኛ መሆን ካለብኝ ደስተኛ የምሆነው ይህን ዋንጫ በመውሰዴ ሳይሆን ደስተኛ እንዳልሆናችሁ እናንተ ሳታውቁ፤እኔ ልነግራችሁ በመቻሌ ነው፤ግን አሁንም አይደለሁም፤ ምክንያቱም ከራሴ ውጪ ነኝ!! … አመሰግናለሁ፡፡”
 መደነቅ በሁሉ ልቦና ሞላ!
ግራ መጋባትም በሁሉ ፊት ላይ ደመቀ!
ከአዳራሽ ወጥተው ተመራቂዎች ከቤተ ዘመድ ሲገናኙ በራሪ ወረቀቶች ከወላጅ ወደ ወላጅ ሲወረወሩ ታዩ፤ … ከሰው ወደ ሰው ሲሸጋገሩ፡፡
“ውድ ወላጆች፡- ህልማችሁ ልጆቻችሁ ትልቅ እንዲሆኑላችሁ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እነሆ ዛሬም ‹ትልቅ ሰው ሆኑ› ብላችሁ ጮቤ እረግጣችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‹ልጆቻችሁ ትልቅ ተቋም ገብተው፤ ትንሽ ሆነው ወጡላችሁ!› ይሄን አምናችሁ ለመቀበል እንደማትፈቅዱ አውቃለሁ። ግና ከእውነት ብትሸሹም ሽሽታችሁ የትም አያደርሳችሁም፡፡ ለምን? ካላችሁ፤ ለእውነት ውሸት የሚል ስም አውጥተን ራሳችንን እንሸነግላለን እንጂ ከእውነት ወጥተን መኖር አንችልማ፡፡
አሁንም እላችኋለሁ፡- ልጆቻችሁ ሰውነታቸውን ጥለው፤ ሰው የመሆን ክብር ሳይገባቸው፣ ከእንስሳት ያነሱ ሆነው ተመረቁላችሁ፡፡
ለሰው ክብርና ፍቅር የሌለው ሰው፣ ለራሱ ክብር የለውም፡፡ ራሱን የማያከብር ደግሞ ሰው ሳይሆን ግዑዝ ነው፡፡ ምክንያቱም እንስሳትም ክብርና ፍቅር ያውቃሉ፡፡ ልጆቻችሁ ግን እርስ በእርስ በብሔርና በሃይማኖት ተቧድነው የሚባሉ አውሬዎች ሆነዋል። ገዝጋዥ ጥርስ አብቅሎ ያሾለላቸው ደግሞ ሳያውቁ ‹አወቅን› ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ‹ማንነታችንን አወቅን› ብለው ሰው የመሆንን ታላቅነት ጥለዋል፡፡ የማንነት ምንነት ተዛብቶባቸዋል፡፡
እናም ልጆቻችን ተምረው መጡ እንዳትሉ። ርህራሄና ፍቅርን ሸጠው መጡ በሉ፡፡ እናንተ ፍቅር አውቃ ልብ ነው ያላችሁ፡፡ ልጆቻችሁ ግን ጥላቻን፣ ግድያን የሚጠነስስ አዕምሮ ነው ያላቸው። መማራቸውም ያስገኘላቸው ታላቅ ጥበብ ወንድማቸውን የሚያቆስሉበትን፣ የሚያገሉበትን የጥላቻ ስልት አነዳደፍ ነው፡፡ … እና ከውጭ ጠላት ይልቅ ልጆቻችሁን ፍሯቸው፡፡
መማር ከተፈጥሮ የሚያርቅ መንገድ ከሆነም ልጆቻችሁን ዳግም ወደ ዩኒቨርሲቲ ላለመላክ ለራሳችሁ ቃል ግቡ፡፡ ምክንያቱም አለመማር ውስጥ ንፁህነት አለ፡፡ ምክንያቱም አለመማር ውስጥ የዋህነት አለ፡፡ ሳያሳውቅ እንዳወቅን እንድናስብ በሚያደርገው ወለፈንድ ትምህርት ውስጥ ከማንነት መራቅና መሰሪነት፤ ከፍ ሲልም አረመኔነት ይገኛል። ወገኖቼ፤መማር የነፍሳችንን መንገድ ውስጣችንን ካልዘረጋ፣ የፍቅርን ሰንደቅ ከልባችን ከሰወረ ቢቀርብንስ?!”
ባለ ዋንጫው!
የማይነበብ ፊርማ!


Read 2108 times